የአሰልጣኞች ገጽ | የአስራት ኃይሌ 40 አመታት የዘለቀ ስኬታማ ጉዞ [ክፍል 2]

በአሰልጣኞች ገፅ አምዳችን የአንጋፋው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ለ4 አስርት አመታት የዘለቀ የአሰልጣኝነት ጉዞ ፣ የስኬት መንገዶች እና ታሪኮች በክፍል አንድ አቅርበንላችኋል፡፡ በዛሬው የክፍል ሁለት ዝግጅታችን ደግሞ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በአሰለጣጠን መንገዳቸው፣ በዘመናቸው ስለነበሩ አሰልጣኞች እና ቅድሚያ ስለሚሰጧቸው መርሆዎች የሰጧቸው ምላሾችን አቅርበንላችኋል፡፡


በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


የክፍል አንድ ጽሁፍን እዚህ ያገኛሉ ፡- የአሰልጣኞች ገጽ | 40 ዓመታት የዘለቀው የአስራት ኃይሌ ስኬታማ ጉዞ [ ክፍል አንድ ]



ከአሰልጣኝነት ጅማሮ እንነሳና ወደ ሰልጠናው ህይወት እንዲገቡ በጎ ተጽዕኖ ያሳረፈብዎ አሰልጣኝ ማን ነበር ?

ተጽእኖ ያሳረፈብኝ አሰልጣኝ ሉቺያኖ ቫሳሎ ነው፡፡በስልጠናው አለም የተከተልኩት የአሰራር መንገድም የሱን ነው፡፡ ሉቺያኖ እጅግ በጣም ጠንካራ ስብዕና ነበረው፡፡ ስነምግባር ላይ ያለውም አቋም የተለየ ነበር፡፡ ልምምዶችን በጥሩ ሁኔታ ያሰራሀል፡፡ ከሰራህ በኋላም በቂ እረፍት እንድታደርግ ያደርግሀል፡፡ በስብዕናህ ላይ ይሰራል፡፡ ቁጥጥሩም ሀይለኛ ነው፡፡ ከሰፈር ተነስቼ ለብሔራዊ ቡድን ተጫዋችነት የደረስኩት እሱ ጋር በሰራሁት ስራ ነው፡፡ በሙያዬ እንደ ምልክት የማየው ታላቅ ሰው ነው፡፡ የሱን ፈለግ ተከትዬ በመጣሁበት ሒደት እኔም አላፈርኩም፤ እሱንም አላሳፈርኩም፡፡ ሉቺያኖ አንድ ጊዜ እዚህ መጥቶ በነበረ ጊዜ ‘የእኔን ፈለግ የተከተለው አስራት ነው፡፡’ ብሎ መስክሮልኛል፡፡


ከወሰዷቸው የአሰልጣኝነት ኮርሶች በተጨማሪ ራስዎን ያበቁበትበት የተለየ መንገድ አለ?

በአጨዋወት ረገድ ወግ አጥባቂ የምባል አሰልጣኝ አይደለሁም፡፡ በአለም አቀፋዊ እውነታ እግር ኳስ የወቅታዊነት ባህሪን የተላበሰ ስፖርት ነው፡፡ በቀደመው የአሰራር መንገድህ ብቻ የምትጓዝ ከሆነ አለም አቀፋዊው የስልጠና ባህሪ አልገባህም ማለት ነው፡፡ ሁሌም ቢሆን በእግር ኳስ በሒደት የሚሻሻሉ፣ የሚያድጉ እና የሚለወጡ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ 3-5-2 ፎርሜሽንን ውሰድ፡፡ ይህ ሲስተም ከቀደመው ጊዜ ይልቅ ወደ ተለያዩ ፎርሜሽኖች ተከፋፍሎ በበርካታ ታክቲካዊ አቀራረቦች ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ መጽሀፎች በየጊዜው የሚኖሩትን አዳዲስ እግር ኳሳዊ ሐሳቦች ያስገነዝባሉ፡፡ በሜዳ ውስጥ ስለሚኖሩ ታክቲካዊ ጉዳዮች እና የአጨዋወት ዘይቤዎችም አለማቀፋዊ መልክን ያሳያሉ፡፡ ስለዚህም በየጊዜው በታክቲካዊ ጉዳዮች መሻሻል ታሳያለህ፡፡ በአካል ብቃቱ ጉዳይም ተመሳሳይ ነው፡፡ እኔ በባህሪዬ ሌሎች ያላዩትን በማየት አዳዲስ ነገሮችን ለመስራት እደፍራለው፡፡ ተጫዋቾቻችን ብዙ ቢሰራባቸው የተሻለ ነገር ሊያሳዩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡

የእግር ኳሳችን ስርዓት አለማቀፋዊውን መንገድ እንድንከተል የሚያግዝ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአካል ብቃቱ በኩል የስልጠናውን አይነት፣ ቆይታውን፣ ድግግሞሹን፣ ሪከቨሪውን እና ሌሎችንም አገናዝበህ ነው መስራት ያለብህ፡፡ በተጫዋችነት ዘመናችን እንዲህ አይነት አሰራር አልነበረም፡፡ ድሮ ድሮ ልምምድ ላይ ከደከመህ ‘ ማታ ሲጠጣ አድሮ እኮ ነው፡፡’ ነው የምትባለው፡፡ ስለ ዲሀይድሬሽን ማንም ቁብ ሰጥቶ የሚያስብ አልነበረም፡፡ በእረፍት ሰዓትም ውሃ ስትጠጣ ከታየህ  ‘ሲጠጣ አድሮ ራዲያተሩ ፈላ፡፡’ ትባላለህ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን በልምምድ ወቅት በየአስራ አምስት ደቂቃው ተጫዋቾችህ ውሃ እንዲጠጡ ታደርጋለህ፡፡ ጫና ባላቸው ሥራዎች ላይ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በሙሉ ከአለምአቀፍ ወቅታዊ አሰራሮች ታገኛለህ፡፡ በሳምንት አንድ ጊዜ የሚጫወት ቡድን ምን አይነት ልምምድ መስራት አለበት? ሁለት ጊዜ የሚጫወትስ? ለነዚህ እና መሰል ጥያቄዎች ከወቅታዊና አለምአቀፋዊ አሰራሮች ምላሽ ትሰጣለህ፡፡

ታክቲካዊ ጉዳዮችን በተመለከተም በተጫዋቾች የሜዳ ውስጥ ሚና ተቀያያሪነት የተለያዩ መረጃዎችን አነባለው፡፡ ይህንንም በስራዬ ለመተግበር እሞክራለው፡፡ Poliometric Exercise (የዝላይ ልምምድ – በአጭር የጊዜ ልዩነት በድግግሞሽ ጡንቻ ከፍተኛ የሆነ ጉልበት እንዲያወጣ በማድረግ የሰውነት ኃይልን መጨመር እና ፍጥነትን ከፍ የሚያደርግ የልምምድ አይነት)ን እንመልከት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በደምብ እየተሰራበት ያለ የልምምድ አይነት ነው፡፡ እኔ ግን ቀደም ብዬ የማሰራበት የስልጠና አይነት ነው፡፡  እንዲያውም አንዳንዴ ‘ፈጥኛለው ማለት ነው እንዴ? ‘ ብዬ ራሴን እጠይቃለው፡፡ ተጫዋቾች እያለን ሉቺያኖ የ ‹‹5 ለ 2 ›› ጨዋታ ያጫውተን ነበር፡፡ አሁንም እንደ አዲስ ይሰራበታል፡፡ ይህንን ስታይ ወግ አጥባቂ አሰልጣኞች ምድብ ውስጥ አትመድበኝም፡፡ በአጭሩ ወቅቱ የሚፈልገውን የስልጠና መንገድ እከተላለው፡፡


የአሁኑ ዘመን አሰልጣኞች በቂ እንቅልፍ የሚተኙ ይመስለኛል፡፡ በፊት እኛ ወደቅን፤ ተነሳን በማለት እየተጨነቅን የምንተኛው የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነበር፡፡


ሌላ ጉዳይ ላንሳልህ፡፡ በPressing Football (ተጋጣሚን  በራሱ የሜዳ ክልል ተጭኖ የመጫወት ዘይቤ) የትኛው የሜዳ ክፍል የበለጠ ዋጋ አለው ቢባል? በእኔ እምነት የመሀል ክፍሉ ዋነኛ ሚና ይጫወታል እላለሁ፡፡ በቡድኔ ውስጥ ለአማካዮች ከፍተኛውን ትኩረት እሰጣለሁ፡፡ ፎርሜሽንን በተመለከተም በተጫዋቾች ፍጥነት፣ አካል ብቃትና ችሎታ ላይ በመወሰን እና በማዘጋጀት 3-5-2፣ 4-4-2 ና 4-2-3-1ን ለመተግበር እሞክራለው፡፡ በደደቢት 4-2-3-1ን የተጠቀምኩት በቡድኑ ውስጥ የነበሩት ተጫዋቾች የአጨዋወት ባህሪ ለዚህ ፎርሜሽን አመቺ ነበሩ ብዬ በማመኔ ነው፡፡ በክለቡ ብዙ ጨዋተዎችን ያሸነፍኩት በዚህ ፎርሜሽን ነበር፡፡ እኔ ከወጣው በኋላ ግን ወደ 4-4-2 እንደተመለሱ አይተናል፡፡ በ4-4-2 ፎርሜሽን ፊት መስመሩ  በጌታነህና ዳዊት የተዋቀረ ነበር፡፡ ሁለቱም ተመሳሳይ የአጨዋወት ባህሪ ያላቸው አጥቂዎች በመሆናቸው በ4-4-2 ውጤታማ ላይሆኑ እንደሚችሉ ሰፋ ያለ ትንተና አቅርቤ ነው የለቀቅኩት፡፡ የዘመኑ ቴክኖሎጂ በቤትህ ሆነህ ብዙ እንድትማር ስለሚያግዝህ የወቅቱን የእግር ኳስ አጨዋወት ዘዴዎችን በጥልቀት እቃኛለው፡፡ የበፊቱን ካነሳን ጊዜው እንዳሁኑ በቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት የማታገኝበት በመሆኑ በአንድ የስልጠና መንገድ ረጅም ጊዜ ትቆያለህ፡፡ አሁን ግን በየጊዜው ተቀያያሪና ራስህን የምታሻሽል መሆን ይኖርብሀል፡፡

አንዳንዴ ለከባባድ ጨዋታዎች ዝግጅት ተጫዋቾቼን በእርሻ ውስጥ ሁሉ አስሮጣቸው ነበር፡፡ በዚህ ልምምድ አካላቸው እጅጉን ይጠነክራል፡፡ይህን የማደርገው ግን በመጀመርያ እኔ ራሴ ሮጬ ነው፡፡ በተደጋጋሚ እኔ ሮጬ ምንም ካልሆንኩ እነሱን አስሮጣለው፡፡ሁሌም ‘አስራት ሰርቶ እንዴት እኛ ያቅተናል?’ የሚል ስሜት እንዲሰማቸው አደርግ ነበር፡፡ ተጫዋቾች ራሳቸውን ለከፍተኛ አካል ብቃታዊ ደረጃ በመድረስ ከቀላል ጉዳቶች ይጠበቃሉ፡፡

በጣም  ጥሩ የሚባል የፍጥነት ልምምድም አሰራ ነበር ፡፡ በተጫዋችነት ዘመኔ ካገኘኀቸው በተለይም  እ.ኤ.አ. ከ1970ዎቹ መጽሐፎች በአንዱ በእጅጉ እጠቀም ነበር፡፡ መጽሐፉ እስካሁንም በቤቴ ተቀምጦ ይገኛል፡፡

በእርግጥ ሙሉ በሙሉ በዚህ መንገድ ተጉዣለሁ ብዬ ባልደመድምም በሰራሁባቸው ክለቦች ውጤት ያመጣሁባቸውን ዘዴዎች እጠቀምባቸዋለሁ፡፡ በሴካፋ ዋንጫ ተጫዋቾቹ ቀድመው በክለቦቻቸው በ4-4-2 እና በ4-3-3 አሰላለፎች መጫወት የጀመሩ የነበሩ ቢሆንም የመጀመሪያ ምርጫዬ በሆነው 3-5-2ን ተጠቅሜ ዋንጫ አምጥቻለሁ፡፡ ዋናው ነጥብ በሁኔታዎች ላይ በመመስረት ተገቢ ውሳኔ ማሳረፍ መቻል ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን አሰልጣኞች በቂ እንቅልፍ የሚተኙ ይመስለኛል፡፡ በፊት እኛ ወደቅን፤ ተነሳን በማለት እየተጨነቅን የምንተኛው የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነበር፡፡

የአሰልጣኝነት ትምህርቶችን በተመለከተ የ Basic፣ የ Intermediate እና Advanced ኮርሶችን የወሰድኩት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ High Level ኮርስን ደግሞ በዩጋንዳ ተከታትያለሁ፡፡ በሰር ቦቢ ቻርተን አማካኝነት የተሰጠውን ይህን የ15 ቀናት ኮርስ በካምፓላ ወስጃለሁ፡፡ በስፖርት ኮሚሽን እና በእግርኳስ ፌዴሬሽን የተሰጠ ሌላ የስድስት ወራት ኮርስ ደግሞ በጃንሜዳ ወስጃለሁ፡፡ በተከታተልኳቸው ኮርሶች በሰበሰብኳቸው ወረቀቶች ብቻ መስራት በቂ እንዳልሆነ ስለምገነዘብ ራሴን በልምድና በንባብ አሻሽያለሁ፡፡ ብዙውን ጊዜ ለቫኬሽኖች ወደ ውጪ ስወጣም የምገዛቸውን መፃህፍትና ፊልሞችን እጠቀማለሁ፡፡


ወደ ቀደመው ዘመን ተመልሰን በእግርኳሱ በይበልጥ የሚተገበረውን ፎርሜሽን እንመልከት? ብዙዎች የአሰልጣኞቻችን አቀራረብ በአመዛኙ ተመሳሳይ ነበር ይላሉ. . .

በቀደመው እግርኳሳችን በቡድኖች ሁሉ ተመራጭ የነበረው ፎርሜሽን 3-5-2 ነበር፡፡ ፎርሜሽኑ ለመከላከልም ለማጥቃትም በሚሳተፉት  የመስመር ተጫዋቾች (አሁን ዊንግ ባክ የሚባሉት) ጫና ለመፍጠር አመቺ ነበር፡፡ እኔም የምጫወተው እና ውጤት የማመጣው በዚሁ ቅርጽ ነበር፡፡ በዚህ ሲስተም የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ (አጥቂዎቹ) በመከላከሉ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ በተለይ የተጋጣሚን የማጥቃት የጨዋታ ሒደት ከኋላ እንዳይጀመር በማድረግ ወይም በማዘግየት ስራ ላይ እንዲሳተፉ ያስችላል፡፡ 3-5-2 ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ መተግበር የጀመረው በጀርመናዊው አሰልጣኝ ፒተር ሸንግተር አማካኝነት በ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ወቅት ነበር፡፡ ይህን የአጨዋወት መንገድ በብሔራዊ ቡድን ተጫዋችነት ዘመናችን ሸንግተር ቴምፕሌት አድርጎ ሰጥቶን ነበር፡፡ እኔም በተጫዋችነት ጊዜዬ ያገኘሁትን እና ፋይል አድርጌ ያስቀመጥኩትን  ይህን ቴምፕሌት ነበር በማሰለጥንበት ወቅት የምጠቀመው፡፡


የፎርሜሽኑ የተለያዩ ንዑሳን ውልድ አደራደሮች (ለምሳሌ 3-4-1-2፣ 5-3-2፣ 3-1-4-2 . . .) ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር? ከፎርሜሽኑ ጋር የተገናኘው የተጫዋቾች የሚና ትግበራስ ምን ይመስል ነበር?                                                                     

ለሲስተሙ ትግበራ የሚሆኑ ተጫዋቾች በቡድኔ ውስጥ ነበሩ፡፡ በሁሉም የሜዳው ክፍሎች የሚገኙት ተጫዋቾቼ ለ3-5-2 የተጫዋቾች አሰላለፍ አመቺ ነበሩ፡፡ በሌሎቹ ክለቦች የነበሩት ተጫዋቾች እና ለሲስተሙ አመቺ የመሆናቸውን ነገር እርግጠኛ አልነበርኩም፡፡ ለረጅም ጊዜ ይህን ፎርሜሽን ስጠቀም በፊተኛው መስመር ላይ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ተጠቅሜያለሁ፡፡ ገ/መድህን ኃይሌ፣ ሙሉጌታ ከበደ፣ አሸናፊ ሲሳይ፣ ሰለሞን ዮሃንስ (ቸርኬ) እና ሌሎችም ነበሩኝ፡፡ ከሁሉም ግን ከሪም የሚባለው የመስመር ተጫዋቼ የነበረው የአካል ብቃት እና ፍጥነት ያስገርመኛል፡፡ መቶ ሜትሩን በፍጥነት ሮጦ በፍጥነት ሲመለስ የሚያስገርም ብቃት ያሳይ ነበር፡፡ ከፍተኛ ጉልበትንና ፍጥነትን ከመያዙም በላይ ጎሎችን የማስቆጠር ችሎታውም  ልዩ ነበር፡፡

በአሰልጣኝነት ስራዬ ለምጠቀመው የአጨዋወት ሲስተም ተጫዋቾችን የመመልመል ቅድመ ተግባር አከናውናለሁ ፡፡ በሌሎች ቡድኖች ለሲስተሙ ብቁ የሆኑ  ተጫዋቾችን የማግኘት እና የመጠቀም ችግር እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ለምሳሌ በሐጎስ ደስታ አየር ኃይል ውስጥ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ቢኖሩም ለጥንካሬያቸው አክሻፊ መንገድ በማበጀት ሁሌም አሸንፌያቸው እወጣ ነበር፡፡

በተጫዋቾች አጠቃቀም ረገድ ደግሞ መጀመሪያ የማየው የተጫዋቹን የአካል ብቃት ሁኔታ ነው፡፡ በጨዋታ ወቅት መድከም  አለመድከሙ እና ወቅታዊ ብቃቱ እንጂ ቀድሞ የነበረው ችሎታ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ስለዚህም በተመሳሳይ ሲስተም እየተጠቀምክ አሸናፊ እንድትሆን እና በሌሎች ላይ ከፍተኛ ብልጫ እንድትወስድ የሚያግዙህ ነገሮች በተጫዋቾች ችሎታ ላይ የተመረኮዘ የቦታ አሰጣጥ እና የተጫዋቾች ተገቢ የሚና አተገባበር እንዲሁም ጠንካራ የአካል ብቃት ናቸው፡፡


ቀደምት አሰልጣኞች እግርኳሳዊ በሆኑ ጉዳዮች ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ውይይቶች የማታደርጉበት ሒደት እግርኳሱን ምን ያህል ጎድቶታል ይላሉ?

በዚህ ጉዳይ እንኳን የታደልን አይደለንም፡፡ አብዛኞቻችን እርስ በእርሳችን ስንወቃቀስ ነው የኖርነው፡፡ የምንቀራረብና ጓደኛሞች የሆንን አሰልጣኞች እንነጋገራለን፡፡ እኔ፣ ስዩም አባተ እና ካሳሁን ተካ ጓደኛማቾች ነበርን፡፡ ስንገናኝ እናወራለን፤ እንተቻቻለንም፡፡ እኔም ስዩምም የየራሳችን አካሄድና ፍልስፍና ነበረን፡፡ ስዩምን ‘ሁለታችንም በምናምንበት መንገድ እንሂድ፤ ስታሸንፈኝ ያንተን ሀሳብ እቀበላለሁ፡፡’ እለዋለሁ፡፡ በውጤታማነት መንገዶቻችን ላይ እንከራከር ነበር፡፡ በአደባባይ ወጥቶ ለውይይት እና ለመፍትሔነት የቀረበ ሀሳብ ግን አልነበረም፡፡ የዚህን ችግር መንስዔ ወደ ውስጥ ጠልቀን ካየን አሰልጣኞች እርስ በእርስ እንዲቀራረቡ የማይፈልጉ ሰዎች ነበሩ፡፡ በተለይም የሚድያ አካላት፡፡ የግድ እንድንራራቅ ይደረግ ነበር፡፡ ከስዩም ጋር ለረጅም ጊዜ በተጫዋችነት ስላሳለፍን በደንብ እንተዋወቃለን፡፡ ተተቻችተንም ቂም አንያያዝም፤ መልሰን እንገናኛለን፡፡ እርስ በእርሳችን እንማማራለን፡፡ ነገር ግን በማህበር ደረጃ ስለ እግር ኳስ ውይይቶችን የምናካሂድበት መድረክ አልፈጠርንም፡፡ አሰልጣኞች በርከት ብለን የምንገናኘው ኮርስ ሲኖር ብቻ ነበር፡፡ ለኮርሱ ሲባል በአስተማሪው አማካኝነት በሚሰጡ የመወያያ ርዕሶች ላይ ከምንነጋገረው ውጪ ብዙም አናወራም፡፡ በዚህም ሳቢያ አገራዊ ፋይዳ ባለው የአሰልጣኞች ውይይት ላይ የመገናኘት እድል አልገጠመንም፡፡


በጊዜው ተፎካካሪ የነበሩ ትልልቅ አሰልጣኞችን የተለየ ጠንካራ ጎን ምን ምን ነበሩ

ውጤትን በማየት ግምገማን የማደርግ ሰው በመሆኔ በዚህ በኩል ዝርዝሮችን ለማቅረብ እቸገራለው፡፡ ውጤት የአሰልጣኞችን ስራ ለመለካት ዋነኛው መስፈርት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ እውቀት ሊኖርህ ይችላል፡፡ ያለ ውጤት ከሆነ ግን ፍሬ አልባና ትርጉም የለሽ ነው የሚሆነው፡፡ በእርግጥ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን በማፍራት እና ጠንካራ ቡድን በመገንባት ስዩም አባተን እጠቅሳለሁ፡፡ ስዩም በጣም ጎበዝ አሰልጣኝ ነው፡፡ በእኔ ዘመን ታክቲካዊ በሆኑ ጉዳዮች የተለየ ቡድን ሰርቷል፡፡ ጥሩ ተፎካካሪዬ ነበር፤ ሆኖም አሸንፌዋለሁ፡፡ ሐጎስም አስቸጋሪ ተጋጣሚን ያዘጋጅ ነበር፡፡ በተለይ በአካል ብቃቱ ረገድ ጠንካራ ቡድን ሰርቶ ይፈትነኝ ነበር፡፡ አየር ኃይሎችን የማሸንፈው በጠባብ ውጤት 1-0 ወይም 2-1 ነበር፡፡ ካሳሁን ተካና መንግስቱ ወርቁም ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በእኛ ጊዜ የነበሩት አሰልጣኞች ብርቅዬ እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከእኛ በኋላ በመጡት አሰልጣኞች ላይ ግን ብዙም የሚጠቀስ ነገር አላይም፡፡


 

በኢትዮጵያ እግርኳስ ለዘመናት ‹‹ሁለት የስልጠና መንገድ ›› ጎራዎች ይነሳሉ፡፡ የአስራት ኃይሌ ‹‹በአካል ብቃት ላይ የሚያተኩረው››  እና የስዩም አባተ ‹‹ኳስን መሰረት ያደረገው ›› ሲባል እንሰማለን. . .

አዎ ይባል ነበር፡፡ የአካል ብቃት ስራን በኳስና ያለ ኳስ ይሰራ ነበር፡፡ እኔ ሁለቱንም መንገዶች እጠቀማለሁ፡፡ ስዩም ደግሞ የበለጠ ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኩር ነበር፡፡ እሱ በአጫጭር ቅብብሎችና በኳስ ቁጥጥር ላይ ሲሰራ እኔ ደግሞ የኳስ ቅብብሎች በፍጥነት ወደተጋጣሚ የጎል ክልል የሚደርሱበት ስራዎችን አሰራ ነበር፡፡ ጎሎች ዋነኛ ዉጤት ማስገኛ በመሆናቸው ቅብብሎች ከግብ ጠባቂው ተነስተው ወደ አማካይ ክፍሉ፣ ከአማካዩ ወደ አጥቂው መስመር በስንት ቅብብሎች መድረስ አለባቸው? የሚለው ላይ አተኩራለው፡፡ በሁለትና ሶስት ንክኪዎች ከተከላካዩ ወደ አማካዩ፣ አማካዩ ደግሞ የተጋጣሚን ተከላካይ የማስከፈት አላማ ያላቸው ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች (Through-Balls) አልያም በአጫጭር አንድ-ሁለት ቅብብሎች (Double-Passes) ያለቁላቸው ኳሶችን ለአጥቂው ክፍል እንዲደርስ እፈልጋለው፡፡ እንደ ተጋጣሚ የመከላከል አደረጃጀት እና ሁኔታ በአማካይ ክፍሉና በአጥቂ ክፍሉ መካከል የሚደረጉት ቅብብሎች ሊያንሱም ሊበዙም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ የተጋጣሚ ቡድን በእኔ የሜዳ ክልል ወስጥ የሚገኝ ከሆነና ፈጣን አጥቂዎችን ካሰለፍኩኝ ግብ ጠባቂዬ የመልሶ ማጥቃቱን በፍጥነት እንዲያስጀምር ‘የመጀመሪያ ኳስ (First Ball) ተጫወት፡፡’ ብዬ አዘዋለሁ፡፡ ብዙ ጨዋታዎች ላይ በዚህ ዘዴ ጎሎችን አግኝተናል፡፡ ድምፄ ሃይለኛ በመሆኑ የጨዋታውን ሒደት በማንበብ እንዲህ አይነት ሽግግሮችን በቶሎ እንዲጀምሩ እመራለሁ፡፡ የእኔ እምነት ጎሎችን በፍጥነት አስስቆጥረህ ኳስን የመቆጣጠርና የጨዋታ ብልጫን ማስከተል ነው፡፡


በአሰልጣኝነት ስራዎ በመርህ ደረጃ የትኛን መስፈርት ያስቀድማሉ?

በመጀመሪያ በዲሲፕሊን አምናለው፡፡ በአሰልጣኝነት ስራዬ ቅድሚያ የምሰጠው ለስነምግባር ነው፡፡ በስነስርዓት የታነፀ ተጫዋች ማሰልጠን ለአሰልጣኙ ስራን ያቀልለታል፡፡

 


የእናንተ እና ከእናንተ ቀደም ብለው የነበሩ አንጋፋ አሰልጣኞች በተጫዋችቻቸው ዘንድ በእጅጉ የሚከበሩበትና የሚፈሩበት ምስጢር ምንድን ነው?

ይህ ቤተሰብን በአግባቡ ከመምራት የሚገኝ ክህሎት ነው፡፡ ቤተሰብ ውስጥ ልጆችን በማሳደግ ሒደት ሁሉንም እኩል በማየት የምትመራበትን መንገድ ነው በስልጠና ውስጥ የምታመጣው፡፡ በትክክለኛው ስርዓት እንዲቀራረቡና እንዲከባበሩ ማድረግ ይኖርብሀል፡፡ ሁሉም ተጫዋቾችህ በግልጽነት ሐሳብ የመስጠት መብታቸውን ማክበርም አለብህ፡፡ በልምምድ ወቅትም ሁሉንም  ተጫዋቾች በእኩል አይን ነው የምመለከተው፡፡ ስቆጣም ሆነ ሳወድስ ልዩነት አላደርግም፡፡ በእኔ አመለካከት በእግር ኳስ አስተዳደር ተጫዋቾች ወደ አሰልጣኙ መንገድ እንዲመጡ እንጂ አሰልጣኙ ወደ ተጫዋቾቹ መንገድ እንዲሄድ አልመክርም ፡፡ ተጫዋቾቼ ስርዓት ያላቸው እንዲሆኑ እኔ ራሴ ስርዓት ያለው ሰው መሆን አለብኝ፡፡ በአሰልጣኝነት ዘመኔ እንደማስተማሪያ እንዲሆን ብዬም ተጫዋቾች ሲያጠፉም በሌሎች ፊት የመቆጣትና የመገሰጽ ልማድ ነበረኝ፡፡ በይሉኝታ የእገሌ ሞራል ይነካል ብዬ የማስብ ሰው አይደለሁም፡፡ ወቀሳውንም ሙገሳውንም ፊትለፊት እናገራለው፡፡ እግርኳስ የአደባባይ ስፖርት ነው፡፡ ስህተቶችን በግልጽነት ስትናገር ሌሎች እንዲማሩበት በማድረግ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሁሉንም የስህተት ምክንያቶች በተገቢው ሁኔታ መዘርዘር አለብህ፡፡ ፊት ለፊት መናገር፣ ፊት ለፊት መቆጣት፣ ፊት ለፊት ማረም እና ማሻሻል እንዲሁም ማስተማር ይኖርብሀል፡፡ ተጫዋቾች ከዚህ ያለፈ የስርዓት ችግር የሚያሳዩ ከሆነ ወደ ማባረር አልያም መቀነስ ታመራለህ፡፡ አሰልጣኞች የአስተዳደር አካሄዳቸው ራሳቸውን እንዲያስከብሩ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

ተጫዋቾችን የምትቀርብበት እና የምትይዝበት መንገድ ክብር የምታገኝበትን ሁኔታ ይወስነዋል፡፡ እኔ ተጫዋቾቼን የምቀርባቸው እንደ አስተማሪ፣ አባት እና ታላቅ ወንድም ነው፡፡ ተጫዋቾቼን ስርዓት እንዲይዙ ለማድረግ እስከ መማታት የሚደርስ ቅጣት አደርግባቸዋለው፡፡ ግብ ግብ ለመፍጠር የሚሞክር ካለም ምንም ችግር አልነበረብኝም፡፡ እንደ አሁኑ አልምሰልህ፤ ያን ጊዜ አቅሙ ነበረኝ፡፡ ተጫዋቾቼም ይህን ይረዱታል፡፡ የእግር ኳስ ተጫዋችነት ህይወቴ በእንደዚህ ያለ የስርዓት መስመር ውስጥ ያለፈ ነው፡፡ ምንም የምፈራው ነገር የለም፡፡ በማሰለጥንበት ወቅት ከተጫዋቾቹ ያልተናነሰ ጉልበት እንደነበረኝ ሁሉም ያውቃሉ፡፡ ስርዓት ለማስፈን የሚያስፈልጉ ማናቸውንም ዕርምጃዎች ለመውሰድ ዝግጁ ነበርኩ፡፡ በእርግጥ የአሰልጣኝነት ስራዬ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የፈጠረብኝ ተጫዋች አልገጠመኝም፡፡ ሰዓት ከማክበር ጋር በተያያዘም በየትኛውም ቦታ እኔ ከመድረሴ በፊት ተጫዋቾቼ ቀድመውኝ ይደርሳሉ፡፡ በልምምድ ወቅት ሜዳ ውስጥ ሆነ በመኪና ላይ እነርሱ በቶሎ ይገኛሉ፡፡ እኔ አብሬያቸው በምሆንበት ጊዜ ቧልት ነክ ነገሮች አያሰሙም፡፡ እንዲያውም አንዳንዴ ቀልድ ፍጠሩ እንጂ እላቸዋለው፡፡ ነፃነት እንዲሰማቸው ለማድረግም አልፎ አልፎ እኔ ሳልኖር ለብቻቸው እንዲሆኑ እፈቅዳለው፡፡

ለኮሚቴዎች ተጫዋቾቼን አሳልፌ አልሰጥም፡፡ የትኛውም አይነት የንግግር ግንኙነትም ይሁን የቅጣት ጉዳይ እኔ ሳላውቅ እና ሳላምንበት እንዲወሰን አላደርግም፡፡ የተጫዋቾችን ጉዳይ ሐላፊነት በመውሰድ ራሴው እወጣዋለው፡፡ የአስተዳደር ሰዎችም በጣልቃ ገብነት የተጫዋቾቼን ስነ-ልቦናና ሞራል እንዲጎዱ አልፈቅድም፡፡ በዚህ አካሄዴ ነው የተጫዋቾችን አክብሮት የማገኘው፡፡


የተጫዋቾች አያያዝ ስርዓትን በተመለከተ የሚከተሉት ከየዘመኑ አካሄድ ጋር ተለዋዋጭ የማስተዳደር መንገድን ነው ወይስ ከሁኔታዎች ጋር የማይቀያየረውን ?

እኔ በእግር ኳስ ጊዜ የሚያመጣውን ለውጥ ባምንበትም በስነ-ምግባር ጉዳይ ግን በዘመን የሚቀየር አመለካከት የለኝም፡፡ ሁሌም ውጤታማ ሲያደርገኝ የኖረው የስነምግባር ጥብቅ አስከባሪነቴ ነው፡፡ እስከዛሬም ድረስ የሚያስከብረኝ እና ጥሩ ስም ያስገኘልኝ በዲሲፕሊን ላይ ያለኝ አቋምና ቋሚ የሆነ ፍልስፍናዬ ነው፡፡ በጊዜ ሒደት ከዚህ አቋሜ ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም፡፡ በቅርብ ጊዜው የአሰልጣኝነት ስራዬም ቢሆን ስነ-ስርአትን በማስከበር ረገድ ያሳየሁት አቋም ቀድሞ ከነበረኝ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ በደደቢት ያደረኩትም ይህንን ነው፡፡ በቡድኑ ትልቁ ተጫዋች ጌታነህ ከበደ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ከልምምድ ላይ ያለ እኔ ፈቃድ በመውጣቱ አባርሬው ነበር፡፡ ጎንደር ከፋሲል ጋር ለነበረብን ጨዋታም እንዳይሄድ አግጄው ቤቴ ድረስ በመምጣት ይቅርታ ጠይቆኝ እርቅ አውርደናል፡፡ በእርግጥ አልፎ አልፎ ከእኔ ፍላጎት ውጪ በሆነ ሁኔታ የስነምግባር ግድፈቶች ይታዩ ነበር፡፡ በእኔ አካሄድ ከገባሁበት ሌላ ውዝግብ እንዳይፈጥር በማሠብ ያለፍኳቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ቡድኑን ጥሩ ደረጃ ላይ ስላደረስኩም የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ጀመረ፡፡ በሒደት እኔንም የጤና እክል ገጠመኝ፡፡ ቡድኑን ስረከብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር፡፡ ያንን ለማስተካከል ከአቅም በላይ መስራት ተጠበቀብኝ፡፡ በከፍተኛ ጥረት ችግሮችን በማስወገድ ጥሩ እና ስርዓት የነበረው ቡድን ሰራው፡፡ መጀመሪያም የክለቡ አመራሮች በስራዬ ጣልቃ እንደማይይገቡ በመነጋገር ነው ስራውን የጀመርኩት፡፡ በእግር ኳስ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት  ለስርዓት ተገዢ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና የአስተዳደር ሰዎች በሙሉ የስራን ህግና ደንብ ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡ ከደደቢት የለቀኩት ከእኔ የአመራር ፍላጎት ጋር የተስማማ ሁኔታ በክለቡ እንዳልነበር በማስረዳት መታረም ያለባቸው ነገሮች ላይ ተነጋግሬ ነው፡፡ ክለቡን ስለቅ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበረው የጎል ልዩነት እንጂ የነጥብ አልነበረም፡፡ እኔ በቡድኑ እስከ መጨረሻው ብዘልቅ ኖሮ ክለቡን ቻምፒዮን አደርገው ነበር፡፡ አምስት ጨዋታ እየቀረ ነው ከክለቡ ጋር የተለያየሁት፡፡ ዋጋዬን እንዲረዱኝ ብዬ ነው በስምምነት የወጣሁት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *