የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በዕለተ እሁድ በወልድያ ፣ በአርባምንጭ እና በሶዶ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላል። ሦስቱን ጨዋታዎች በተናጠል እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።
ወልድያ ከ መቐለ ከተማ
ወልድያ በደካማ አጀማመር እና በክለቡ ዙሪያ እየወጡ ባሉ አሉታዊ ዜናዎች ታጅቦ መቐለን ያስተናግዳል። የመጀመሪያ ጨዋታውን ድል በማድረግ አመቱን የጀመረው ወልድያ ከእዚያ በኃላ ግን ወደ አሸናፊነቱ መመለስ አልቻለም። በተቃራኒው መቐለ ከተማ በተከታታይ ሶስት ጨዋታዎች አቻ ቢለያይም ሳምንት ጅማ አባጅፋርን መርታት ችሏል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ መጋራቱም በራሱ እንዳዲስ አዳጊ ክለብ ትልቅ ውጤት ነበር።
እንግዳዎቹ መቐለዎች በጊዮርጊሱ ጨዋታ ላይ እንደታዩት የአማካይ ክፍላቸውን ወደኃላ አስጠግቶ በመጫወት እና የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን በመጠበቅ እንደ ጋይሳ አፖንግ እና አቼምፖንግ አሞስ ባሉ ጉልበተኛ አጥቂዎቻቸው የሚጠቀሙበት ሂደት አስፈሪ ያደርጋቸዋል። በማጥቃቱ ረገድ የአማኑኤል አለመኖር የቡድኑን የመስመር ስልነት የሚቀንሰው ቢሆንም የቡድኑ ሌላ ጠንካራ ጎን በሆነው ያሬድ ከበደ አማካይነት ከፊት የሚሰለፈው አጥቂ ኳሶችን ማግኘት እንደማይቸገር ይታሰባል።
አሰልጣኝ ዘማሪያም የተገደበ የአማካይ ክፍል ምርጫ ያላቸው መሆኑ ቡድኑ ውስጥ ካለው ጥሩ ያልሆነ መንፈስ ጋር ተዳምሮ ለወልድያ ነገሮችን ሊያከብዱበት እንደሚችሉ ይገመታል። ምንአልባት ቡድኑ እስካሁን በሜዳው ግብ አለማስተናገዱ ጥሩ የራስ መተማመን የሚፈጥርበት መሆኑ እና በሊጉ ልምድ ያላቸው ሌሎች ተጨዋቾችን መያዙ መቐለ ከተማ ላይ ቀድሞ ግብ አስቆጥሮ ነገሮችን ለመቆጣጠር ዕድል ሊሰጠው እንደሚችልም የሚገመት ነው።
ወልድያ ወሳኙ ተከላካይ አዳሙ መሀመድን በረጅም ጊዜ ጉዳት ማጣቱ የሚታወስ ሲሆን አንዷለም ንጉሴ እና ተስፋውን ሸጋውም የጉዳት ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል። ከዚህ ውጪ ተስፋዬ አለባቸው እና ብሩክ ቃልቦሬ ለሴካፋ ዋንጫ ወደ ኬንያ አምርተዋል። በተመሳሳይ መልኩ መቐለ ከተማም አምኑኤል ገ/ሚካኤልን ለብሔራዊ ቡድን ሲያስመርጥ በጉዳት የሚያጣው ተጨዋች ግን አይኖርም።
ፌ/ዳ ኢሳያስ ታደሰ በዋና ዳኝነት እንዲሁም ፌ/ዳ ሙሉነህ በዳዳ እና ፌ/ዳ አሸብር ታፈሰ በረዳት ዳኝነት በጨዋታው ተመድበዋል።
አርባምንጭ ከተማ ከ መከላከያ
አርባምንጭ እና መከላከያ በሊጉ ተመሳሳይ ጊዜን እያሳለፉ የሚገኙ የአምስተኛ ሳምንት ተጋጣሚዎች ናቸው። ሁለቱም በአራት ሳምንታት ጉዟቸው ማሳካት የቻሉት ነጥብ ሁለት ብቻ ሲሆን አርባምንጭ ሁለት መከላከያ ደግሞ አንድ ግብ ብቻ መስቆጠር ችለዋል። አምና 25ኛ ሳምንት ላይ በአርባምንጭ ተገናኝተው 1-1 ተለያይተው የነበሩት ቡድኖቹ ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ ቢያንስ በአንዳቸው የሊግ ጉዞ ላይ ነፍስ ሊዘራ እንደሚችል ይጠበቃል። እንደ 2009ኙ ጨዋታው በአቻ ውጤት ከተጠናቀቀ ግን ሁለቱም ካሁኑ የዘንድሮ ጉዟቸው በስጋት መሞላት ይጀምራል።
እስካሁን ድረስ የአማካይ መስመሩን ችግር ማሻሻል ያልቻለው መከላከያ በቁጥር የበዙ አማካዮችን ከሚጠቀመው አርባምንጭ ጋር የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ጨዋታውን ማድረጉ እንዲቸገር ሊያደርገው ይችላል። ሆኖም የአርባምንጭ የአማካይ ክፍል በራሱ በውህደት ረገድ ብዙ የሚቀረው መሆኑ ጥያቄ እንዲነሳበት ያደርጋል። ከዚህ ይልቅ መከላከያ በምንይሉ ወንድሙ እና ተመስገን ገ/ፃዲቅ የግል እንቅስቃሴ ላይ ተመስርቶ ግቦችን ለመፍጠር እንደሚሞክር ይገመታል። በተመሳሳይ አርባምንጭም ከወንድሜነህ ዘሪሁን በሚነሱ ኳሶች ላይ ተመስርቶ ከፊት ለሚኖረው አጥቂ ዕድሎችን ሊፈጥር ይችላል። በጥቅሉ ግን ቡድንኖቹ ካሉበት ጫና አንፃር ቀድሞ ግብ ያገኘ ቡድን ጨዋታውን በጠባብ ውጤት የማሸነፍ ዕድሉ ሰፊ እንሰሆነ ግልፅ ነው።
እንዳለ ከበደ እና ተመስገን ካስትሮ ከአርባምንጭ ከተማ ቴዎድሮስ በቀለ ደግሞ ከመከላከያ በቤሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት ይህ ጨዋታ ያመልጣቸዋል። በጉዳት ዜና ለረጅም ጊዜ ከሜዳ የራቀው አማኑኤል ጎበና እና ወንደሰን ሚልኪያስ ከአርባምንጭ ከተማ ከጨዋታው ውጪ ሲሆኑ የመከላከያው አዲሱ ተስፋዬም በተመሳሳይ ለጨዋታው አይደርስም።
በዋና ዳኝነት ፌ/ዳ አሰፋ ደቦጭ ሲመደብ በረዳት ዳኝነት ፌ/ዳ ካሳሁን ስዩም እና ፌ/ዳ ሰለሞን ተስፋዬ ጨዋታውን ይመራሉ።
ወላይታ ድቻ ከ ድሬደዋ ከተማ
የጦና ንቦቹ መልካም አጀማመር ቀስ በቀስ ትዝታ የሆነ ይመስላል። ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ማሳካታቸው አመቱን በተስፋ እንዲጀምሩ ቢያደርጋቸውም በተከታታይ መሸነፋቸው ቀጣይ ጉዟቸውን ፈታኝ አድርጎታል። የብርቱካናማዎቹም የአራት ሳምንት ጉዞ ደብዛዛ የሚባል አይነት ነው። ሜዳቸው ላይ ጅማ አባ ጅፋርን 1-0 ካሸነፉበት ጨዋታ ውጪ ማሸነፍም ሆነ ግብ ማስቆጠር ለድሬዎች ከባድ ሆኗል።
የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን የማጥቃት ስትራቴጂ ጥያቄ ውስጥ በገባበት ወቅት በቀላሉ ክፍተት ከማይሰጥ ቡድን ጋር መገናኘቱ ፈተናውን ከፍ ያደርግበታል። በአመዛኙ በጃኮ አራፋት እንቅስቃሴ ላይ መሰረት ያደረገው የድቻዎች የማጥቃት አቀራረብ የመከላከል ባህሪ ባላቸው አማካዮች በተሞላው የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን ላይ በርካታ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የመስመር ተመላላሾቹ እና የመስመር አጥቂዎቹ የማጥቃት ተሳትፎ በእጅጉ ያስፈልገዋል። ድሬዎች ይዘውት ከሚገቡት መከላከል ላይ የተመሰረት አጨዋወት በመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀም በሶስት ተከላካዮች በተደራጀው እና ከፊቱ የሁለት አማካዮችን ሽፋን ከሚያገኘው የድቻ የኃላ መስመር ጋር መጋፈጥ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ጨዋታው ላይ ጎሎችን ለመመልከት አዳጋች ሊሆን እንደሚችል እና የግብ ዕድሎችም በብዛት ከተጨቾች የግል ስህተት ሊመነጩ እንደሚችሉ የሚያስገምት ነው።
የቡድኑ አምበል ተክሉ ታፈሰ እና በዛብህ መለዮ በጉዳት ፀጋዬ ብርሀኑ በቤሔራዊ ቡድን ጥሪ በጨዋታው ለወላይታ ድቻ አገልግሎት አይሰጡም። ድሬደዋ ከተማም ጉዳት ላይ የሚገኙትን ወሰኑ ማዜን እና ያሬድ ታደሰን የማይጠቀም ይሆናል።
ፌ/ዳ ላቀው ደጀኔ እና ፌ/ዳ ትንሳኤ ዘለቀ በረዳት ዳኝነት እንዲሁም ፌ/ዳ ሚካኤሌ አራአያ በዋና ዳኝነት ጨዋታውን ይመሩታል።