የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም 24ኛ ሳምንት መሰናዶ በታላቁ የሀንጋሪ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጉስታቭ ሴቤዝ ላይ አተኩሮ እንዲህ ይቀርባል ።
|| ክፍል 23 | LINK |
እግርኳስ ጥቁር ሰሌዳ ላይ በሚተነተኑ ንድፈ ሐሳባዊና ምናባዊ ምሪቶች ብቻ የሚከወን ጨዋታ አለመሆኑ እሙን ነው፡፡ የሜዳ ላይ ስኬት በተጫዋቾች የብቃት ጀረጃ እና ኅልዮታዊ መርሆዎች (Theoretical Principles) መካከል የሚፈጠር የወል አዎንታዊ መስተጋብርን ይሻል፡፡ ለአብነት ያህል የማርቲን ቡኮቪ ቀዳሚ የአጨዋወት ጽንሰ ሐሳብ ለሃንጋሪዎች ምቹ ነበር፡፡ አራት የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Four Front Men) እና ወደኋላ አፈግፍጎ የሚጫወት አጥቂ (Withdrawn Centre-Forward) የሚያካተው የማርቲን <ሲስተም> የማጥቃት ዑደቱን ፍሰት (Attacking Fluidity) መጠበቅ ስለሚያስችልና ለአጥቂዎቹ እግርኳሳዊ አመለካከት ተስማሚ ሆኖ ስለተገኘ የአሰልጣኙ እቅድና የተጫዋቾቹ ውህደት አመርቂ ህብር ፈጠረ፡፡ አሁን ላይ ሆኖ እንኳ የዚያን ግጥሚያ ቪዲዮ ማየት ለዎልስተንሆልም (ያኔ የእንግሊዝ አሰልጣኝ የነበረ፡፡) አስገራሚ ስሜት ይጭርበታል፡፡ የጨዋታውን የመጀመሪያ አጋማሽ ሲቃኘው የደስታና የመደነቅ ቃና ባለው ድምጸት ” ይገርማል’ኮ! የግራ መስመር አጥቂው (Outside Left) ዚቦር በፍጥነት በተቃራኒው መስመር (Outside Right) ይመጣና ኳስ ይቀበላል!” ይላል፡፡
በተጫዋቾች መካከል ያልተቆራረጡ፣ የተሳኩና አላማ ያላቸው ቅብብሎች እየተደረጉ የጨዋታው ፍሰት ተጠብቆ በዘላቂነት የሚከወንበት ሒደት (Fluidity) መሰረታዊ የእግርኳስ ግብዓት ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ቡድን ይበልጡን የሚዋልል መዋቅራዊ መልክ በያዘ ቁጥር የመከላከል አደረጃጀት ቅርጹን (Defensive Structure) ማስጠበቅ አዳጋች እየሆነበት ይሄዳል፤ በዚህ ምክንያት እጅግ አስፈላጊ የሆነው ይህ የጨዋታ ሒደት (Defending Phase) ለተጋጣሚ በቀላሉ ተጋላጭ የመሆን እክል ይጋረጥበታል፡፡ በእነዚያ ዓመታት ለዚህ ውስብስብ የታክቲክ ችግር የጉስታቭ ሴቤዝን ያህል መፍትሄ በማበጀት በኩል የተጋ አሰልጣኝ አልተገኘም ፤ የላቀ አዕምሯዊ ክህሎቱን የተጠቀመውም ይሄኔ ነበር፡፡ አሰልጣኙ ቡድኑን ክብደት ባላቸው እንግሊዝ-ስሪት ኳሶች ከማሰልጠን አንስቶ ልምምድ የሚሰሩበትን የሜዳ ርዝመትና ወርድ ልኬት ከዌምብሌይ ስፋት እኩል እንዲሆን እስከማድረግ የሚደርሱ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለማናቸውም ጥቃቅን ዝርዝሮች (Details) ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን አዘወተረ፡፡
ሴቤዝ በእግርኳስ ታክቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጣም ጥንቁቅ እንደነበር በወቅቱ የሚጠቀምባቸው ማስታወሻ ደብተሮቹ ላይ የሰፈሩ ጽሁፎችና ምስሎች ያሳያሉ፡፡ ቡዛንስኪና ሚኻይል ላንቶስ የተባሉት ሁለት የመስመር ተከላካዮች (Full-Backs) ወደፊት እየተጠጉ እንዲጫወቱ ሲደረጉ በቡድኑ የመሃል ተከላካይ-አማካይነት (Center-Half) የሚያገለግለው ጊዩላ ሎራን ደግሞ በጥልቀት ወደኋላ እንዲመለስ ይታዘዛል፤ የተጫዋቹ ሚና በአሰልጣኝ ካርል ራፕን አማካይነት በተጸነሰውና በጥብቁ የመከላከል አጨዋወት ስርዓት (Verrou System) ውስጥ ከአራቱ ተከላካዮች አንደኛው ወደኋላ አፈግፍጎ በመቆም ከሌሎቹ የኋላ መስመር ተሰላፊዎች አልፈው የሚመጡ ኳሳችን እንዲያጸዳ ኃላፊነት ከተጣለበት የመጨረሻው “ጠራጊ” ተከላካይ (Sweeper) ጋር ተመሳሳይነት ነበረው፡፡ ፌሬኔክ ፑሽካሽ ሜዳ ላይ እንደፈለገ የመዟዟር ነጻነት ተሰጠው፤ በወረቀት ሲታይ የቀኝ መስመር አማካይ (Right-Half) የሚመስለው ቦዚክ ደግሞ ሌሎቹን አጥቂዎች በእንቅስቃሴ ወደፊት እየገፋቸው ለኼጁኩቲ ድጋፍ እንዲያደርጉ መትጋቱ ተወደሰለት፡፡ ታዲያ ይህ የማጥቃት ስርዓት በጠንካራ የመከላከል አጨዋወት መታገዝ ነበረበት፡፡ ሴቤዝ ለጨዋታው (እንግሊዝ-ከ-ሃንጋሪ) ያዘጋጀውን ታክቲካዊ እቅድ የነደፈበት አጀንዳ ላይ እንደሚታየው የግራ መስመር አማካዩ (Left-Half) ዘካሪያስ እጅጉን ወደኋላ በመሳብ በሁለቱ የመስመር ተከላካዮች መሃል ሆኖ ይስተዋላል፡፡ ሁለት የመስመር ተከላካዮች (Full- Backs) ፣ ሁለት በጥልቀት ወደኋላ ያፈገፈጉ የመሃል-ተከላካይ አማካዮች (Defensive Centrals) ፣ መሃለኛውን የሜዳ ክፍል የሚቆጣጠሩ ሁለት ተጫዋቾች (Players Running the Middle) እና አራት የፊት መስመር ተሰላፊዎችን (Four up Front) የያዘው የሃንጋሪያኑ <ሲስተም> ለ4-2-4 ፎርሜሽን እጅጉን የቀረበ ሆኖ ታየ፡፡
የ<አራኒሳፓት/Aranycsapat> ቡድን እስካሁን ድረስ በእግርኳስ አጥጋቢ ስኬት ሳያስመዘግብ ብዙ ዘመን ተጓዘ፤ የውጤታማነት ገድ እንደራቃውም ቀረ፡፡ ከዚያ ቀደም ለሰላሳ ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሳይረቱ ከርመው በ1954ቱ የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ምዕራብ ጀርመንን በሁለት ጎሎች ልዩነት ይመሩ የነበሩበትን አጋጣሚ አሳልፈው ሰጡ፤ እድል ፊቷን አዞረችባቸው፡፡ ቅብብሎች ላይ የተመረኮዘ አጨዋወታቸውን (Passing Game) የሚያሰናክል ጭቃማ ሜዳ፣ በእግርኳስ የደረሱበት ደረጃ የፈጠረባቸው የመታበይ ስሜት (Touch of Complacency)፣ የጀርመኑ አሰልጣኝ ሴፕ ሄርበርገር ተጫዋችን-በ-ተጫዋች የማስያዝ ዘዴ (Man-To-Man Marking) በመጠቀም ሆርስት ኤክል በቀላሉ ኼጁኪቲን እንዲቆጣጠረው ማድረጉ እና ገደ-ቢሱ እጣ ፋንታቸው ተደማምሮ በመጨረሻ 3-2 ተሸነፉ፡፡ የመሃል አጥቂን ሰውን-በ-ሰው በመያዝ ጥብቅ ቁጥጥር ሥር (Man Marking System) ከሚያደርጉ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች (Markers) ተጽዕኖ ነጻ ለማድረግ የተዘየደው መላ እነዚህ ተጫዋቾች ከአጥቂው በቅርብ ርቀት ሆነው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ አልበጅ አለ፡፡
በእርግጥ ሃንጋሪዎች በመከላከል ድክመታቸውም ዋጋ ከፍለዋል፤ በወቅቱ በእግርኳስ የማጥቃት ሒደት የላቀ ብቃት ቢያሳዩም የሃንጋሪያውያኑ ተከላካይ ክፍል ስስ (Porous) ነበር፡፡ ጀርመናውያኑ ያስቆጠሩባቸው ሦስት ግቦች በውድድሩ በአጠቃላይ የገባባቸውን የጎል መጠን አስር ያደርሰዋል፡፡ በ1953ም እንዲሁ በዌምብሌይ 6-3 የተጠናቀቀውን ግጥሚያ ጨምሮ በስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች አስራ አንድ ጎሎች አስተናግደዋል፡፡ በጊዜው የሃንጋሪን ሃያልነት ከግንዛቤ በማስገባት ብዙ ሰው እንግሊዞች ከጨዋታው ያገኟቸው ሶስት ግቦች እንዳኩራራቸው ቢስማማም ከሃንጋሪ የወረደ የመከላከል ብቃት አንጻር በሜዳቸው ከዚያም የበለጡ ጎሎችን ለማግኘት አለመጣራቸው በዝንጉነት ከመተቸት አላዳናቸውም፡፡
ሶስት የመሃል ተከላካዮችን (Three at the back) በሚጠቀም ቡድን ውስጥ የተከላካይ ክፍሉ በሜዳው ቁመት የቀኝ አልያም የግራውን መስመር የእንቅስቃሴ ሽክርክሪት ማዕከል (Pivot) አድርጎ ለመውሰድ ይገደዳል፡፡ ተጋጣሚ ቡድን የማጥቃት ጨዋታውን በቀኝ መስመር የመተግበር አዝማሚያ ካሳየ የግራ መስመር ተከላካዩ (Left-Back) ወደ ቀኝ ጎኑ ጠለቅ ይልና ከመሃል ተከላካዩ (Center-Back) ጋር በመሆን የተቃራኒ ቡድን ጥቃትን የመመከት ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ ባላጋራ የማጥቃቱን ሒደት በግራ መስመር የሚያስኬድ ከሆነም የቀኝ መስመር ተከላካዩ (Right-Back) ወደ መሃል ተከላካዩ ተጠግቶ ተመሳሳዩን ሚና ይወጣል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ የማጥቃት ሒደቱ ከሚከናወንበት መስመር (Attacking Line) በተቃራኒው አቅጣጫ (Opposite Flank) ለሚሰለፈው የመስመር አማካይ (Winger) ረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶችን እንዲጠቀም የሚያስችል ሰፊ የመሮጫ ክፍተት (Acceleration Room) ይፈጥርለታል፡፡ በታሪካዊው ጨዋታ በተለምዶ አማካይ እንደሆነ የሚታሰበው የሃንጋሪው ዘካሪያስ ከጎኑ የሚገኘው የመስመር ተከላካይ (ላንቶስ) ፊትለፊቱ የሚጋፈጠውንና ጥብቅ ቁጥጥር እንዲያደርግበት የሚጠበቅበትን የተጋጣሚ የመስመር አማካይ በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ በቂ ከለላ መስጠት የሚያስችለው ርቀት ድረስ ወደኋላ ተስቦ አልተጫወተም፤ ይህም ሌላ የመከላከል ህጸጽ ነበር፡፡
ሃገሪቱ በርን (የፍጻሜው ጨዋታ የተካሄደበት የሲውዘርላንድ ከተማ) ላይ ለደረሰባት ሽንፈት የሚጠቀሱት ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም የሃንጋሪያውያን አጸፋ ግን ቁጭትና የኃይል እርምጃ ሆኖ አረፈው፡፡ እንግሊዝን በዌምብሌይ ድል አድርገው ሲመለሱ አራኒካፓቶች በአድናቂዎቻቸው የደመቀ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በዓለም ዋንጫው የፍጻሜ ጨዋታ ከተሸነፉ በኋላ ግን ወደ ሃገራቸው ሲገቡ የመንገድ ላይ ህዝባዊ ቁጣን ለመሸሽ ሲሉ በሰሜናዊ የሃንጋሪ ከተማ <ታታ> በኩል ማለፍ ተጠበቀባቸው፡፡ በሊግ ጨዋታዎች ፑሽካሽ ላይ ደጋፊዎች ከፍተኛ የተቃውሞ ጩኸት ያሰሙ ጀመር፤ የሴቤዝ ልጅም ትምህርት ቤት ውስጥ ተደበደበ፤ ግብ ጠባቂው ጉይላ ግሮሲስ ደግሞ ታገተ፡፡ በ1955 ሴቤዝ የመሰረተው የአመራር ቡድን ፈረሰ፤ አባላቱም ተበተኑ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በቤልጂየም 4-3 መሸነፋቸውን ተከትሎም ከሃላፊነቱ እንዲነሳ ተደረገ፤ በቡኮቪ የሚመራና አምስት የኮሚቴ አባላት ያሉት የአሰልጣኞች ቡድንም የሴቤዝን ወንበር ተረከበ፡፡ በሃገሪቱ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ ሲፋፋም በርካታ ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ሃገራት መኮብለል ጀመሩ፡፡ ይህም የቡኮቪን ሃላፊነት ይበልጡን አከበደው፡፡ ሴቤዝ ለጥቂት ጊዜያትም ቢሆን በብሔራዊ የሰውነት ማጎልመሻ እና ስፖርት ማህበር መስሪያ ቤት ውስጥ በስፖርት አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሹም ሆኖ ሰራ፤ ከዚያም በተለያዩ ቦታዎች የአሰልጣኝነት ህይወት መግፋቱን ተያያዘው፤ በመጨረሻም በ1970 ራሱን ከስልጠናው ዓለም በጡረታ መልክ አገለለ፡፡ ” ልጅ ሆኜ ሴቤዝ በቡዳፔስት ከተማ በምኖርበት አካባቢ ይኖር ነበር፡፡ ከጓደኞቼ ጋር እግርኳስ ወደምንጫወትበት ሜዳ እየመጣ ይመለከተናል፤ ወደ መኖሪያ አፓርትመንቱ ይወስደንና ሳንድዊች ይመግበናል፤ ከዚያም የ6-3 እና 7-1 ድሎችን የሚያስታውሱ የ<ሱፐር-8> ፊልሞች ያሳየናል፡፡ ለፌሬንካቮርስ ስለ እኔ ጥሩ ምስክርነት በመስጠት የክለቡ አባል እንድሆን ጥሯል፡፡ ልክ እንደ አያቴ አየው ነበር ፡፡ ሙሉ ህይወቱን የኖረውም ለእግርኳስ ነው፡፡” ይላል የ1970ዎቹ የ<ፌሬንካቮርስ> ክለብ ታላቁ አጥቂ ቲቦር ኒላሲ ስለ ሴቤዝ ሲያወሳ፡፡
ይቀጥላል...
ስለ ደራሲው
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡
–Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)
–Sunderland: A Club Transformed (2007)
–Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)
–The Anatomy of England (2010)
–Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)
–The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)
–The Anatomy of Liverpool (2013)
–Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)
–The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)