የብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ቀጥሏል

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአለም ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ከኮንጎ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ በካፒታል ሆቴል ተቀምጦ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡

የፔትሮጄቱ አማካይ ሽመልስ በቀለ ትላንት አዲስ አበባ በመግባት ዛሬ ረፋድ ላይ የብሄራዊ ቡድን ልምምዱን ያደረገ ሲሆን ራምኬል ሎክ ከፍርድ ቤት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በዛሬው ልምምድ ላይ አልተካፈለም፡፡ በአጠቃላይ 23 ተጫዋቾችም የዛሬውን ልምምድ ሰርተዋል፡፡

ከውጭ ክለቦች ጥሪ ከደረሳቸው መካከል አንዱ የሆነው የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ፕሪቶርያው አጥቂ ጌታነህ ከበደ ትላንት ሌሊት አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ነገ ብሄራዊ ቡድኑን ተቀላቅሎ ልምምድ ይጀምራል፡፡ የጊንኪልብሪጊው ተከላካይ ዋሊድ አታ ግን እስካሁን አዲስ አበባ አልገባም፡፡

የወዳጅነት ጨዋታ ማግኘት ያልቻሉት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ቡድኑን ለሁለት በመክፈልና እርስ በእርስ በማጫወት የተጫዋቾቻቸውን ወቅታዊ አቃም ለመገምገም አስበዋል፡፡ በነገው እለትም ቡድኑን ለሁለት በመክፈል ጨዋታ ያደርጋሉ ተብሏል፡፡ ጨዋታው ለህዝብ ክፍት በመሆኑ ማንኛውም ተመልካች ስታድየም ተገኝቶ መከታተል እንደሚችልም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ እና የኮንጎ ጨዋታ በመጪው ቅዳሜ (ህዳር 4 ቀን 2008) በአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረግ ሲሆን ከ3 ቀን በኋላ (ህዳር 7 ቀን 2008) ደግሞ የመልስ ጨዋታውን በብራዛቪል ያደርጋሉ፡፡

IMG_8428

© Soccer Ethiopia

ያጋሩ