የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን በ2020 በቶኪዮ ለሚካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የአፍሪካ ዞን የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታ ሶማሊያን በአዲስ አበባ ስታዲየም ገጥሞ በሁለቱ አጋማሾች በተቆጠሩ ሁለት ሁለት ግቦች በድምሩ 4ለ0 ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ያለውን እድል አስፍቷል፡፡
ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ በታየበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በንጽጽር የተሻለ የሚባልን የጨዋታ ቁጥጥር የበላይነት አሳይቷል። ነገርግን ሶማሊያዎችም በመልሶ ማጥቃት አደገኞች ነበሩ፡፡
ከክፍት ጨዋታ የግብ እድልን መፍጠር የተሳነው የኢትዮጵያ ቡድን በተደጋጋሚ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ ወደ ግብ ከሚላኩ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በዚህም በ28ኛው ደቂቃ ዳዊት ማሞ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በቅርቡ ቡድኑን የተቀላቀለው ከነዓን ማርክነህ ቡድኑን ቀዳሚ ያረገችውን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡
በግቧ መቆጠጠር የተነቃቁ የሚመስሉት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች በ39ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ ያሳለፈለትን ግሩም ኳስ ተጠቅሞ የሀዋሳ ከተማው እስራኤል እሸቱ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ያሳደገችውን ግብ አስቆጥሮ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ክፍል በኢትዮጵያ 2-0 መሪነት ማምራት ችለዋል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታው ሂደት ከመጀመርያው ጋር ተመሳሳይ ይዘት የነበረው ነበር፡፡ በዚህ አጋማሽ ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት አማኑኤል ገብረሚካኤልና አቡበከር ሳኒ የቡድናቸውን አሸናፊነትን ያረጋገጡትን ቀሪ ግቦች ሲያስቆጥሩ አቡበከር በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣውም በዚህ አጋማሽ ነበር።፡፡
ሀብታሙ ገዛኸኝን ተክቶ የገባው አማኑኤል ገ/ሚካኤል ራሱ ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት በ66ኛው ደቂቃ ሲያስቆጥር በ70ኛው ደቂቃ እንዲሁ ከነዓን ማርክነህ ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ አቡበከር ሳኒ የማሳረጊያውን ኳስ አስቆጥሯል፡፡
በ68ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አቡበከር ሳኒ ለ8 ያክል ደቂቃዎች በሜዳ ላይ ቆይታ ካደረገ በኃላ በ75ኛው ደቂቃ ላይ በሰራው አደገኛ ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል፡፡
ጨዋታው በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን የ4ለ0 የበላይነት መጠናቀቁን ተከትሎ በቀጣዩ ሳምንት ማክሰኞ ከሚደረገው የመልስ ጨዋታ በፊት የማለፍ እድሉን አስፍቷል፡፡
የጨዋታውን ሙሉ መረጃ ሊንኩን ተጭነው ያገኛሉ | LINK |