በዝነኛው እንግሊዛዊ የእግርኳስ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና በእግርኳስ ታክቲክ ዝግመታዊ የሒደት ለውጦች ላይ የሚያተኩረው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የተሰኘውን መጽሃፍ በትርጉም እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። በዛሬው መሰናዶም የምዕራፍ አንድ ሶስተኛ ክፍልን እነሆ ብለናል፡፡ መልካም ንባብ!
|| የመፅሀፉን ክፍል ሁለት ለማንበብ ይህን ይጫኑ | ምዕራፍ አንድ- ክፍል ሁለት |
ኩዊንስ ፓርኮች ተግባራዊ ያደረጉት እና በተጫዋቾች አመርቂ የሜዳ ውህደት የተቃኘው አጨዋወት ስልት ያመጣው አንጻራዊ ስኬት ቢያንስ በሃገሪቱ ሰሜናዊ ጠረፋማ አካባቢዎች ” በአጭር ርቀት የሚደረጉ ቅብብሎች ላይ የተመሰረተው አቀራረብ ከድሪብሊንግ ጨዋታ የላቀ ነው፡፡” የሚል አስተሳሰብ እንዲሰፍን አደረገ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ አይነቱ ዘይቤ ቀደም ሲል በስኮትላንድ የጨዋታው አካል ባይሆን ኖሮ በኩዊንስ ፓርክም ትኩረት ተሰጥቶት የማደግ እድል አያገኝም ነበር፡፡ ክለቡ በ1867 በተመሰረበት ወቅት ” ከተጋጣሚ የመጨረሻ ተከላካይ ጀርባ የተገኘ እና በሜዳው ቁመት የባላጋራ ቡድን 13.7 ሜትር ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀስ ተጫዋች የጨዋታ ውጭ> ስምምነትን ጥሷል፡፡” የሚለውን ደንብ ተቀብሎ ጥቅም ላይ አዋለ፡፡ ይህ ውሳኔ በእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ከወጣው የመጀመሪያው ከጨዋታ ውጪ መመሪያም ሆነ በ1866 ከተሻሻለው ህግ ይልቅ ቅብብሎች ላይ ለሚያተኩረው አጨዋወት አመቺ መሆኑ በግልጽ ታየ፡፡ በህዳር 9-1870 ኩዊንስ ፓርኮች የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር አባል ሆኑ፤ አንድ ተጫዋች በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳይገኝ ሶስት-የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን የሚያካትተውን የጨዋታ ውጪ ደንብም መከተል ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ በቅብብሎች ላይ የተመሰረተው አጨዋወት ተቀባይነቱ ስር መስደድ ቻለ፡፡ በስኮትላንድ ኳስን በረጅሙ እየለጉ መጫወት እንጂ እንዲያው ዝም ብሎ ማንከባለል ብቻውን ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንዳልነበር የሚያንጸባርቅ ሐሳብ የያዘ እና ኩዊንስ ፓርኮች በ1869 ሃሚልተን ጂምናዚየምን ሲረቱ ድሉን ያከበሩበት የኤች.ኤን. ስሚዝ አጭር ግጥም ውስጥ የሚገኙ ስንኞች በሙሉ የወቅቱን እግርኳሳዊ አተያይ ፍንትው አድርገው ያቀርባሉ፡፡
ዓለምአቀፍ አግባብነታቸው የተረጋገጠ የብሄራዊ ቡድኖች ጨዋታ ሳይጀመር በፊት በአልኮክ አስተባባሪነት የተዘጋጁ፣ ተቀማጭነታቸውን ለንደን ከተማ ባደረጉ ስኮትላንዳውያን እና እንግሊዛውያን መካከል የተካሄዱ አራት ግጥሚያዎች ነበሩ፡፡ በመጀመሪያው የሃገራት እግርኳስ ግንኙነት በስኮትላንድ ብሄራዊ ቡድን ውስጥ የቀኝ መስመር ተጫዋችና የኩዊንስ ፓርክ አባል የነበረው ሮበርት ስሚዝ ደግሞ ከእነዚህ አራቱ ግጥሚያዎች በቀዳሚው ላይ የመሳተፍ እድል አግኝቷል፡፡ ከተሳትፎው በኋላ ለክለቡ በላከው ደብዳቤ ” በጨዋታ እንቅስቃሴ ወቅት ኳሱን በከፍታና ረዘም ባለ ርቀት ከመምታት ይልቅ በእግር ይዞ መሮጥን አልያም ድሪብል ማድረግን እንመርጥ ነበር፡፡” ሲል አሳውቋል፡፡ ይህም የድሪብሊንግ ስልት በመስፋፋት ሒደት ጅማሮ ላይ መሆኑን አመላካች ምሳሌ ነበር፡
ኩዊንስ ፓርኮች በእንግሊዝ እግርኳስ ማኅበር ስር እንዲታቀፉ ካነሳሱ ጉዳዮች መካከል የሚከተሏቸውን የጨዋታ ህግጋት ተቀብለው ግጥሚያዎች የሚያደርጉ ተቃራኒ ቡድኖች ለማግኘት የሚገጥማቸውን ተግዳሮት ለማርገብ ሲሉ ነበር፡፡ በእግር ኳስ ማኅበሩ ተቀባይነት ሊያገኙ በተቃረቡበት የመጨረሻዎቹ ወራት ከአንድ ተጋጣሚ ጋር አስር፣ አስራ አራት፣ አስራ አምስትና አስራ ስድስት የሚደርሱ ጨዋታዎችን የማድረግ አጋጣሚ አግኝተዋል፡፡ ሶስት ጨዋታዎች ብቻ ባካሄዱበት የ1871/72 መጨረሻም ቢሆን ” ክለቡ በፍፁም ልምምዶች ማድረጉን ችላ አላለም፡፡” ሲል ሪቻርድ ሮቢንሰን በ1920 ባወጣውና <የኩዊንስ ፓርክ ታሪክ> በሚለው መጽሃፉ ላይ አስፍሯል፡፡ ልክ እንደ 1930ዎቹ አርጀንቲናዊያን ኩዊንስ ፓርኮችም ከሌሎች ተነጥለው እርስበርሳቸው የሚያደርጓቸው መደበኛ ግጥሚያዎች ልማድ እየሆኑ በቀላሉ ጎልተው መታየት ጀመሩ፡፡ በዚህ የተነሳም ቅብብሎች ላይ አጽዕኖት የሚሰጠው ጨዋታ በውጤታማነት የሚታይ፣ በዝቅተኛ እድሜ እየተሰጠ ላቅ ያለ ትምህርት የሚገኝበት እና ከጠንካራ ተጋጣሚዎች የሚመጡ አሰልቺ ተግዳሮቶች ነፃ የሚያደርግ ሆነ፡፡
“የስኮትላንዳውያኑን ጨዋታ ከፍ ወዳለ የፈጠራ እርከን ያሸጋገረው ድሪብሊንግና ቅብብሎች ላይ የተመሰረተው ቅይጥ ልምምድ ይበልጡን እድገት ማሳየት ጀመረ፡፡” ሲልም ሮቢንሰን ይቀጥላል፡፡” ድሪብሊንግ የእንግሊዛውያን እግርኳስ መገለጫ ነበር፡፡ እንዲያም ሆኖ ብዙም ሳይቆይ በደቡባዊ የሃገሪቱ ክፍል ጨዋታውን የሚያዘወትሩ እግርኳስ ወዳዶች በኩዊንስ ፓርክ ክለብ ውስጥ በተጫዋቾች ጠንካራ መደጋገፍ የሚታገዘው ኳስ የማንሸራሸርና ከቦታ ቦታ የማሸጋገር ዘዴ ጋር ከተገናኘው የአጨዋወት መርህ አንድ ቡድን ምርጡን ሊያገኝ እንደሚችል ተገነዘቡ፡፡ በጊዜው ኩዊንስ ፓርኮች በተሳካ ዉህደት የተለየ ህብር ፈጥሮ መቅረብ ላይም የተካኑ ስለነበሩ ስልቱ ዋነኛው የአቀራረብ ባህሪያቸው ማሳያ ተደርጎ ተወሰደ፡፡ አልኮክም በእነዚህ አንኳር ጉዳዮች ይገረምና ከቀደምት አመታዊ መጽሔቶቹ በአንዱ ላይ ስኮትላንዳውያን ተጫዋቾችን የሚያወድስ መጣጥፍ አዘጋጀ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጥልቀት ታስቦባቸው የተሰሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥናታዊ ጽሁፎች በእንግሊዛውያን ተጫዋቾች ወዲያውኑ ተቀባይነት ያገኘው የስኮቶቹ ዘዴ በሰሜናዊው ትዊድ ክልል ጨዋታውን ወደ ላቀ ደረጃና ከፍተኛ ስኬት እንዲሸጋገር አደረገው፡፡”
በእርግጥ አልኮክ በድሪብሊንግ እጅጉን ያምን ነበር፡፡ ምንም እንኳ በህብረት ጨዋታ የተማረከ ስለመሆኑ በግልፅ ቢያውጅም፣ በሼፊልድ ቆይታው በዚሁ ዘይቤ ልዩ ችሎታውን ቢያሳይም በ1879 በወጣው መጽሄት ” ሙሉ በሙሉ ቅብብሎች ላይ የተመሰረተው የአጨዋወት ስርዓት ዋጋ ያስከፍላል፡፡” በማለት ስጋቱን አስቀምጧል፡፡” ቅብብል እንደ አንድ አማራጭ የአጨዋወት ዘይቤ ሊታሰብ የሚችል እንጂ በድሪብሊንግ ምትክ ፍጹም ጥቅም ላይ መዋል የሚኖርበት ስልት እንደማይሆን ያስብ ነበር፡፡
የኩዊንስ ፓርክ ተጽዕኖ በከፍተኛ መጠን በሚያይልበት ስኮትላንድ ድሪብሊንግ በፍጥነት መስፋፋቱን ተያያዘው፡፡ በአጫጭር ቅብብሎች የተገመደው የሽመና ንድፍ መሳዩ ስልት በመሀለኛውና ፊተኛው የሜዳ ክፍል ተጫዋቾች ጠመዝማዛ እንቅስቃሴያዊ ቅርጽ እየሰሩ የሚጫወቱበት ልዩ ባህርይ የተላበሰው አቀራረባቸው ይበልጥ ተወዳጅነት እየኖረው ሄደ፡፡ ኩዊንስ ፓርኮች የስኮትላንድ እግርኳስ ማኅበር ከተቋቋመ በኋላ እንኳ ሃገሪቱ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎች እንድታደርግ ብሄራዊ ቡድኗን በማደራጀት በኩል እገዛ አድርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስፖርቱን በመምራትና መሰረታዊ ቅርጽ እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ትልቅ ተሰሚነትና ተጽዕኖ ነበራቸው፡፡ በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እየተዘዋወሩ የኤግዚቢሽን ጨዋታዎችን በማድረግ የእግርኳስ አስተዋዋቂነት ሚናንም ተወጥተዋል፡፡ እግርኳስ በ1873 በስኮትላንድ ርዕሰ መዲና ኤደንበርግ በተጀመረበት ወቅት በሀይቆቿ ብዛት ተለይታ በምትታወቀው ሌላኛዋ የሃገሪቱ ማዕከላዊ ከተማ ሌቨን የሚገኘውና ቀደምት የእግርኳስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የነበረው ቫሌ የተባለው ቡድን ግጥሚያዎችን ሲያደርግ የተመዘገቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ጨዋታዎቹ በተወሰኑ የጊዜ ልዩነቶች እየተቋረጡ ህግና የአጨዋወት ስልቶች ላይ ገለጻ ይደረግ ነበር፡፡ የእነዚያ ጨዋታዎች ተጽዕኖ ምናልባትም የጠረፍ ከተሞቹ በራግቢ ጨዋታ ላይ ያላቸውን ጥንካሬ ይዘው እንዲቀጥሉ ለማድረጉ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ በጊዜው በኤፍ.ኤ ዋንጫ ጨዋታዎች ምክንያት ኩዊንስ ፓርኮች ራቅ ወዳሉት ከተሞች እየሄዱ ስለ እግርኳስ መስበክ ባለመቻላቸውና ግጥሚያዎችን ባለማድረጋቸው እነዚያ ቦታዎች ላይ የመስፋፋት ሒደቱ ስር ሊሰድ አልቻለም፡፡ ማክ ቤርቲ እንዳለውም “በሀገሪቱ ማዕከላዊ ከተሞች ባለው ከፍተኛ የህዝብ ስርጭት ተከታታይ ማህበረሰባዊ ግንኙነት የሚያመዝነው በግላስኮውና በኤደንበርግ በመሆኑ እንግሊዛውያኑ በየክልሎቻቸው ከሚያሳዩትና ጨዋታውን በተለያዩ መንገዶች ከሚያከናውኗቸው ሁኔታ በተለየ አንድ የአጨዋወት ስልትን ለማስረጽ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡”
በመጀመሪያው የሃገራት የእርስበርስ ጨዋታ የኩዊንስ ፓርኮች ታክቲክ ለእንግሊዞች ዓይን ገላጭ ሆነ፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ደቡባዊው የእንግሊዝ ክልል የተዛመተውና ቅብብሎችን የሙጥኝ ያለው አጨዋወት ይበልጡን እውቅና ያገኘው በሁለተኛው ዓለም አቀፍ ጨዋታ ስኮትላንድ እንግሊዝን ስትረታ ለአሸናፊው ቡድን ተሰላፊ በነበሩት ሄንሪ ሬኒ-ቴይለር እና ጆን ብላክበርን በተባሉ ሰዎች አማካኝነት ነው፡፡ ሁለቱም በጦሩ ክፍል በመቶ- አለቅነት ማዕረግ የሚያገለግሉ ወታደሮች የነበሩ ከመሆናቸውም በላይ የእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመናቸውን በሮያል ኢንጂነርስ ክለብ አሳልፈዋል፡፡ የስኮትላንድ አጨዋወት ዘይቤንም ወደ ደቡባዊ ምስራቅ የእንግሊዝ ከተማ ኬንት ይዘው ተጉዘዋል። በ1930 ክሌይግ የተባለው የቀድሞ የሼፊልድ ተጫዋች “ሮያል ኢንጂኒርሰ የህብረት-ጨዋታ ስልትን በማስተዋወቅ ረገድ የመጀመሪያው ቡድን ነው፡፡” ሲል ሼፊልድ ኢንዲፔንደንት ላይ ጽፏል፡፡ ” ቀደም ብሎ ሼፊልድ ከሮያል ኢንጅነርሶች ጋር ያደርግ የነበረውን ጨዋታ ሁሉ ያሸንፍ ነበር፡፡ በሒደት ከአንዱ የውድድር ዓመት ወደ ሌላው በተሸጋገርን ጊዜ ሁሉ ወታደራዊ የእግርኳስ ታክቲክ በመያዝ ቡድናችን በአዲሱ የአጨዋወት ዘዴ በከፋ ሁኔታ የሚሸነፍበትን ስልት ቀይሰው እጅጉን ያስገርሙን ጀመር፡፡” በማለት ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
ቅብብሎችን ተገን ያደረገው አቀራረብ በትምህርት ቤቶች ውስጥ በሚካሄደው እግርኳስ ዘንድ ቦታ ያገኘው ሪቨረንድ ስፔንሰር ዎከር ቀድሞ በተማሪነት ወዳሳለፈበት ላንሲንግ ኮሌጅ በአለቅነት ተመልሶ “እንደነገሩ” የነበረውን ስብስብ በአግባቡ ወደ ተደራጀ ቡድንነት ሲቀይረው ነበር፡፡ “በመጀመሪያ የመጣልኝ ሐሳብ ከፊት ያለውን ዋና አጥቂ በሌሎች የፊት መስመር ተሰላፊዎች ማጀብ ነበር፡፡ እርሱን ከበውት ሁሉም የሜዳው ክፍል ላይ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህም አንደኛው መመሪያችን በተወሰኑ ቦታዎች ሁሉም አጥቂዎች ኳሱን እየተቀባበሉ እንዲንቀሳቀሱባቸው በማድረግ የመጀመሪያዎቹ ተፋላሚዎቻችን ‘ምን ጉድ ውስጥ ነው የገባነው?’ የሚል ግርታ እንዲፈጠርባቸው ማድረግ ሆነ፡፡” በማለት ክሌይግ አክሎ ጽፏል፡፡
የአልኮክ እውነታን የመጠራጠር ባህሪ እንዳለ ሆኖ ቅብብሎች ላይ የተመሰረተ አጨዋወት የወደፊቱ እግርኳሳዊ መሰረት መሆኑ ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ በ1881 የኤፍ.ኤ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ቀደምቶቹን ኢቶንያኖች 3-0 የረቱት የጥንቶቹ ካርቱሲያኖች ቡድን በህብረት ጨዋታቸው ይታወቁ ነበር፡፡ በተለይ በፕሪንሴፕና ፓሪ መካከል የነበረው ውህደት የተለየ ሆነ፡፡ በቀጣዩ ዓመት ብላክበርን ሮቨርሶች ከሰሜናዊው የሃገሪቱ ክፍል ለመጀመሪያ ጊዜ ለፍጻሜ እንዲደርሱ ያስቻለችውና ኦልድ ኢቶንያኖቹ ያስቆጠሯት ግብም ከደን ተነስታ አንደርሰን እግር ስር ያረፈችና ከረጅም ድሪብሊንግና ተሻጋሪ ቅብብል የተገኘች ነበረች፡፡” በማለት የእግርኳስ ማኅበሩን ዋንጫ ታሪክ ባወሳበት ጽሁፉ ጠቅሷል፡፡ እንዲያም ሆኖ ኢቶንያኖች በዋናነት ለድሪብሊንግ ቅድሚያ ይሰጡ ነበር፡፡
በ1883 የመጨረሻው የድሪብሊንግ አጨዋወት ከፍታ ታየ፡፡ በዚህ ወቅት ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በለንደን ውስጥ ካሉት ተወዳዳሪዎች በላቀ ከዋና ከተማው ወጪ ተሳታፊ የሚሆኑ ቡድኖችን ያዘ፡፡ በእግርኳስ ማህበሩ ዋንጫ ታሪክም ከሰሜናዊው የሃገሪቱ ክፍል የተገኘው ብላክበርን ኦሊምፒክ በፍጻሜው ኦልድ ኢቶንያንስን አሸንፎ ዋንጫውን የወሰደ የመጀመሪያ ቡድን ሆነ፡፡ እግርኳስ ላይ የሚታየው የአማተር አመለካከት ዘመን እያከተመ መጥቶ ከሁለት አመት በኋላ እግርኳስ ማህበሩ ደረጃውን የጠበቀና በዘርፉ ስልጡን በሆኑ ባለሙያዎች የሚመራ ተቋም የመሆን ህጋዊ ቁመናን ተላበሰ፡፡ በስተመጨረሻም ጨዋታውና ተሳታፊዎቹም ይህን መንገድ መከተል ጀመሩ፡፡
በወቅቱ የኦሊምፒክ ቡድኑ አባላት የሙሉ ሰዓት ስራ ነበራቸው፡፡ ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት በጊዜው የቡድኑ አማካይና አሰልጣኝ የነበረው ጃክ ሀንተር ተጫዋቾችን ወደ ብላክፑል የልምምድ መስሪያ ቦታ ሲወስዳቸው ከፍተኛ የሆነ ጥድፊያ ነበር፡፡ ይህም አማተሮቹን ግልጽ በሆነ መልኩ ጥረት አልባ የበላይነትን እንዳያልሙ አላደረጋቸውም፡፡ ጨዋታው ተጀምሮ ደቂቃዎች ብዙም ሳይገፉ ኢቶንያንስ አንድ ተጫዋች ተጎዳባቸውና አስር ሆነው ቀጠሉ፡፡ ያ ባይሆን እንኳ ኦሊምፒክሶች ይተገብሩ የነበረውን ከሜዳው አንደኛው የጎንዮሽ መስመር ወደ ሌላኛው በረጅሙ እየተቀባበሉ በደራ ስልት ይጫወቱበት የነበረውን ያልተለመደ ታክቲክ መቋቋም ስለመቻላቸው ጥርጣሬን ያጭራል፡፡ በጭማሪው ሰዓት መገባደጃ ደቂቃ ላይ የተገኘው የማሸነፊያ ግብ የጨዋታውን አጠቃላይ መልክ የሚገልጽ ሒደትን አሳይቷል፦ በቀኝ መስመር ከቶሚ ዶውረስት (ሸማኔው) የተነሳው ተሻጋሪ ኳስ በግራ መስመር ወደነበረው ጂሚ ኮስሊ (ፈታዩ) ጋር ይደርሳል፤ እርሱም በመስመሩ ተቀናቃኙንና በኢቶንያንስ የግብ ክልል አካባቢ የነበረውን ሮውሊንሰንን በእርጋታ አልፎ ግቧን አስቆጠረ፡፡
በወቅቱ በስኮትላንድ ስለ ቅብብሎች ጨዋታ የበላይነት ማውራት ያረጀና ያፈጀ ጉዳይ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ በስኮቲሽ ኢምፓየር አምደኛ የነበረው ሲላስ ማርነር በነሐሴ 1884 የጋዜጣው እትም ላይ ” እግርኳሳዊ እድገት ባሳየ የትኛውም ክለብ ውስጥ ቀጣይ አዎንታዊ ለውጦች የሚገኙት ቅጥ ያጡት እና ዘፈቀዳዊ የሆኑት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች ልኬታቸውን በጠበቁ ፈጣን ቅብብሎች ሲተኩ፣ የሰነበተውን የጨዋታ ስርዓት የሙጥኝ ብሎ በኃይልና ስልጡን ባልሆነ ዘዴ ተጋጣሚን ለመቋቋምና ለመርታት ከሚመነጭ የወረደ ፍላጎት ይልቅም ለኳሱ ፍሰት ትኩረት መስጠት ሲቻል ነው፡፡” በማለት መከራከሪያ ሐሳቡን አሰፈረ፡፡ ሆኖም ይህ አስተያየቱ ሁሉንም የሚያሳምን አልሆነለትም፡፡ በስኮትላንድ ዋንጫ ጄምስታውን አትሌቲክስ በሌቨን ከተማው ቡድን ቫሌ 4-1 ከተሸነፈ ሁለት ወር በኋላ በኢምፓየር ጋዜጣ- ኦን ዘ ዊንግ አምዱ ኦሎምፒያኖች ቅድሚያ በሚሰጡት እና የቡድን ስራ ላይ የሚያተኩረውን አጨዋወት በሰላ ትችቱ ክፉኛ ነቀፈው፡፡ ” ታላቁ ማኪያቬሊ ልዑላኖችን ስለ አመራር ጥበብ ሲያስተምራቸው ተወዳጁና ተመራጩ ፖለቲካዊ የማስተዳደር ስልት ከፋፍለህ ግዛ የሚለው መርህ ነው፡፡ ጄምስታውኖች የአባባሎችን እውነተኛነት ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ሙከራ በምን መልኩ ልገልጸው እችል ይሆን? መነሻ ሀሳቦቻቸው ትክክል ቢሆንም በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ተሳሳተ መደምደሚያ ይደርሳሉ፡፡ ከተጋጣሚዎቻቸው ይልቅ እርስ በርሳቸው የመከፋፈል ከባድ ስህተት ይሰሩና ትልቅ ዋጋ ይከፍሉበታል፡፡ በጋዛ የማይነገር! በኤስኬለን የማይታተም! አሰገራሚ ቅጣት! ስትራቴጂ መቼም ቢሆን የአስራ አንድ ተጫዋቾችን ብቁ አዕምሮና ንቁ ጥምር እግሮች ሊገዳደር አልያም ሊተካ አይችልም፡፡” በማለት ወረፋቸው፡፡
ይቀጥላል…
ስለ ደራሲው
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡
-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)
-Sunderland: A Club Transformed (2007)
-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)
-The Anatomy of England (2010)
-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)
-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)
-The Anatomy of Liverpool (2013)
-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)
-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)
ቀደምት ምዕራፎች | |
መቅድም | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት | LINK |