የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም 23ኛ ሳምንት በሀንጋሪ ወርቃማ ትውልድ እና “የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ጨዋታ” ላይ አተኩሮ እንዲህ ይቀርባል ።
|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ | LINK |
የሃንጋሪያውያኑና እግርኳስ መስተጋብር
የኦስትሪያ <ዉንደርቲም/Wunderteam> እና የዳይናሞ ሞስኮ <ፓሶቮችካ/Passovotchka> የጉዞ ተመክሮዎች የወደፊቱ እግርኳስ መልክ ምን እንደሚመስል ፍንጭ ሰጥተው አልፈዋል፡፡ ይሁን እንጂ እንግሊዞች አህጉራዊው የአጨዋወት ዘይቤ (Continental Game) በየትኛውም ዓይነት ውል አልባ ልፋትና አካላዊ ትጋት የማይካካስ የልህቀት ደረጃ (Level of Excellence) ላይ የመድረሱን እውነታ የተቀበሉት በ1953 ነው፡፡
የሃንጋሪያውያኑ ወርቃማ ትውልድ <አራኒሳፓት/Aranycsapat> ኅዳር 25 -1953 በዌምብሌይ ያደረገው ጉብኝት <የክፍለ ዘመኑ ግጥሚያ> የተሰኘና ዘመን-ተሻጋሪ ትርክት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውን ጨዋታ አስገኘ፡፡ ሃንጋሪ የ1952ቱ ኦሊምፒክ ባለድል ከመሆኗ ባለፈ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ራሷን የስፖርቱ ልዕለ-ኃያል አድርጋ ከምታስበው “የእግርኳስ ፈጣሪዋ” ሃገር ጋር ባከናወነችው ፍልሚያ ለሶስት ዓመታት ያህል አንድም ጊዜ ሽንፈት ያልገጠመው ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን አደራጅታ ቆየች፡፡ ለዌምብሌዩ እግርኳሳዊ ጦርነት የተቸረው ክብደትና የተዥጎደጎደለት ማስታወቂያ ምናልባት የተጋነነ የገበያ ቅስቀሳ አላማ አንግቦ ሊሆን ቢችል እንኳ በእንግሊዝ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ ይህን ያህል ትኩረት የተሰጠው እና ከፍተኛ አጀብ የበዛበት ጨዋታ አልተደረገም፡፡ ሃገሪቱ ከዚያ ቀደም በውጭ ተጋጣሚዎች ለመጨረሻ ጊዜ የተረታችው እጅጉን ባልተጠበቀ ሁኔታ ከሶስት ዓመታት ቀደም ብሎ በተካሄደው የ1950ው የዓለም ዋንጫ በአሜሪካ ነበር፡፡ የአየር ሁኔታና የዳኝነት በደሎች በሰበብነት ሳይጠቀሱ በ1949 ጉዲሰን ፓርክ ላይ በሪፐብሊክ አየርላንድ ከገጠማት ሽንፈት በስተቀር በሜዳዋ እጅ ሰጥታ አታውቅም፤ ከዚህ በተጨማሪ በባላንጦቿ የጨዋታ ብልጫ ተወስዶባትም አልታየችም፡፡ በእርግጥ የሃንጋሪው የ6-3 ሽንፈት የእንግሊዝ እግርኳስ ቁልቁል መምዘግዘግ የጀመረበት ቅጽበት አይሁን እንጂ የውድቀት ጊዜ መምጣቱን የሚያመላክት ጥቆማ ቢጤ ደውል ማቃጨሉ ግን እሙን ነው፡፡ በጉዳት ሳቢያ በጋዜጠኞች መቀመጫ ሆኖ ጨዋታውን ለመከታተል የተገደደው ቶም ፊኒ ከሰላሳ ዓመታት ቀደም ብሎ ጋብሬል ሃኖት ያነሳውንና በጋማ ከብቶች ዙሪያ የሚያጠነጥነውን ዘይቤአዊ አገላለጽ አሰታውሶ ” በሁለቱ ቡድኖች መካከል የተስተዋለው ልዩነት የጋሪ ፈረሶችን ለግልቢያ ውድድር ከተዘጋጁ ፈረሶች እኩል የመጠቀም ያህል ነበር፡፡” ሲል ተናገረ፡፡
በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው ግማሽ ምዕተ-ዓመት በእግርኳሱም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ ሃንጋሪ በኦስትሪያ ጥላ ስር ነበረች፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በማያጠያይቅ መልኩ የሃንጋሪያውያኑ አጨዋወት ፍልስፍና ላይ የሑጎ ሜይዝል ተጽዕኖ እና የዳኑቢያኑ ግራ አጋቢ የሽክርክሪት እንቅስቃሴ (Danubian Whirl) አጥልቶባቸው ኖሯል፡፡ ከሁሉ በላይ በጥልቀት የማሰብ እና ምክንያታዊ ሆኖ የመገኘት ልማዳቸው (Thinking) እግርኳሱ ላይም ቀዳሚ እሴት ሆነላቸው፡፡ እንደቪየናው የቡና ቤቶች ምሁራዊ ወግ ሁሉ በቡዳፔስትም እግርኳስ የልሂቃኑ የዘወትር አጀንዳና መከራከሪያ አርዕስት ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህን ተከትሎም ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲጀመር ወደ ሃገሩ ለመመለስ ከመገደዱ በፊት በሃንጋሪ የማሰልጠን እድል ያገኘው የቀድሞው የቶተንሐም ተጫዋች አርተር ሮው በ1940 W-M ፎርሜሽንን በሚመለከት ትምህርታዊ ማብራሪያ (Lecture) እንዲሰጥ ግብዣ ቀረበለት፡፡ በቀደሙት ጊዜያት አብዛኞቹ ብሪታኒያውያን አሰልጣኞች በመሃል ሜዳ ተገድቦ የሚንቀሳቀሰው ግትሩ የተከላካይ አማካይ (Stoper Center-Half) ላይ ጥገኛ የመሆን አዝማሚያ አሳይተዋል፡፡ በተጫዋቾች የሜዳ ሚና እና እንቅስቃሴያዊ አደራደር (Formation) ዙሪያ የሚያተኩረው የአስተሳሰብ አድማሳቸው ተሸብቦ የከረመውም በዚሁ ቅኝት ነበር፡፡ የኋላ ኋላ ረጃጅም ኳስና ፍጥነትን አጣምሮ የሚይዘው አቀራረብ (Push-and-Run) ላይ ቢያመዝንም አርቱር ሮው በሌሎች የ<ሲስተሙ> በጎ ጎኖች ላይ የማተኮር ዝንባሌ ሲያሳድር ስለኖረ የማስተማር እድሉ ለእርሱ እንዲሰጥ ሳይወሰን እንዳልቀረ ይገመታል፡፡
በራሱ ከነበሩበት አሉታዊ የመዋቅር ህጸጾች በተጫማሪ በሰፊው የተንሰራፋውና ረዘም ላለ ጊዜ የሰነበተው የW-M ፎርሜሽን አረዳድ የመሃል አጥቂዎች (Centre-Forward) አመራረጥን በተመለከተ በብዙዎች ዘንድ በዘላቂነት ያሰረጸው ግንዛቤ ትልቅ ችግር ፈጠረ፡፡ በውስን እንቅስቃሴ መሃል ሜዳው ላይ የሚጫወቱት የተከላካይ አማካዮች (Stoper Center-Halves) በአብደኞቹና <ድሪብለሮቹ> ተጫዋቾች ላይ ከፍተኛ የአካላዊ ፍልሚያ ብልጫ ሲወስዱ ያስተዋሉ አሰልጣኞች ፊታቸውን ወደ ቁመተ መለሎዎቹና የግዙፍ ተክለ ሰውነት ባለቤት የመሃል አጥቂዎች አዞሩ፡፡ እነዚህ የፊት መስመር ተሰላፊዎች እስካሁንም ድረስ በብሪታኒያ አይነተኞቹ ዘጠኝ ቁጥሮች (Classic No.9s) ተብለው ይጠራሉ፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ ብሪያን ግላንቪል ደግሞ በ1950ዎቹ እነኚሁኑ ተጫዋቾች እምብዛም አዕምሯዊ ብቃትን የማይጠቀሙ፣ በእንቅስቃሴያቸውም የደመነፍስ ምሪታቸውን የሚከተሉ እንደሆኑ ለማሳወቅ ሲል <Brainless bull at the gate> በማለት ሰይሟቸዋል፡፡ ማቲያስ ሲንድለር የማዕከላዊ አውሮፓ የመሃል አጥቂዎች ተምሳሌት ከሆነ፥ ጠንካራው፣ ጉልበታሙ፣ ደፋሩና ሃሳብ-የለሹ የአርሰናል አጥቂ ቴድ ድሬክ ደግሞ የእንግሊዞችን የፊት አጥቂዎች ውክልና ይወስዳል፡፡
በ1930ዎቹ አስገራሚ ክህሎት ኖሯቸው ተፈጥሯዊ ተክለሰውነታቸው ደቃቃ የሆኑት ተጫዋቾች (Der Papierenes) በእንግሊዝ እግርኳስ ውስጥ ቦታ እንዳልተሰጣቸው ሁሉ ጠብደሎቹ የመሃል አጥቂዎችም (Beefy Target-Men) በ1940ዎቹ የሃንጋሪ እግርኳስ እምብዛም ተፈላጊ አልነበሩም፡፡ በእርግጥ ጉዳዩ አከራካሪ ቢሆንም ከጥቂቶቹ ሐሳባውያን በስተቀር በብዙዎች ዘንድ 2-3-5 ፎርሜሽን በW-M (3-2-2-3) እንዲተካ፥ የእንግሊዞቹን የመሃል አጥቂዎች አጨዋወት ዘይቤ ቀጥታ በመውሰድ ማሻሻልና ማሳደግ አልያም የፎርሜሽኑን ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት እንዳለ አስጠብቆ የማጥቃት ሒደቱን ያለ ጡንቸኛ አጥቂ ማስቀጠል ለሃንጋሪያውያኑ የቀረቡ ሁለት አማራጮች ነበሩ፡፡
የMTK ክለብ (በ1949 በሃገሪቱ የሚገኙ ትልልቅ የግል ንብረቶች በሙሉ ህዝባዊ ባለቤትነት እንዲኖራቸው በመንግስት ሲታወጅ የክለቡ ስያሜ ቮሮስ ሎቦጎ ተብሎ መሰየሙን ልብ ይሏል፡፡) አሰልጣኝ የነበረው ማርቶን ቡኮቪ በ1948 ትውልደ ሩማኒያዊው ፈርጣማ ተከላካይ ኖርበርት ኾፍሊንግን ለላዚዮ ሲሸጥ ለችግሩ መፍትሄ አበጀ፡፡ “ለአጨዋወት ስልቴ ምቹ የመሃል አጥቂ ስላልነበረኝ በቦታው ተስማሚ ያልሆኑ ሌሎች ተጫዋቾችን ለመሞከር ከምገደድ ይልቅ ያን የፊት መስመር ተሰላፊ ሙሉ በሙሉ ላለመጠቀም ወሰንኩ፡፡” ይላል ችግሩን ስለቀረፈበት መንገድ ሲገልጽ፡፡ ከነባሩ <W-M> ፎርሜሽን ላይ <W>ን ወደ <M> ገለበጠና <M-M> መሳዩን አዲስ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያዊ አደራደር ፈጠረ፡፡ ቀስ በቀስ የመሃል አጥቂዎች ቀድሞ ከሚንቀሳቀሱበት ተለምዷዊ ክልላቸው በጥልቀት ወደ ኋላ አፈግፍገው እንደ አጋዥ አማካዮች (Auxiliary Midfielders) መጫወት ሲጀምሩ ሁለቱ የመስመር አማካዮች (Wingers) ደግሞ ይበልጡን ወደ ፊት ተጠግተው ታዩ፡፡ ይህ ለውጥ በአራት የፊት መስመር ተሰላፊዎች አማካኝነት የሚዋልል የአጥቂን ክፍል (Fluid Front-Four) አስገኘ፡፡ በጥልቀት ወደኋላ ባፈገፈገ ሚናው በዌምብሌይ እንግሊዝን ከፍተኛ ስቃይ ውስጥ የከተታት ናንዶር ኼጁኩቲ ” የመሃል አጥቂዎች በተጋጣሚ ተጫዋቾች ጥብቅ የሆነ የቅርብ ክትትል (Marking) እየተደረገባቸው ሲቸገሩ ዘጠኝ ቁጥሮቹ መጠነኛ ክፍት ቦታ ወደሚያገኙበት የሜዳ ክፍል አፈግፍገው እንዲጫወቱ የሚያስችለው ሐሳብ መነጨ፡፡” ሲል ስለአዲሱ የአጥቂዎች ሚና ያብራራል፡፡
” በMTK ቡድን ውስጥ በሜዳው ቁመት የመሃለኛው ክፍል በመስመር የሚጫወት (Wing -Half) ፒተር ፓሎታስ የሚባል የተሳኩ ቅብብሎች የሚከውን ምርጥ የማጥቃት ተጫዋች ነበር፡፡ ፒተር ጠንካራ ምቶችን (Shots) ጭራሽ የማይደፍር ፣ ግቦች የማስቆጠር ልምድ ያልተላበሰ ስለነበር ዘጠኝ ቁጥር መለያውን ለብሶ የሚታወቅበትን አጨዋወት ቀጠለ፡፡ መሃለኛው የሜዳ ክፍል ላይ እየተገኘ ከተከላካዮች ኳሶችን እየተቀበለ ለመስመር አማካዮችና ከመሃል አጥቂ ግራና ቀኝ ለሚንቀሳቀሱት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) በጥሩ ሁኔታ ማሰራጨት ጀመረ፡፡ እየዋለ-እያደር የመሃል አጥቂዎች ከሚያዘወትሩት የተለመደ ቦታቸው ወደኋላ አፈግፍጎ የሚጫወተው (Withdrawn Center-Forward) ፓቶላስ ቀድሞ በሚሰለፍበት የሜዳ ክፍል (Wing-Half) ከሚወጣው ሚና አንጻር ይህኛው ኃላፊነቱ ያልተለመደ ሆነ፡፡ ስለዚህ አንደኛው የክንፍ አማካይ ወደኋላ ተመልሶ በጥብቅ የመከላከሉ የጨዋታ ዑደት ውስጥ (Tight Defensive Game) የግድ ተሳታፊ መሆን ተጠበቀበት፤ ሌላኛው ደግሞ ከፓቶላስ ጋር በመጣመር ከአማካይ ክፍሉ የሚነሳውን የማጥቃት እቅድ መምራት ኖረበት፡፡” ይላል ዝነኛው አጥቂ በወቅቱ ወሰብሰብ ብሎ ብዙዎችን ግራ ስላጋባው የጨዋታ ሲስተም ሲያስረዳ፡፡
ኼጁኩቲ ለMTK በመስመር አማካይነት (Winger) ተጫውቷል፤ ጉስታቭ ሴቤዝ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ይህን የተጫዋቾች የሚና ለውጥ ተግባራዊ ሲያደርግ ወደኋላ ያፈገፈገ የፊት መስመር ተሰላፊነት (Withdrawn Striker) ኃላፊነቱን ለፓሎታስ የሰጠበት ምክንያትም ይኸው የተጫዋቹ ብቃት አሳምኖት ሳይሆን አይቀርም፡፡ አሰልጣኙ በ1952ቱ የኦሊምፒክ ውድድር ሃንጋሪ ስኬታማ እንድትሆን ኼጁኩቲን በቡድኑ ውስጥ አካቶ መያዙ ጠቅሞታል፡፡ ብዙውን ጊዜ ኼጁኩቲ በቀኝ ቢጫወትም በዚያ የመስከረም ወር ሃንጋሪ በወዳጅነት ጨዋታ ሲውዘርላንድን 2-0 መምራት ስትጀምር ፓሎታስን ተክቶ ወደ ሜዳ ገባ፡፡ በእርግጥ ሴቤዝ ይህንኑ ቅያሪ ቀደም ብሎ ከጣልያንና ፖላንድ ጋር በተደረጉት የወዳጅነት ግጥሚያዎች ሞክሯቸዋል፡፡ የሃንጋሪያዊው አሰልጣኝ ውሳኔ ጨዋታዎቹን በሬዲዮ የቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፈው ጂዮርጂ ዜቤሲን በወቅቱ ሰላሳ አመቱ ላይ የነበረው ኼጁኩቲ ወደኋላ ባፈገፈገ ሚና (Withdrawn Role) ዝግጁ መሆኑን ለመገምገም እየሞከረ ስለመሆኑ ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ገፋፍቶታል፡፡ ይህንንም ግጥሚያ ሃንጋሪ 4-2 አሸነፈች፤ በተጋጣሚ ቡድኖች ዘንድ ለቁጥጥር ፍጹም አስቸጋሪ ቦታ ላይ የተሰለፈው ኼጁኩቲ ደግሞ በጨዋታው የሚቀመስ አልሆነም፡፡ እውቁ የሃገሪቱ ተጫዋች ፌሬንክ ፑሽካሽም ” ኼጁኩቲ አስገራሚ ጨዋታ የማንበብ ብቃት የታደለ ትልቅ ተጫዋች ነበር፡፡ ከአማካዮቹ ፊት ሆኖ አስደናቂ ቅብብሎችን ሲያደርግ፣ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን ወደ ራሱ እየሳበ ከመከላከል ቅርጻቸው ውጪ እንዲሆኑ በማስገደድ እንዲሁም ግቦችን ለማስቆጠር በሚያካሂደው ፈጣን ሩጫ ለአዲሱ ሚናው እጅግ ብቁ መሆኑን አስመስክሯል፡፡” ሲል ያወድሰዋል፡፡
ኼጁኩቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደኋላ ያፈገፈገ የመሃል አጥቂ (Withdrawn Centre-Forward) በሚል ስያሜ ይጠራል፤ ሆኖም ግን ስያሜው በአመዛኙ ተጫዋቹ ከሚለብሰው የመለያ ቁጥር አኳያ የወጣ በመሆኑ አሳሳች ይዘት አለው፡፡ ኼጁኩቲ በዘመናዊው እግርኳስ የተጫዋቾች ሚና አሰያየም (Modern Terminology) የአጥቂ አማካይ ነበር፡፡ ” አብዛኛውን ጊዜ የምንቀሳቀስበትን ቦታ በመሃለኛው የሜዳ ክፍል ዙሪያ በጆዜፍ ዛካሪያስ ጎን አደርጋለሁ፤ በሌላኛው መስመር ጆዜፍ ቦዚክ እስከ ተጋጣሚ ሳጥን ክልል ድረስ እየሄደ የማጥቃት ሒደቱን በማገዝ በርካታ ጎሎች ያስቆጥራል፤ በፊት መስመራችን ላይ በተከታታይ ግቦች የሚያመርቱልን ሁለቱ አጥቂዎቻችን (Inside-Forwards) ፌሬንክ ፑሽካሽና ሳንዶር ኮዚክ ነበሩ፡፡ እነዚህ ተጫዋቾቻችን በW-M ፎርሜሽን ከተለመደው ቦታቸው በላቀ ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ቀርበው ይጫወታሉ፤ ሁላችንም አጠር ላለ ጊዜ አዲሱን እንቅስቃሴያዊ የአደራደር ቅርጽ ከተለማመድነው በኋላ ጉስታቭ ሴቤዝ ሁለቱን የመስመር ተጫዋቾች (Wingers) ጥቂት ወደ መሃል አማካዮቹ ፈቀቅ እንዲሉ ሊጠይቃቸው ወጠነ፤ የማጥቃት ሒደትን የሚያስጀምሩ የቅብብል ስርጭቶች በሙሉ ከቦዚክና እኔ እንዲጀምሩ አደረገ፤ ይህም የመጨረሻውን ታክቲካዊ እመርታ አስገኘለት፡፡” በማለት ስለ አጨዋወታቸው ስርዓት ይተነትናል፡፡
በእርግጥ በጨዋታው እንግሊዝ ላይ ከፍተኛ ችግር የፈጠረው ኼጁኩቲ ነበር፡፡ በሃገሪቱ (ብሪታኒያ) ተጫዋቾች የሚጫወቱበት የሜዳ ክፍሎች (Positions) በሚለብሷቸው የመለያ ቁጥሮች መሰረት እየተወሰነ የሚያድጉበት የከረመ ልማድ ይስተዋላል፡፡ (7) – የቀኝ መስመር አማካይ (Right Winger) ሆኖ ከተጋጣሚ የግራ መስመር ተከላካይ (3) ጋር ይፋጠጣል፤ (5) – የመሃል ተከላካይ አማካይ (Center-Half) ደግሞ የተቃራኒ ቡድን የመሃል አጥቂ (9) ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርግበታል፤ በቃ ይህ መሰረታዊው ንድፍ ነበር፡፡ በቴሌቪዥን የጨዋታ ቀጥታ ስርጭት አስተላላፊ የነበረው ኬኔዝ ዎልስተንሆልም በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች የውጭ ሃገራቱን የአሰላለፍ ባህል ለተመልካቾች ለማስረዳት ተገዶ ነበር፡፡ ” በተወሰኑት ሃንጋሪያውያን ተጫዋቾች የመለያ ቁጥር ግራ ልትጋቡ ትችላላችሁ፤ እነርሱ (ሃንጋሪያውያኑ) በምክንያታዊነት ለመሃል ተከላካይ አማካያቸው (Center-Half) 3-ቁጥር ፣ ለመስመር ተከላካዮቻቸው ደግሞ 2-ቁጥር እና 4-ቁጥር የሰፈረባቸውን መለያዎች ያለብሷቸዋል፡፡” እያለ የብስጩነት ስሜት የሚንጸባረቅበት ቃና ባለው ድምጸት ገለጸላቸው፡፡ በእርግጥም ሃንጋሪዎች አሃዞችን በተጫዋቾች መለያ ላይ ሲያሰፍሩ የሜዳውን ስፋት (Across-the-Pitch) መሰረት አድርገው እንጂ ጊዜ ያለፈበትን የሜዳ ርዝመት የመጠቀም ልማድ አልነበረም፡፡ ታዲያ እንግሊዛውያኑ ይህን ያልተለመደ አሰላለፍ እንዴት ይቋቋሙት? ከጉዳዩ ጋር የሚያያዘው ሌላው ጥያቄ ደግሞ የባላጋራ ቡድን የመሃል አጥቂ (Centre-Forward) ወደ ሜዳው አጋማሽ ተጠግቶ የሚጫወት ከሆነ የመሃል ተከላካይ- አማካዩ (Center-Half) ኃላፊነት ምን ሊሆን ነው? በዚያን ዕለት በመሃል-ተከላካይ አማካይነት ሚና የተሰለፈው ሃሪ ጆንስተን ግለ-ታሪኩ ላይ እንደጻፈው ” እንደ እኔ ከሆነ ከሁሉ የሚያሳዝነው ከፍተኛ የሆነው ልፍስፍስነታችን ነበር፡፡ በአሰቃቂነት የሚፈረጀው አቋማችንን ለማረቅ ምንም ማድረግ አለመቻላችን ደግሞ የከፋ ችግር ውስጥ ከተተን፡፡” ብሏል፡፡ በመሃል ተከላካይነት እና በመሃል አማካይነት ሚናዎች መካከል የሚዋልል እንቅስቃሴ የሚያደርገው የመሃል- ተከላካይ አማካዩ (Center-Half) የተጋጣሚውን የመሃል አጥቂ (Centre-Forward) የሚከታተል ከሆነ በሁለቱ የመስመር ተከላካዮች (Full Backs) መሃል ሰፊ ክፍተት ይፈጠራል፤ ያን ማድረግ ትቶ በቦታው ላይ ብቻ የተገደበ እንቅስቃሴ ካደረገ ደግሞ ኼጁኩቲ እንደፈለገ በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ጨዋታውን የመቆጣጠር እድል ያገኛል፡፡ በመጨረሻም ጆንስተን በመስመር ተከላካዮቹ መሃከል መገኘትን መረጠ፤ ኼጁኩቲም ሶስት ግቦችን አስቆጠረ፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ የመልሱ ጨዋታ በቡዳፔስት ሲደረግ ጆንስተንን የተካው ሲድ ኦዌንም የተለየ አስተዋፅኦ አላበረከተም፤ እንግሊዝም 7-1 ከመረታት አልተረፈችም፡፡
እንግሊዞችን ድንግርግር እንዲሉ ያደረጋቸው ኼጁኩቲ ብቻ አልነበረም፡፡ አጠቃለይ የቡድኑ የአጨዋወት ስርዓት (Whole System) እና የአቀራረብ ዘይቤ (Playing Style) ለብሪታኒያውያን እንግዳ ነበር፡፡ ኦዌን ይህን ልዩነት ሲያስረዳ ” ከሃንጋሪዎች ጋር መፋለም ከሌላ ዓለም ከመጡ አካላት ጋር እንደመጫወት ሊታይ ይችላል፡፡” ብሏል፡፡ የዚያኔው የእንግሊዞች አምበል ቢሊ ራይትም ” በእግርኳስ ሃንጋሪያውያን የደረሱበትን የእድገት ከፍታ ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ሁኔታ ቦታ አልሰጠነውም፤ የለውጡን ዋጋም ዝቅ አድርገን ተመለከትነዋል፡፡” ሲል ስህተታቸውን አምኗል፡፡ እንግዲህ ይህ ምስክርነት በወቅቱ የነበረውን የእንግሊዝ እግርኳስ አጠቃላይ የቴክኒክ ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ እንዲያውም ፑሽካሽ ተጫዋቾችን እያሞኘ በርካታ አብዶዎችን በመስራት የሚመታ እያስመሰለ በግዴለሽነት ግቦችን በማምከኑ ዎልስተንሆልም ደስተኛ የነበረ ይመስላል፡፡ እንግዲህ ያ ድርጊት ዘመናዊውን የእንግሊዝ እግርኳስ አከርካሪ በፍርሃት የሚያርድ መልዕክት ካላው ፍራንክ ኮልስ በጨዋታው ማግስት <ዴይሊ ቴሌግራፍ> ላይ የጻፈው ምንም ሊባልለት የማይችል ነጥብ ይሆናል፡፡ ” አስደናቂዎቹን የሃንጋሪ እግርኳስ ጥበበኞች በሃይለኞቹ ኳስ ነጣቂዎቻችን (Tacklers) መቆጣጠር ይቻል ነበር፡፡” ሁኔታው ብዙም ግርምት ያልፈጠረበት ብሪያን ግላንቪል ሽንፈቱን ” ሽንፈቱ ማየት የተሳነንን ነገር እንድናስተውል ያደረገ ክስተት ነበር፡፡” ሲል በበጎ ጎን ተመለከተው፡፡
ችግሩ ከቴክኒካዊ ክህሎት ማነስ ጋር ብቻ የተያያዘ አልነበረም፡፡ ግቡም ለተፈጥሮአዊ የተጫዋቾች ችሎታ ቅድሚያ የመስጠት ጉዳይን አይመለከትም፡፡ በእርግጥ ሃንጋሪ የዚያን ዘመን አምስት የዓለም ታላላቅ ተጫዋቾችን ፑሽካሽ፣ ኼጁኩቲ፣ ኮዚስ፣ ቦዚክና ዞልታን ዚቦር እንዲሁም አነሳሹ እና ጥንቁቁ አሰልጣኝ ጉስታቭ ሴቤዝን ይዛ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የቡድኑ ቀኝ መስመር ተከላካይ ጄኖ ቡዛንስኪ ” ሃንጋሪ ያሸንፈችበት አይነተኛ ምክንያት የታክቲክ ብልጫ በመውሰዷ ነበር፡፡ ጨዋታው የሁለት ፎርሜሽኖች ፍልሚያ ታይቶበታል፤ እንደተለመደው አዲሱና ይበልጡን እድገት ያሳየው ቅርጽ የበላይነትን ወስዷል፡፡” ሲል አውስቷል፡፡
ምናልባት ሁለቱን (ታክቲክና ቴክኒክን) ነጣጥሎ ለማየት መሞከር ተገቢ አይሆንም፤ ምክንያቱም ቴክኒካዊ ክህሎት እንዲዳብር ታክቲክ የራሱ የሆነ ድርሻ ይኖረዋል፤ ያለ ቴክኒክ ድጋፍም ታክቲክ ፋይዳቢስና የድግግሞሽ ጉዳይ ሆኖ ይቀራል፡፡ እንግሊዞች ሜዳ ላይ በሃንጋሪዎች አማካኝነት ይደርስባቸው ለነበረው ችግር ምላሽ ለመስጠት ዝግመት ተስተውሎባቸዋል፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ በቡዳፔስት በተካሄደው የመልሱ ግጥሚያም በተጋጣሚያቸው ለሚደርስባቸው ጫና መፍትሄ ለመፈለግ ፍጹም ቸልተኝነት አሳይተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አሰልጣኝ ዋልተር ዊንተርቦተም በዕለቱ አዋጭ ያልሆነ ታክቲክ መርጧል ብሎ መሟገት የሚቻል አይመስልም፤ ምክንያቱም ችግሩ ስር ሰዶ የቆየና በመላ ሃገሪቱ የተንሰራፋ (Endemic Problem) ነበር፡፡
በጨዋታው ማግስት ጂኦፍሪይ ግሪን በ<ዘ-ታይምስ> ላይ እንደጻፈው ” እንግሊዞች ባልለመዱት ዓለም ላይ ራሳቸውን ባይተዋር ሆነው አገኙት፡፡ ቀይና የሚያደነጋግር ዓለም! የሃንጋሪ ተጫዋቾች ደመቅ ያለ መለያቸውን ለብሰው አስገራሚ ክህሎት እያሳዩ በአውዳሚ ፍጥነት ድንቅ የአጨራረስ ብቃታቸውን የሚተገብሩበት ሒደት ልዩ ነበር፡፡ አንዳንዶች አዲሱ የእግርኳስ አጨዋወት ሃሳብ ከአህጉራዊው እና ደቡብ አሜሪካኖቹ ሃገራት ፍልስፍና ጋር ተማክሎ እድገት ያሳየ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ይህን የጨዋታ ዘይቤ በሚመለከት ዘወትር የሚቀርበው ትችት ‘በተጋጣሚ የግብ ክልል ዙሪያ ጠንካራ የመጨረሻ ምት አይተገበርበትም፡፡’ የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ይህ አስተያየት የሚሰጠው አልፎ አልፎም ነው፡፡ ምናልባት ‘እንከን የለሹ የእግርኳስ አጨዋወት መንገድ ጠንካራ ምቶችን (Hard-Hitting) በሚተገብረው ክፍቱ የእንግሊዛውያን ዘዴ እና የተደራጀ የመከላከል መዋቅርን ሰብሮ ለማስከፈት ጥረት በሚያደርገው ስልት መካከል ይገኛል፡፡’ የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ በትናንትናው ዕለት ሃንጋሪዎች በሚያስገርም የቡድን ስራ ይህን በፍልስፍና ጽንፎች መካከል የሚገኝ የጨዋታ አይነት (Mid-Point) ምሉዕና ፍጹም አደረጉት፡፡” አለ፡፡
ጉስታቭ ሴቤዝ ግን ቡድኑን በአጨዋወት ስርዓት መሃል ሰፋሪነት ሊመለከት አልፈቀደም፡፡ ከጦርነቱ በፊት በፓሪስ የሪኖ መኪኖች ማምረቻን የላብ አደሮች አመጽ ስላደራጀ የመደብ አልባ ስርዓተ ማኅበር ሹመኝነቱ (Communist Credential) እንከን አልባ ነበር፡፡ አንዳንዴ አሰልጣኙ የሃገሪቱ መንግስት ሊሰማ የሚሻውን ጉዳይ የእርግጠኝነት ስሜት በተሞላበት መንፈስ ሲናገር ሃንጋሪ ስኬታማ እንድትሆን ስለሚተጋ የራሱን አስተያየት እየሰነዘረ አይደለም ብሎ ለማመን መወሰን ተገቢ አይሆንም፡፡ በግልጽ እንደሚታየው በብሄራዊ ቡድኑ ስር የሰደደው የኅብረት አጨዋወት በግል ተጫዋቾች ብቃት ላይ ጥገኛ ከነበረው የእንግሊዞች አቀራረብ ይልቅ ውጤታማ መሆኑ የሶሻሊዝም ፖለቲካዊ ርዕዮተ-ዓለም ድል ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ የታላቋ ግዛት ታሪካዊ ሽንፈት (Symbolic Defeat) የገዘፈ እግርኳሳዊ ውድቀት ጅማሮ መሆኑን የሚያሳስብ ምናባዊ ስጋት እንኳ አለመጫሩ ግርምት ይፈጥራል፡፡
ይቀጥላል...
ስለ ደራሲው
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡
–Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)
–Sunderland: A Club Transformed (2007)
–Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)
–The Anatomy of England (2010)
–Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)
–The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)
–The Anatomy of Liverpool (2013)
–Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)
–The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)