የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን የአሰልጣኝ ጉልላት ፍርዴን ቃለ መጠይቅ ሁለተኛ ክፍል ይዘን ቀርበናል
ጉልላት ፍርዴ በተጫዋችነት ዘመናቸው ፔፕሲን ለቀው በ1980 ወደ ኤሌክትሪክ ካመሩ በኋላ ለሁለት አስርት ዓመታት በለክቡ ተጫዋችነት እና አሰልጣኝነት ቆይተዋል። በብዙዎች የሚታወሰው የ1993ቱ የሊግ እና ጥሎማለፍ አሸናፊ ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ የነበሩ ሲሆን በቀጣይ ዓመታትም ተፎካካሪ አድርገውት ቆይተዋል።
በዛሬው የመጀመርያ ክፍል መሰናዷችን ስለ ኤሌክትሪክ ስኬታማ ዘመናት አውግተናል። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ፤ ከኤሌክትሪክ ይልቅም በአሰልጣኙ የስራ ዘመን የነበረው ስያሜ ” መብራት ኃይል” ተጠቅመናል።
የመጀመርያውን ክፍል ለማግኘት ይህን ይጫኑ /LINK/
በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም
የአሰልጣኝነት ሙያን እንዴት ጀመርክ?
★ እግርኳስ ማሰልጠን የጀመርኩት በ1990 ዓ.ም. በመብራት ኃይል ክለብ የአሰልጣኝ ሐጎስ ደስታ ረዳት በመሆን ነበር፡፡ በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ከጋሽ ሐጎስ ጋር በምክትልነት እየሰራሁ ሳለ በ1992 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ጋሽ ሐጎስ ህመሙ እየበረታበት በመሄዱ ከእርሱ በማገኘው ምክርና ድጋፍ ለ1993 ዓ.ም. የውድድር ዘመን ቡድኑን ሳዘጋጅ ቆይቼ ከታህሳስ ወር 1993 ዓ.ም. ጀምሮ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ተረክቤ መስራት ጀመርኩ፡፡ መብራት ኃይል በ1990 የውድድሩ ሻምፒዮን፣ በ1991 እና 1992 ሁለተኛ፣ በ1993 ደግሞ የሊጉና የጥሎ ማለፉ ባለድል ከመሆኑም በላይ የጸባይ ዋንጫ አሸናፊ፣ ኮከብ አሰልጣኝ ያስመረጠና እና በዮርዳኖስ አባይ አማካኝነትም ኮከብ ግብ አስቆጣሪን ያስገኘ ቡድን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ይሄን መሰል ታሪክ የሰራ ቡድን ያለ አይመስለኝም፤ ሪከርድ እንደሆነም አስባለሁ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ወቅቶች በምክትልና በዋና አሰልጣኝነት ህይወት የመጀመሪያዎቹ አመታት ስኬታማ ጊዜዎቼን የሚያወሱ ናቸው፡፡ በወጣት ብሄራዊ ቡድንም የጋሽ ሰውነት ቢሻው ረዳት ሆኜ ከሃያ አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችን ይዘን የምድብ ማጣሪያውን በማለፍ በሲሸልስ የዙር ውድድር ጨዋታዎች አድርገን ተመልሰናል፡፡ ከዚያ በኋላም በኦሎምፒክና ወጣት ቡድኖች በረዳት አሰልጣኝነት ሰርቻለሁ፡፡ ከ1995 ዓ.ም. በኋላ በመብራት ኃይል ክለብ ውስጥ ለመጡት ሁለቱ የውጭ ዜጋ አሰልጣኞች ምክትል ሆኜም አገልግያለሁ፡፡ በጣልያንያዊው ፔትሬሊና በእንግሊዛዊው ኬን ሞርተን ስር ለሁለቱም አንድ- አንድ አመት በምክትል አሰልጣኝነት ሚናዬ ጥሩ ጥሩ ልምዶችን እየቀሰምኩ ደስ የሚል ጊዜ አሳልፌያለሁ፡፡ ፔትሬሊ ታክቲካዊ በሆኑ ልምምዶች ላይ የሚያተኩርና ብዙ የሚሰራ አሰልጣኝ በመሆኑ ብዙ እውቀቶችን እያገኘሁ ራሴን እንዳሻሽል አግዞኛል፡፡ ሞርተንም በእንግሊዝ ለማንችስተር ዩናይትድ ተጫውቶ ያሳለፈና የእንግሊዝ እግርኳስ አጨዋወት በሚታወቅበት ስልት በተለይ ደግሞ <ሁለት-ሁለት ሆኖ በክንፍ በኩል መጫወት>የሚለውን የልምምድ አይነት ያዘወትር ስለነበር ከእርሱም ብዙ ተምሬያለሁ፡፡ በወቅቱ በክለቡ ከስር-ከስር ወጣቶችን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ የሆነ ስራ በመሰራቱ ከክለቡ በየጊዜው ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች እየለቀቁብን እንኳ በምናሳድጋቸው ተጫዋቾች አማካኝነት ያለምንም ችግር የወጡትን እየተካን ጠንካራ ቡድን ገንብተናል ፡፡ ለምሳሌ አንዋር ያሲንና ዮርዲያኖስ አባይ ቡና ሄደውም እነሱን ስንገጥም በተተኪዎቹ ልጆች እናሸንፋቸው ነበር፡፡ ጊዮርጊሶችንም ቢሆን በጣሙን ፈትነናቸል፡፡ ጊዮርጊሶች ላይ አራት ግቦች ካስቆጠርንባቸው ከረጅም ጊዜ በኋላ ይመስለኛል፥ በቅርቡ አዋሳዎች አራት ጎሎች ያገቡባቸው፡፡ ጊዮርጊስ ላይ አራት ግብ ያስቆጠርነው አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁለቴ ነው፥ ያውም በጠንካራ ውድድር!!! ጊዮርጊሶች ጠንካራ ፉክክር ያደርጉና ይፈሩት የነበረው የእኛን ቡድን ነው፡፡ ቡናም ቢሆን እንደዚሁ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ መብራት ኃይል አነስተኛ ደረጃ ካላቸው ቡድኖች ጋር ሲጫወት በስነ ልቦናው በኩል ችግር ነበረበት፡፡ በጣም ትንንሽ በሚባሉ ምክንያት ነጥቦችን ይጥላል፡፡ በ2000 ዓ.ም ይህ አካሄድ ያልተመቻቸው የክለቡ ሐላፊዎች “ይሄ ቡድን እኮ ሻምፒዮን መሆን የሚችል ነው፤ “ለምን አራተኛ ደረጃ ያዝክ?”ብለው ከቡድኑ እንድወጣ ተደረገ፡፡ ከዚያ በኋላም ጋሽ አስራት ቡድኑን ተረከበና አንድ አመት ቆይቶ ሲለቅ ክለቡ በውጤት ማጣት እየተንሸራተተ ሄዶ-ሄዶ የመውረድ አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ በድርጅቱ ሰራተኛ ስለነበርኩ እንደገና
“ክለቡን ያዝ!” ተባልኩና ተመልሼ ኃላፊነቱን ተረከብኩና ቡድኑጅ ከመውረድ አተረፍኩት፡፡ እኔ ያልመሰለኝን ነገር አላደርግም፤ አጎብድጄ መኖርም አልችልም፤ የማይሆን ነገር ሳይም ‘አይሆንም’ እላለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ባህሪያቴ ደግሞ የበላይ ሰዎችንና አመራሮችን አያስደስታቸውም ነበር፡፡ “ክለቡ የተያዘበት መንገድና አደረጃጀቱ ጥሩ አይደለም፤ የተጫዋቾች ምርጫ ትክክለኛ አካሄድ አይታይበትም፡፡” በማለት የሰጡሁት ሀሳብ ጥሩ አስተያየት እንዳልሆነ ተደርጎ በመታየቱ ለሁለተኛ ጊዜ ከመብራት ኃይል እንድሰናበት ምክንያት ሆነ፡፡ እንግዲህ ቡድኑም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይኸው አሁንም ድረስ ላለመውረድ መጫወቱን ተያይዞታል፡፡ ከአስር አመት በፊት የነበረውን መብራት ኃይልና አሁን ያለውን ስናነጻጽረው ልዩነቱ እጅጉን ስሜት የሚነካ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ያን የመሰለ ቡድን በዚህ አቋም ላይ ተገኝቶ ሳየው እኔ ራሴ እጅግ በጣም አዝናለው፡፡ ክለቡ ምንም ያጣው ነገር የለም፥ ጥሩ የገንዘብ አቅም አለው፤ በተጫዋቾች አያያዝም ቢሆን የተሻለ የሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል፤…….ጥቃቅን ነገሮች ላይ መሻሻሎችን ቢያደርግ አሁንም ተፎካካሪ የመሆን አቅም እንዳለው ይሰማኛል፡፡
የአሰልጣኝነት ኮርሶችን በመውሰድ ነው ወደ ስልጠናው ሙያ የገባኸው?
★ የተጫዋችነት ጊዜዬ ሲያበቃ በመብራት ኃይል ድርጅት የስፖርት ጽ/ቤት ውስጥ የባለሙያ እጥረት ስለነበር በአጋጣሚ ለቢሮ ስራ ተመድቤ ስሰራ ከጋሽ ሐጎስ ጋር በእግርኳስ ዙሪያ ውይይቶችን እናደርግ ነበር፡፡ የምሰጣቸው አስተያየቶችና የነበሩኝ ሐሳቦች ተመችተውት ሳይሆን አይቀርም፥ የእርሱ ምክትል አሰልጣኝ ሲነሳ ለክለቡ አመራሮች ” ጉልላትን ረዳት አድርጉልኝ!” አላቸውና ወደ ሙያው አስገባኝ፡፡ ከዚያ በፊት የሁለተኛ ደረጃ የአሰልጣኝነት ኮርሶችን ወስጄ ስለነበር እግረ መንገዴን ስራውን መስራት ጀመርኩ፡፡
በምክትል አሰልጣኝነት ጅማሮ ወደዚህ ሙያ እንደገባህ ፈጣን በሆነ የጊዜ ሒደት የጋሽ ሐጎስ ደስታን ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ በአገሪቱ ትልልቅ ከሚባሉ ቡድኖች በአንዱ ዋና አሰልጣኝ ሆንክ፡፡ በጊዜው ወጣትና ከስመ ጥር አሰልጣኝ ስር ልምድ እየቀሰምክ የምትገኝ ስለነበርክ በሹመቱ ምክንያት ምን አይነት ስሜት አደረብህ? በምን መልኩስ ተቀበልከው?
★ በጊዜው የመብራት ኃይል እግርኳስ አስተዳደር ኮሚቴ አባላት ” አብሮህ እየሰራ የሚረዳህ ባለሙያ እናምጣልህ ወይስ አንተ መቀጠል ትችላለህ?” በማለት ጠይቀውኝ ነበር፡፡ ‘ ለትንሽ ጊዜ ቢሆንም በስልጠና ሙያ ውስጥ አልፌያለሁ፥ ስለዚህ ሐላፊነቱን መወጣት እችላለሁ፤ የምችለውንም ማሳየት እፈልጋለሁ፤ በወደፊት ቆይታዬም ውጤታማ የማልሆን ከሆነ በጊዜ እለቃለሁ፡፡ ስለዚህ ስራውን ለኔ ስጡኝና ካልቻልኩ እወጣለሁ፡፡’ አልኳቸው፡፡ ከዚያም እድሉ ተሰጠኝና ተሰካልኝ፡፡ በእርግጥ በነበርኩበት ሁኔታ በዚያ ሙያ ውስጥ መቀጠል አልፈልግም ነበር፡፡ አጋጣሚውን በማግኘት ዋና አሰልጣኝ ሆኜ በነበረኝ ልምድ ላይ ያለኝን እውቀት እያስማማሁ ያንን የመሰለ ቡድን ማንቀሳቀስ ባልችል ኖሮ አቅጣጫዬን ድሮ እቀይር ነበር፡፡ ባይሳካልኝ ደግሞ ወደ ሌላ ሙያ ውስጥ ነበር መግባት የሚኖርብኝ፡፡ አጋጣሚውን በአግባቡ ስለተጠቀምኩና ጥሩ ውጤት ስላገኘሁ እስካሁንም ድረስ በአሰልጣኝነት ስራው ልቀጥል ችያለሁ፡፡
የአሰልጣኝ ሐጎስ አስተዋፅኦስ ምን ያህል ነበር? በእርሳቸው ስር ለረጅም ጊዜ ከመስራትህ አንጻር በቶሎ ትልቅ ደረጃ ላይ እንድትደርስና ሁሌም ዝግጁ እንድትሆን በማገዝ ረገድ የነበራቸው አበርክቶ ምን ይመስላል?
★ ጋሽ ሐጎስ እጅግ በጣም ጎበዝና በሳል የነበረ አሰልጣኝ ነው፡፡ በሙያው ውስጥ በአንዳንድ ጉዳዮች ምክንያት መቼ መቆጣት እንዳለብህና በየትኛው ጊዜ እርጋታን እንደምታሳይ ያሳውቅሀል፡፡ እኔ በወቅቱ በሰላሳዎቹ የእድሜ ክልል የምገኝ ብሆንም ብዙም የወጣትነት ባህሪ የማላሳይና በተፈጥሮዬ የተረጋጋሁ ስለነበርኩ የጋሽ ሐጎስን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ እከታተል ነበር፡፡ የቡድን አመሰራረት ምን እንደሚመስል በማሳወቅ፣ በጨዋታ ወቅት ደግሞ ከኋላ የመከላከል አደረጃጀትንና በማጥቃት ሒደት ውስጥ የቡድን እንቅስቃሴዎች ወደፊት በምን መልኩ እንደሚደረጉ እያሳየኝ እኔም ስጫወት “ስህተት” ብዬ የማስባቸውን ነገሮች እያረምኩ እንድጓዝ ረድቶኛል፡፡
“የቀደሙት ዘመን ተጫዋቾች ከምክትልነት ተነስተው ወደ ዋና አሰልጣኝነት እድገት ለተሸጋገሩት ባለሙያዎች የሚሰጡት ክብር የተሻለ ነበር፡፡” እየተባለ ሲነገር ይሰማል፡፡
★ እኔ በዋና አሰልጣኝነት ስመረጥ ለተጫዋቾቹ የነገርኳቸው ” በየትኛውም አሰልጣኝ ስር ብትሆኑም ዋናው ነገር እናንተ ስራችሁን መስራታችሁን መቀጠላችሁ ነው፡፡ የሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በመስማማት፣ የማይሆኑ ነገሮች ሲታዩ ደግሞ ግልጽ በሆነ መንገድ ተቃውሞን ማሰማት ይቻላል፡፡” በክለቡ በቋሚነት ለመሰለፍ የሚያስችል ብቃት ያለውን ቅድሚያ በመስጠት ውድድሮችን ማድረግ ከቻልክ ማንም ሊቃወምህ የሚችል አይመስለኝም፡፡ ምናልባት ዘወትር የመሰለፍ እድሉን የማያገኙ ተጫዋቾች ሊቃወሙህ ይችላሉ፡፡ ግን ደግሞ ተቃውሞ ምክንያታዊ መሰረት ሊኖረው ይገባል፡፡ አንድ ተጫዋች ችሎታውና አቅሙ ከሌለው ማመን አለበት፡፡ እኔ በተፈጥሮዬ ማዳላት አልወድም፤ በትውውቅና በዝምድና መስራት ስለማይመቸኝም ማንም ተጫዋች ስለ ራሱ ባለው ግምትና በወቅታዊው ብቃቱ መሀል ስላለው ልዩነት እንዲያምን ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡ ዋሽቼ ተጫዋቾችን መቅረብ አልፈልግም፡፡ በየትኛውም ቦታና በምትሰራው ስራ ችግር ሊፈጠር ይችላል፤ የመጣውን ደግሞ መቀበል ግዴታ ነው፡፡ ከተጫዋቾቹ ጋር የምጣላበት ጊዜ አለ- ‘ስለምትበለጥ ነው፤ አትችልም፤ የሚጎድሉህ ነገሮች አሉ፤ ማስተካከል ያሉብህን ችግሮች ካስተካከልክ የመጀመሪያ ተሰላፊነት እድሉ ይሰጥሀል፡፡’ እላለሁ፡፡ እኛ አገር በእግርኳሱ ጥሩ የገንዘብ ዝውውር ስላለ ትልልቅ ተጫዋቾች ከዚህ አካባቢና ስራ መራቅ ስለማይፈልጉ ለወጣቶች ብዙ እድል ላይገኝ ይችላል፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች በወጣቶች የማይተኩ ከሆነ ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ሊያድግ አይችልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ቆፍጠንና ኮስተር ብሎ መልስ መስጠት የሚገባው ሰው መገኘት መቻል አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን እድሉን አግኝተው እየተጫወቱ የሚገኙ ተጫዋቾች የሚችሉትን ያህል እያደረጉና እየሰሩ ነው፡፡ ሲቆሙ ደግሞ መሰረት ኖሯቸው ከስር-ከስር በተሻለ የሚተኳቸው ታዳጊዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ በሁሉም ክለቦች ውስጥ ለወጣቶች ቦታ ለመስጠትና ለማሳደግ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ U15፣ U17፣ U19 እና U21 ሲባል ይሰማል፡፡ ስም ብቻ ምን ይሰራል? የተጫዋቾቹ የእድገት ሒደት ምን ይመስላል? እየወሰዱ ያሉት ስልጠናስ ምን አይነት ይዘት አለው? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ በቂ ምላሽ መገኘት አለበት፡፡ ደረጃው እየተጠበቀ ተጫዋቾቹ የሚያድጉበትን መንገድ መፈለግ አለብን፡፡ በእኛ ጊዜ መብራት ኃይል ከወጣት ቡድኖቹ ጥሩ የሆኑትን ተጫዋቾች በየአመቱ ያሳድግ ነበር፡፡ ሁሌም ከስር የሚተኩትን ብቁዎች እናዘጋጅ ስለነበር ትልልቅ ተጫዋቾች ሲለቁብን ብዙም አያሳስበንም ነበር፡፡ ታች ቡድን ውስጥ እንኳ አንድ ላቅ ያለ ችሎታ ያለው ታዳጊ ተጫዋች ስናገኝ ” ና! ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ ስራ፤ የቡድኑን አጨዋወት አስተውል፤ ከከባቢው ጋር ተላመድ፤ ከአንጋፋ ተጫዋቾች ልምድ ቅሰም!……..” እያልን እናበረታታቸዋለን፡፡ በዚህ አይነት ስልት እድል ይሰጣቸውና ትልቁን ቡድን ይቀላቀላሉ፡፡ በክለብ ስራ ውስጥ ሆነንም ለአገር ማሰብም ያለብን ይመስለኛል፡፡
ከአቶ ሐጎስ ደስታ ውጪ በረዳት አሰልጣኝነት ያገለገልካቸው ሌሎች አንጋፋ አሰልጣኞች እነማን ናቸው?
★ በታዳጊና ወጣት ብሔራዊ ቡድኖች ከጋሽ ሰውነት ቢሻው፣ አቶ ፀጋዬ ደስታና አሰልጣኝ ወንድማገኝ ከበደ ጋር ሰርቻለሁ፡፡
መብራት ኃይልን ለሁለተኛ ጊዜ አሰልጥነህ ከመውረድ ከታደግኸው በኋላ በድሬደዋ የነበረህ ግማሽ የውድድር ዘመን ቆይታ ብቻ ነበር፡፡ እዚያስ ያልሰነበትከው ለምን ይሆን?
★ በወቅቱ ድሬደዋም ላለመውረድ ትግል ሲያደርግ የነበረ ቡድን ነው፡፡ ክለቡን እንዳይወርድ ካስቻልኩ በኋላ ውሌን ስጨርስ ለቀቅሁ፡፡ በእርግጥ ክለቡ እኔ ከወጣሁ በኋላ በቀጣዩ አመት ከፕሪምየር ሊጉ ወርዷል፡፡ ስለዚህ በተከታታይ ሁለት አመታት ማለትም በ2002 እና በ2003 ዓ.ም ሁለት ቡድኖችን ወደ ታችኛው የሊግ እርከን እንዳይወርዱ አድርጌያለሁ ማለት ይቻላል፡፡
በ2006 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ ካደረከው የስድስት ወር የአሰልጣኝነት ስራ ቆይታ በኋላ ስምህ እምብዛም ከክለቦች ጋር ተያይዞ ሲነሳ አይሰማም፡፡ ከእግርኳሱ ሙያ ርቀሃል እንዴ?
★ በባህርዳር ከነማ የጥቂት ወራት ቆይታዬ በክለቡ ለረጅም ጊዜ የሚያቆይና የሚያስተማምን ከባቢ እንዳልነበር ስረዳና በቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ ስለኳሱ ብዙም እውቀቱ ያልነበራቸው ሰዎች ሊያሰሩን ስላልቻሉ ስራውን ትቼ ወጣሁ፡፡ ከእግርኳሱ አለም መለየት ስለሌለብኝም በአሁኑ ጊዜ በሰንሻይንና በንፋስ ስልክ አካባቢ በሚገኙ የግል የህጻናት ስልጠና ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
ክለቦችን ልትይዝ እንደሆነ በጭምጭምታ ደረጃ ይሰማና በመጨረሻ ግን አንተ ሳትመረጥ ትቀራለህ ፡፡ ራስን ካለማብቃት ጋር የሚያያዝ ነው?
★ እንዳላችሁት ብዙውን ጊዜ እንደዚህ አይነት ወሬዎች ይነገሩና ፍጻሜያቸው ሳይሰምር ይቀራል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ውስን ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ በተፈጥሮዬ ተጨባጭ ባልሆኑ ጉዳዮች ውስጥ ጥልቅ ብዬ በመግባት ሁኔታዎችን የማመቻመች ችሎታው የለኝም፡፡ ስለዚህ ይህንን ባህሪዬን ምንም ላደርገው አልችልም፡፡ በቀደሙት ጊዜያት “ካልሰጠህ አትገባም!” አይነት ተገቢ ያልሆኑ ነገሮች አልነበሩም፡፡ አሁን ግን < መቀባበል> የግድ ሆኗል፡፡ ይህ አይነቱ ሁኔታ ማንን እንደሚጠቅም አይገባኝም፡፡ ስራ አስኪያጅ የሆኑ ግለሰቦች በ< ቦታቸው> የሚኖራቸው ቆይታ ጊዜያዊ በመሆኑ ተጠቅመው ዞር ማለታቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ ብዙዎቹ “ወደ ቦታው በመጣንበት ጊዜ ተጠቅመን እንሂድ፡፡” የሚል አስተሳሰብ እንጂ የክለቦችንና የአገሪቷን እግርኳስ ለማሳደግና የተሻለ ደረጃ ላይ ለማድረስ ደንታ የላቸውም፡፡ የራስን ጥቅም የማስቀደምና የማስጠበቅ ፍላጎት በሚያይልበት ተለምዶአዊ አሰራር እግርኳሱን ማሻሻል በጣም ከባድ ይሆናል፡፡
ብዙውን ጊዜ ” ክለቦች ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ከመውረድ ለመትረፍ በጭንቀት ሰዓት የሚጓዙበትን አቋራጭ መንገድ እቃወማለሁ፡፡” ስትል ይሰማል፡፡ ያ < አቋራጭ መንገድ> የትኛው ይሆን? ችግሩን ዘርዘር ባለ መልኩ ግልጽ ብታደርገው…
★ ችግሩ ያለው አመራሮች ጋር ብቻ አይደለም፤ ፌዴሬሽኑና አሰልጣኞችም የችግሩ አካል ናቸው፡፡ ያላየሁትን ነገር “እንዲህ ነው!” ብዬ መናገር ስለሌለብኝ እንጂ ብዙ ነገር እንደሚደረግ ይሰማል፡፡ ያልሰራ ሰው እንዲሁ ዝም ብሎ ለጥቅማ ጥቅም ሲል ይቀመጣል፡፡አሰልጣኙ በራሱ የሚያወጣው ብዙ ነገር አለው፡፡ ማንም ሰው የሚችለውን ሰርቶ ቀሪው ካቅሙ በላይ ሲሆን መቆም ይኖርበታል፡፡ ከምትችለው በላይ ያለውን በገንዘብህ ገዝተህ የምታስተካክለው የዛሬውን ሊሆን ይችላል፡፡ ነገ ግን ያንን ነገር መልሰህ ማምጣት አትችልም፤ ያለ አንዳች ለውጥና መሻሻል የነበርክበት ቦታ ላይ ትቆማለህ፡፡ስለእውነት ለመናገር ተጫዋቾቻችንም በአዕምሮ መብሰል አለባቸው፡፡ በእንደዚህ አይነት ነገር ውስጥ ፍጹም ተሳትፎ ማድረግ የለባቸውም፡፡ ሙያቸውን ማክበርና ፕሮፌሽናል አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለሚከፈላቸው እንጂ አግባብ ባልሆነ መንገድ በጎን በኩል ለሚያገኙት ጥቅም መስራት የለባቸውም፡፡ የሚደረገው ነገር ቀልድ፣ ግፍና አጸያፊ ነው፡፡ አመቱን ሙሉ ሰርተህ የልፋትህን ውጤት ማግኘት ይገባሀል፡፡ በማጭበርበር፣ አለአግባብ ገንዘብ በመስጠትና በመቀበል የሚሰራው ስራ ያጸይፈኛል፡፡ ወደዚህኛው አስነዋሪ ድርጊት ላለመግባት የሚቻለውን ያህል ጥረት ማድረግ መቻል አለብን፡፡ እንደ አሰልጣኝ ቡድናችንን ለማነሳሳትና የተሻለ ውጤት ለማምጣት በምንችለው መጠን መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ አሰልጣኙ ብቻውን የሚያደርገው ሳይሆን ከክለብ አመራሮች ጋር በመተባበር ቡድኑ አንድነት፣ፍቅርና ሰላም ኖሮት ተጫዋቾች ያላቸውን በሙሉ አውጥተው እንዲሰጡና በጥሩ ብቃት እንዲጫወቱ ቢደረግ እንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ አይገባም፡፡ ስለዚህ መሰራት ያለበት በጊዜ ነው፡፡ በውሸት በሚደረግ ነገር እንዴት ነገ ዋስትና ሊኖረን ይችላል? ድርጊቱ አሳፋሪ መሆኑ ለማንኛውም ክለብ ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡ ማንም ሰው የልፋቱን ነው ማግኘት ያለበት፡፡ ከዚያ ውጪ ” ሰው ለመርዳት” በሚል የሚደረገው ነገር አግባብ አይደለም፡፡ መረዳት የሚገባው ብዙ ሰው ያለው ሌላ ቦታ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ እንጀራ የምንበላበትን ሙያ፣ ክለቦችንና የእግርኳስ ጨዋታን ለማየት የሚመጣ የስፖርት ቤተሰብን መናቅ፣ ወንጀልና ትክክለኛ ያልሆነ ነገር ነው፡፡
አሰልጣኞችና የሚያስመዘግቡት ውጤትን በተመለከተ ስላለው ልል የተጠያቂነት አሰራር ልምድ ምን የምትለው ይኖራል?
★ አንድ አሰልጣኝ አመቱን ሙሉ ላለመውረድ አጫውቶ ሲያበቃ ምንም የሚሆነው ነገር የለም፡፡ በቀጣዩ አመትም ሲቀጥል ይታያል፡፡ ማንም አሰልጣኝ ለሰራው ስራ መጠየቅ አለበት፡፡ ሐላፊነት ስትሰጠው ” ይህንን ቡድን ለዚህ ደረጃ አበቃዋለሁ!” ያለውን ካላደረገ የሚጠየቅበት ስርዓት መፈጠር አለበት፡፡ የተሻለ የሰራውም ሊወደስና ሊበረታታ ይገባል፡፡ አሰልጣኞች አንድን ክለብ ሲይዙ ቡድኑ በሜዳ ላይ የሚያሳየው የስነ-ምግባር ፣ አካል ብቃት፣ ቴክኒክ፣ ታክቲክና ስነ-ልቦና ደረጃ ለውድድሮች የተዘጋጀ ሆኖ ውጤት የሚያመጣበትን መንገድ ቀይሰው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ ከላይ ከተጠቀሱት የእግርኳስ መሰረታዊ መመዘኛዎች በአንዱም የሌለበት ከሆነ የአሰልጣኙ ህልውና ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ እነዚህን ሁሉ ስራዎች ሰርቶና ቡድኑን ቀርጾ የሚያወጣው አሰልጣኙ ነው፡፡ የእግርኳስ አሰልጣኞች በሜዳ ላይ ያለውን እንዳንዱን ጥቃቅን እንቅስቃሴ ሳይቀር መመልከት መቻል አለባቸው፡፡ በጨዋታ ወቅትም በሜዳው ሶስቱ ሲሶዎች ምን አይነት የጨዋታ ሒደቶች መከወን አለባቸው? የሚለውን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በጥልቅ ትንተና የተደገፉ ማብራሪያዎችን ለተጫዋቾቻቸው መስጠትም ተገቢ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የሚታየው ከቴክኒካል ሳጥኑ ጠርዝ የሚላክ ትዕዛዝ እኮ አስገራሚ ነው፡፡ ምንም የባላጋራ ተጫዋቾች በሌሉበት ቦታ ላይ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት እየተቻለ በአንዴ በረጅሙ ሲጠልዝ እያየ ተጫዋቹን ” ብራቮ!” እያለ የሚያበረታታ አሰልጣኝ ምን እያደረገ እንደሆነ ራሱን ሊጠይቅ ይገባዋል፡፡ እኔ እንዲህ አይነቱን የተጫዋቾች ጊዜንና ቦታን ያላገናዘበ ውሳኔ ሳይ በጣም እናደዳለሁ፡፡ በዚህ ዘመን እኮ < የተጠና ጨዋታ> ነው መጫወት ያለብን፡፡ ለጊዜያዊ ድልና ላለመውረድ መጫወትስ አስከመቼ ነው የሚያስጉዘን? በዘላቂነት ለአገር ጥቅም ሲባል መሰራትን እንልመድ፡፡
በአሰልጣኝነት ሙያህ ለየትኞቹ ተጫዋቾች ቅድሚያ ትሰጣለህ? ጉልበተኛና ወኔያም ባህሪ ላላቸው፣ ለብልሃተኞቹ ወይስ ከሁለቱም ለሆኑት?
★ ብዙውን ጊዜ ፍጥነትና ፍላጎት ኖሮት እየሰራ ኳስ የሚችል ተጫዋች ያስደስተኛል፡፡ ተጫዋች ሙልት ያለ ሲሆን ምርጫዬ ነው፡፡ ሩጫው ላይ ብቻ ጥሩ ሆኖ በቴክኒኩ ባዶ ከሆነ ልፋቱ ከንቱ ይሆናል፡፡ በእርግጥ በሒደት እያረምክና እያስተካከልክ ልታሻሽለው የምትችለው ተጫዋች ይኖራል፤ ሆኖም እኔ ቴክኒካዊ ችሎታን ቅድሚያ ስለምሰጥ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ አስቦና አቅዶ የሚከውን ተጫዋች ይመቸኛል፡፡ የተጋጣሚ ተጫዋች ሲመጣበት በጉልበትና ፍጥነት መቀማት የሚችለው ተጫዋች ኳሱን ከነጠቀ በኋላ ለማንና የት እንደሚሰጥ ወይም እንደሚያቀብል ካላወቀ ምን ያደርጋል? በእርግጥ መንጠቅ አንድ ችሎታ ነው፤ ለቡድን አጋሮች በትክክል ማቀበልም ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱንም ያሟላ ሳገኝ ደስ ይለኛል፡፡
የተለመደና አሰልጣኞች በሚመርጧቸው ተጫዋቾች የክህሎት ዘርፍ ጎራ ስለሚለዩ ያንተ የትኛው ምድብ ውስጥ እንዳለህ ለማወቅ ነው…
★ እኔ በቴክኒክ አምናለሁ፡፡
እንደነ ተክሌ ብርሐኔ፣ ኃይሉ አድማሱ፣ አለማየሁ ዲሳሳና ሌሎቹ የዚህ ዘርፍ ባለሟል የሆኑ ተጫዋቾች በቡድንህ ውስጥ መኖራቸው ተጽዕኖ ፈጥሮብህ ይሆን?
★ እንዴታ! አሁንም ቢሆን ተጫዋቾችን አሰባስብ ብባል ቴክኒካል ችሎታ ላላቸው ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ በቴክኒክ የተሻለ ብቃት ያላቸው ተጫዋቾች በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ከየት ተነስተው ወደ የት እንደሚሄዱ ያውቁታል፤ እነሱን ከያዝክ ቀጣይ የማዋሀድና አመቺ ሲስተም የመፍጠር ስራ የሚሆነው የአሰልጣኙ ነው፡፡ ምርጥ ምርጥ ተጫዋቾች ስለተሰበሰቡ ብቻም ቡድን አይሰራም፡፡ ወደ ፊት የሚኬድበትን፣ ክፍት ቦታዎች የሚዘጉበትን፣ ወደኋላ ማፈግፈግ የሚያስፈልግበትንና ተጫዋቾች ለቡድን አጋሮቻቸው ቅብብሎችን ፈጽመው በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሚንቀሳቀሱ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን እየታየ ባለው ሒደት አንድ ተጫዋች ኳስ ለአንተ ይሰጥህና መልሶ ወዳንተ ይሮጣል፡፡ ስልጠናው ተቀይሮ ከሆነ አላውቅም! የትኛውም ተጫዋች ኳስን ለጓደኛው ካቀበለ በኋላ መሄድ የሚገባው በሜዳው ቁመት ወደሚገኝ ክፍት ቦታ ነው፡፡ እኛ አገር የተለመደው ግን ኳስ ትሰጠዋለህ፤ቀጥሎ ከኋላህ ይከተልህና ” ስጠኝ!” ይልሀል፡፡ ከዚያም ወደ ኋላና ወደ ጎን ስትመልስ ቅብብሎች በሙሉ በዚህ መልኩ መሆን ይጀምራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የፊትለፊት እንቅስቃሴ Rarely የሚታይ ይሆናል፡፡ ስልጠናውም እኮ “ወደ ፊት አቀብል፤ ወደፊትም ሩጥ!” ነው የሚለው፡፡