” በቀጣይ በፕሪምየር ሊጉ የተጋነነ ነገር አናስብም” የሰበታ ከተማ አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከተከታዩ ለገጣፎ ለገዳዲ ጋር በዕለት እሁድ ከሜዳው ውጪ ባደረገው ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተለያይቶ አንድ ጨዋታ እየቀረው አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ወደ 2012 ፕሪምየር ሊግ ማደጉን ማረጋገጡ ይታወሳል። ይህን ቡድን በአጭር ጊዜ ውስጥ በመረከብ ለውጤት ያበቁት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ስለ ቡድናቸው ስኬት እና ቀጣይ ጉዞ አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

” የውድድር ዓመቱ ከባድ ነበር”

” የውድድር ዓመቱ ለእኛ ከባድ ነበር። በክረምት ወራት የቅድመ ውድድር ዝግጅታችንን ከጀመርን ጊዜ ጀምሮ ተጫዋቾቼ ሰበታን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማስገባት በቁርጠኝነት ነበር የተነሱት። እንዳያችሁት በሙሉ በላባችን ይህን ውጤት ማሳካት የቻልነው። ምንም የተፈጠረ ሌላ ነገር የለም። ዘንድሮ በምድባችን ባደረግነው የዙር ጨዋታዎች በአንድም ጨዋታ ሽንፈት አላስተናገድም። ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ በሚደረግ ጉዞ ከዚህ ቀደም ይህን ያሳካ የለም። እኛ የመጀመርያዎቹ ነን። በዚህም ደስተኛ ነን። ዛሬም (እሁድ) እንዳያችሁት ይህ ጨዋታ ለእኛ ወሳኝ በመሆኑ ሌላውን ከምንጠብቅ እዚሁ ጨርሰን መሄድ አለብን ብለን ነው የመጣነው። ይሄም ተሳክቶልናል። በአጠቃላይ የዘንድሮ ዓመት ውጤት ከሚገባው በላይ ለእኛ ይገባናል ብዬ ነው የማስበው።

” ወደ ታች ወርዶ መልፋት ያስፈልጋል…”

አዎ ከዚህ ቀደም አየር ኃይልን ከታች ወደ ፕሪምየር ሊጉ አሳድጌያለው። ጅማ አባ ጅፋርም ቢሆን አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሰርቻለው። ቡድኑ በምድቡ በሰፊ የነጥብ ልዩነት እየመራ ነው በቤተሰብ ምክንያት የወጣሁት። ይህ ማለት ጅማ አባጅፋር ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ ጨርሻለው ማለት ይቻላል። ሰበታ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያስገባሁት ሦስተኛ ክለቤ ነው እንግዲህ። ምንድነው ታች ወርዶ መልፋት ጥሩ ነው። ብዙ ጊዜ በእኛ አሰልጣኞች ዘንድ መገዝገዝ የሚባል ነገር አለ። ቡድን ሰርተህ ፣ አዘጋጅተህ እና ለፍተህ ወደ ውጤት እያመራህ ስራህን ሳትጨርስ አንተ እንድትሰናበት ወይም እንድትፈናቀል የተለያዩ ነገሮች ይደረጋሉ። የክለብ አመራሮች እና የኮሚቴ አባላትን በመያዝ አንተን አስወጥተው ለመግባት የሚያስቡ አሉ፤ ይህ አያዋጣም። ታች ወርዶ ለፍቶ መስራት ያስፈልጋል። ስለዚህ እንደኔ ወደ ታች በመውረድ ለፍቶ ቡድን አደራጅቶ ለውጤት መብቃት ይሻላል። እንደሚታወቀው እኔ በኢትዮጵያ ቡና ነው የምታወቀው። ከዛም በኃላ ታች ወርጄ በተለያዩ ክለቦች ሰርቻለው። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ። ዛሬም ሰበታን ወደ ፕሪምየር ሊጉ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊጉ በመመለሴ እጅግ በጣም ተደስቻለው። ለዚህም ከጎኔ በመሆን ድጋፍ በማድረግ ለተባበሩኝ ለከተማው አስተዳደር ኃላፊዎች፣ ለክለቡ አመራሮች ፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎቻችን ከልብ ላመሰግን እወዳለው።

” በፕሪምየር ሊጉ የተጋነነ ነገር አናስብም”

ሰበታን ስረከብ ባዶ ቡድን ነበር። ይህ ቡድን በዘጠኝ ወር የተሰራ ጠንካራ ቡድን ነው። እንግዲህ በቀጣይ በፕሪምየር ሊጉ ውስጥ የተጋነነ ነገር አናስብም። ከፍተኛ ሊግ ላይ በርካታ ወጣት ተጫዋቾች አሉ። አሁን የሰራነውን ቡድን እንዳያችሁት ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አሉበት። የተወሰኑ ክፍተቶች ላይ ልምድ ያላቸው እና ወጣት ተጫዋቾችን አሰባስበን ፕሪምየር ሊጉ ላይ ላለመውረድ ሳይሆን ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ የሚጨርስ ውጤታማ የሆነ ቡድን ይዘን እንቀርባለን።

ካስፈለገዎ: ሰበታ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን አረጋግጧል


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡