ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ ስድስት – ክፍል ሦስት)

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም 24ኛ ሳምንት መሰናዶ በታላቁ የሀንጋሪያዊ ቤላ ጉትማን መሳጭ ታሪክ ላይ ያጠነጥናል ።

|| ክፍል 23 LINK

በ1950ዎቹ የብዙሃኑን ቀልብ የሳበው የሃንጋሪ ብሄራዊ ቡድን ጀብዱ ቢሆንም ጨዋታው ላይ ዘላቂ ተጽዕኖ በማሳደር ረገድ ግን የጉስታቭ ሴቤዝ የሃገር ልጅ የነበረው ቤላ ጉትማን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ጉትማን ለብራዚላውያን እግርኳስን በማስተዋወቅ ቀዳሚው ሰው እንደሆነ መመስከር ምናልባት የአሰልጣኙን አበርክቶ ማጋነን ሊሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ ሰውየው በሃገሪቱ የአጨዋወት ባህል የራሱን አሻራ ከማሳረፍ ወደኋላ ብሎ አለማወቁ እርግጥ ነው፡፡ ከአወዛጋቢ የህይወቱ ምዕራፍ ጀርባ በማዕከላዊ አውሮፓ ታላቁ የእግርኳስ ዘመን ጉትማን የመጨረሻውን ወርቃማ ጊዜ ይወክላል፡፡ ቤላ የልሂቃን ውይይትና ክርክር ከሚደረግባቸው ቡና-መጠጫ ቤቶች ከተገኙ የመጨረሻዎቹ አሰልጣኞችም (Coffe-House Coaches) አንዱ ነበር፡፡ ታክቲካዊ ገራገርነት ዋጋ በሚያስከፍልበት ወቅት እንኳ ስለ ንጹሁ የእግርኳስ አቀራረብ  ስልት ጥብቅና በመቆም ከሚጠቀሱ እግርኳሰኞች መካከልም የመጨረሻው ሳይሆን አይቀርም።

በእነዚያ ዘመናት ሁለቱ ታላላቅ ሃንጋሪያውያን አሰልጣኞች መጠነኛ የባህሪ ልዩነቶች ታይቶባቸዋል፡፡ ሴቤዝ ጽኑ የመደብ አልባ ስርዓተ-ማህበር አቀንቃኝ (Socialist) ነበር። ስለሚደግፈው የፖለቲካ ፓርቲ ፖሊሲ፣ መርህና ፕሮግራም አደባባይ ላይ በወኔ ለመናገር ለአንዴ እንኳ በማያመነታና በማያወላውል ብርቱ አቋሙ የበርካቶችን ይሁንታ አትርፏል፤ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችም ከፍተኛ ዋጋ የመስጠት አዝማሚያ ተስተውሎበታል፡፡ በተጻራሪው ጉትማን ግልፍተኛና በራሱ አመለካከት ብቻ የሚመራ ሰው (Individualist) ነበር። በዙሪያ ገባው ሁሉ እየተማረረ፣ የመንግስት ባለስልጣናትን በጥርጣሬ እያየ እና ችላ የመባል ስሜት እየተሰማው ኖሯል፡፡ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለሃንጋሪ ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ ካደረገ በኋላ ከቡድኑ እንዲገለል የተደረሰበት ውሳኔም ተጫዋቹ ላይ ሲደረግ ለነበረው ጫና ማሳያ ይሆናል፡፡

ለ1924ቱ የፓሪስ ኦሊምፒክ ሲመረጥ በብሄራዊ ቡድኑ የጠበቀው በቂ ያልነበረ ዝግጅት አስቆጣው፤ ሃገሪቱ ለውድድሩ ከላከችው አጠቃላይ የልዑካን ቡድን ውስጥ ከተጫዋቾቹ ቁጥር ይልቅ የመደበኛ ሰራተኞቹ መጠን ልቆ መገኘቱም ከነከነው፡፡ የሃገሪቱ ታዋቂ የፖለቲካ ፓርቲም ሞንማትረ (Montmartre) አጠገብ በሚገኝ ሆቴል አረፈ፤ ቦታው በፈረንሳይዋ መዲና ዝነኛ የሆነ የኪነ ጥበብ ሰዎች መናኸሪያ ነበር፡፡ ስፍራው የሶሻሊስት ፓርቲው አባላት ርዕዮተ-ዓለማዊ ውይይቶችን እንዲያደርጉ አመቺ ድባብ ፈጠረላቸው፡፡ ነገርግን የካድሬዎቹ ጭውውትና ክርክር ለመተኛት የሚዘገጃጁትን ተጫዋቾች ምቾት ነሳቸው፤ በዚህ ድርጊት የተበሳጨው ጉትማን የቡድን አጋሮቹን አስተባብሮ ለተቃውሞ ተነሳ፤ በሆቴሉ ውስጥም አይጦችን የማጥመድ ዘመቻ ለማድረግ ወጠነ፤ ከዚያም የታደኑትን አይጦች ጭራ በገመድ እያሰረ የፓርቲው መኮንኖች የመሰብሰቢያ ክፍላቸው የበር መክፈቻ ላይ ማንጠልጠል ጀመረ፡፡ እናም ድርጊቱ በማን መሪነት እንደተካሄደ ከታወቀ በኋላ ጉትማን ለሃገሩ በድጋሚ መጫወት አልቻለም፡፡ ቤላ ለብዙ ጊዜ ሌሎችን ሊያበሳጭ የሚችል ነገር ከማድረግ የማይታቀብ፣ ዘወትር ሁከት የሚከታተለው፣ ሁሌም ትኩረት ተነፍጎት የሚታይ፣ በንዴት የሚጦፍበት ምክንያት የማያጣው፣… በአጠቃላይ ይህች ዓለም ፊቷን ያዞረችበት ባይተዋር ሆኖ መኖርን ተላመደ።

ቤላ ጉትማን የተወለደው በ1899 በቡዳፔስት ከውዝዋዜ አሰልጣኝ ቤተሰቦቹ ሲሆን ገና በአስራ ስድስት ዓመቱ የባህላዊ ጭፈራዎች መምህር ለመሆን ችሏል፡፡ እንዲያም ሆኖ የእግርኳስን ያህል ለልቡ ሃሴት የሚሰጠው ነገር አልነበረም፡፡ በቀደሙት የእግርኳስ ዘመናት ማጥቃት ላይ የሚያመዝን የተከላካይ አማካይ (Old-School Attaking Center-Half) ሆኖ እንደተጫወተ የሚያትቱ የዚያን ጊዜ መረጃዎች ” ግርማ ሞገስ የተላበሰ” ስብዕና ባለቤት እንደነበር ይጠቅሱለታል፡፡ በአንደኛ ዲቪዚዮን በሚወዳደር <ቶርኬቬስ> የተባለ ክለብ ስኬታማ ቆይታ ካደረገ በኋላ በ1920 ወደ <MTK> ተዘዋወረ፡፡ ክለቡ በቡዳፔስት የመሀለኛው መደብ አይሁዳውያን የማህበረሰብ ክፍሎችን የሚወክልና እስካሁንም ድረስ የጂሚ ሆጋንን እግርኳሳዊ አስተምህሮ የሚከተል ነው፡፡

ወደ MTK እንደተዘዋወረ ጉትማን ለፌሬንክ ንዪል ሽፋን እየሰጠ ይጫወት ጀመር፡፡ ይሁንና ንዪል MTKን ለቆ ወደ ሩማንያው ቡድን <ኻጊበር ክሉዥ> ሲያቀና ወጣቱ ጉትማን የሚሰለፍበትን ቦታ በቋሚነት ተረክቦ የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች በመሆን የ1921ን የሊግ ዋንጫ አሰካ፡፡ ውድድሩ በአንደኛው ጦርነት ሳቢያ በመሃል ለሶስት ዓመታት ከመቋረጡ ውጪ ይህ ድል ክለቡ በተከታታይ ካሸነፋቸው አስር ዋንጫዎች መካከል ስድስተኛው ነበር፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ንዪል ወደ MTK ተመለሰ፤ ጉትማንም ቦታውን ለአንጋፋው ንዪል የመልቀቅ ግዴታ ከፊቱ ተደቀነበት፤ ስለዚህም ቤላ ጉትማን በቀጣዮቹ የህይወቱ መንገዶች እና በሚወደው ሙያ በዘላቂነት የሚከውነውን ድርጊት “ሀ!” ብሎ ጀመረ፡፡ በጊዜው ብዙ አይሁዳውያን የሚክኽሎስ ዎርዚን ሃይማኖት ላይ የተመሰረተ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ለማምለጥ ሲሉ የተሰደዱበትን ዱካ ተከትሎ እርሱም ወደ ቪየና ሸሸ፡፡ ይህም በመላ የአሰልጣኝነት እድሜው ብሄራዊ ድንበር ካቋረጠባቸው ሃያ ሶስት መዳረሻዎች መካከል የመጀመሪያው ሆነ፡፡

በእርግጥ እንደ ቡዳፔስቱ የከፋ ባይሆን እንኳ በቪየናም ጸረ-አይሁድ ዘመቻ ተስፋፍቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በመዲናዋ ቡና መጠጫ ቤቶች ውስጥ የሚዘወተረው የምሁራኖች እግርኳሳዊ ውይይት ጉትማን በከተማይቱ የቤቱ ያህል ተሰምቶት እንዲቀመጥ ረድቶታል፡፡ በ2001 ጀርመን ኬስል የተባለች ከተማ ውስጥ ለዝነኛው ቤላ ጉትማን በተዘጋጀ የመታሰቢያ ድርሳን ላይ ጋዜጠኛ ሃርዲ ግሩን ” ወደ መጨረሻዎቹ ዓመታት ጉትማን በተደጋጋሚ በሳኦፖሎ፣ ኒውዮርክ አልያም ሊዝበን ከተሞች ውስጥ ሲያርፍ ያኔ በጉልምስናው በቪየና ካፌዎች የሃገሪቱን ተወዳጅ ትኩስ መጠጥ (Melange) ፉት እያለ ከምርጥ ጓደኞቹ ጋር ስለ እግርኳስ ሲያወጉ ያልም ነበር፡፡” ሲል ጽፏል፡፡ ጉትማን እድሜው ሰባ አምስት ሲደርስ ከክለብ ወደ ክለብ፣ ከሃገር ወደ ሃገር፣ ከአህጉር ወደ አህጉር መንከራተቱን አቆመ፤ በቀጥታም ወደ ቪየና ተመልሶ በዎልፊስሽጋዜ ሙዚቃዊ ተውኔት የሚታይበት ቲያትር ቤት አጠገብ ይኖር ጀመር።

የጉትማን የኦስትሪያ ቆይታ በ1921 መጨረሻ ትልቁን የአይሁዳውያን ክለብ <ኻኮኣህ>ን ሲቀላቀል ይጀምራል፡፡ ክለቡ ገቢውን የሚያሟላው ባቋቋመው የውዝዋዜ ማሰልጠኛ ከሚገኝ ትርፍ ነበር፡፡ የእግርኳስ ቡድኑ የሚተገብረው የስኮትላንዶቹን ቅብብሎች ላይ ያመዘነ አጨዋወት (Passing Game) ሲሆን አሰልጣኛቸው ደግሞ ከጂሚ ሆጋን ጋር በቦልተን ዎንደረርስ አብሮ የተጫወተና በሚልዎልም ጥሩ የተጫዋችነት ጊዜ ያሳለፈው ቢሊ ሃንተር ነበር፡፡ ምንም እንኳ ማዕከላዊው የአውሮፓ እግርኳስ ላይ አካላዊ ጉሽሚያዎች የሚበዙበት የእንግሊዞቹ ስልት ተቀባይነት አግኝቶ ባያውቅም የሃንተር ሐሳቦች ግን በክለቡ ዘላቂ የአጨዋወት ተጽዕኖ ማሳረፍ ችለዋል፡፡

በ1925 ኻኮኣህ ራሱን ከአማተርነት አላቆ የፕሮፌሽናል ክለቦችን ፈለግ መከተል ጀመረ፡፡ በቀጣዩ ዓመት በመሃል ተከላካይ አማካይነት (Center-Half) ጉትማንን እያሰለፈ የኦስትሪያ ሻምፒዮና መክፈቻ ውድድርን አሸነፈ፡፡ የጥንቱን የአይሁድ እምነት (Muscular Judaism) የማስተዋወቅ እንዲሁም በፍልስጤም ውስጥ ለአይሁዳውያን የሚሆን ከተማ የመመስረት (Zionism) ዓላማን ያነገበው ገቢ መሰብሰቢያ ጉዞዎች ክለቡ የፋይናንስ ችግሮቹን እንዲያረግብ በእጅጉ ጠቀሙት፡፡ በ1926 <የማይበገሩት አይሁዶች!” የሚል ተቀጽላ ይዘው በምስራቃዊው የባህር ዳርቻ አካባቢ በሚገኙት የአሜሪካ ከተሞች (East Coast States) የጨዋታ ጉዞዎችን አደረጉ፤ አሰራ ሶስት ግጥሚያዎችን አከናውነውም በሁለቱ ብቻ ተረቱ፡፡ ገንዘብ ከማግኘት፣ ማንነትን ከማስተዋወቅና ምስል ከመገንባት አኳያ በጉዞው ትልቅ ስኬት አገኙ፤ ነገር ግን የውድቀታቸው ጅማሮም ያኔውኑ ተጠነሰሰ፡፡ የአሜሪካ ክለቦች ከኻኮኣህ የተሻለ ሃብት ስለነበራቸው አያሌ ማሻሻያዎች የተካተቱባቸው ስምምነቶች ከተደረጉ በኋላ ጉትማን <ኒውዮርክ ጂያንትስ> የተባለውን ክለብ ተቀላቀለ፡፡ ዓመቱ ሲገባደድም ግማሽ የሚሆኑ የኻኮኣህ አባላት ወደ አሜሪካው ክለብ አመሩ፡፡

ጉትማን በ1929 የአሜሪካ ዋንጫን ከክለቡ ጋር ማንሳቱን ተንተርሰን ዝውውሩን በእግርኳስ መነጽር ከቃኘነው የተጫዋችነት ህይወቱ ላይ እድገት ያስገኘ ውሳኔ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን፡፡ይሁንና በቆይታው ባካበተው ሃብት የተከለከሉ መጠጦች የሚቀርቡበት ህገወጥ መሸታ ቤት ሲገዛ ነገሮች መስመራቸውን ይስቱ ጀመር፤ በኒውዮርክ የተፈጠረው የገበያ አለመረጋጋት (Wall Street Crash) የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ካንኮታኮተ በኋላም ጉትማን የሰከነ ኑሮ መምራት አቃተው፤ ህይወቱም ምስቅልቅል አለ፡፡ “የቀረችኝን የአምስት ዶላር ክፍያ ስፈጽም ብሩ ላይ የሚገኙ ሁለቱን የአብርሐም ሊንከን ዓይኖችን በቁጭት በሳኋቸው፡፡ ‘መጨረሻዬማ እንዲህ አይሆንም፡፡’ አልኩ ለራሴ፤ ተስፋ የምቆርጥበት ጊዜ እንዳልነበረም አሰብኩ፡፡” ይላል ጉትማን ስለ ከባዱ ጊዜ ሲያስታውስ፡፡ ሁሌም በህይወቱ የላቀ ጥራት ያላቸው ነገሮች ላይ የሚያርፉ ዓይኖች ባለቤቱ ጉትማን በኻኮኣህ ቆይታው መለያው ከሃር ጨርቅ እንዲሰራለት ያለማቋረጥ ወትውቷል፡፡ ለጓደኞቹም ዳግመኛ ድህነትን ፍጹም እንደማያይ እየማለ ይናገር ነበር፡፡ የአሜሪካ ሊግ እስከፈረሰበት 1932 ድረስ በጂያንትስ ቆየና ከዚያም ወደ ኻኮኣህ ተመልሶ ለሚቀጥሉት አርባ አንድ ዓመታት የሚዘልቅበትን የአሰልጣኝነት ህይወት “አንድ” ብሎ ጀመረ፡፡

ሁለት የውድድር ዘመናትን በቪየና ከከረመ በኋላ በሑጎ ሜይዝል ጥቆማና ድጋፍ ወደ ሆላንዱ <ኤስ.ሲ. ኢንሸዴ> አመራ፡፡ በመጀመሪያ ከክለቡ ጋር የሦስት ወራት ውል አሰረ፤ ሁለቱም ወገኖች አዲስ ስምምነት ለመፈጸም ሲደራደሩ ኢንሸዴ ሊጉን ካሸነፈ ከፍተኛ የማበረታቻ ክፍያ (Bonus) እንዲቀርብለት ጉትማን ጠየቀ፡፡ ክለቡ የምስራቅ ዲቪዚዮን ተብሎ ከሚጠራው ውድድር ላለመውረድ በመፍጨርጨር ላይ የነበረ ከመሆኑ አንጻር የክለቡ ስራ አስኪያጆች በጉትማን የጉርሻ ጥያቄ ወዲያው ተስማሙ፡፡ እያደር የቡድኑ አቋም አስገራሚ መሻሻል አሳየ፤ ይሁን እንጂ በሃገር አቀፉ ሻምፒዮና በሚያስቆጭ መልኩ ለጥቂት ወደቀ፡፡ የውድድር ዘመኑ እየተገባደደ ሲሄድ የኢንሸዴ ሊቀመንበር የቡድኑን ጨዋታዎች ሊመለከት ሲጓዝ ይጨንቀው ገባ፤ የጉትማን ተጨማሪ ክፍያ ክስረት ውስጥ ስለሚከታቸው ክለቡ ሽንፈት እንዲገጥመው እየተመኘና ጸሎት እያደረሰ እንደሚታደም ከጊዜያት በኋላ አምኗል።

ጉትማን በጊዜው የሆላንዱን ክለብ በመረከቡ ተጸጽቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ግዛት የመመስረት ያህል ጽኑ መሠረት አኑረው ለመሄድ የሚጥሩ አንዳንድ አሰልጣኞች አሉ፤ እነርሱ ቡድኑን ከለቀቁ በኋላ ስኬትን በዘላቂነት ማስቀጠል የሚያስችል ጠንካራ መዋቅር ዘርግተው ኗሪ አሻራቸውን ያሳርፋሉ፡፡ ጉትማን ግን እነዚህኞቹ ምድብ ውስጥ አይካተትም፤ ይልቁንም የአጭር ጊዜ እቅድ የሚያሳካ አሰልጣኝ ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ ስምምነት ላይ አጥብቆ ይከራከራል፤ ጣልቃገብነትን ደግሞ ፈጽሞ አይታገስም፡፡ በሙያው ረዘም ያለ ጊዜ ካስቆጠረ በኋላም ” በአንድ ክለብ የአሰልጣኝነት ቆይታ ሦስተኛው የውድድር ዘመን ሁሌም አደጋ ይዞ ይመጣል፡፡” ይል ነበር፡፡ እርሱ በየትኛውም ክለብ ይህን ያህል ዓመት አይከርምም፤ በሆላንድ ሁለት ዓመት ካሳለፈ በኋላ ወደ ኻኮኣህ ተመለሰ፤ ሆኖም ኦስትሪያ ከጀርመን ጋር ውህደት ስትፈጥር (Anschluss) ወደ ሃንጋሪ ኮበለለ፡፡

ከዚያ በኋላ የተከሰተው እስካሁንም ግልጽ አልሆነም፤ ከጦርነቱ መዓት ተርፎ እንዴት በህይወት ሊቆይ እንደቻለ ሲጠየቅ የጉትማን የሰርክ ምላሽ ” እግዚአብሄር ረድቶኝ!” ብቻ የሚል ነው፡፡ የአይሁዳውያን ማጎሪያ ውስጥ ታናሽ ወንድሙ ሞቶበታል፤ ለእርሱ ከኻኮኣህ ቡድን ጋር የመሰረተው ወዳጅነት ህይወቱን ያተረፈለትን አጋጣሚ ሳይፈጥርለት እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ የኦስትሪያው ክለብ ወደ ሲውዘርላንድ እንዲሸሽና እዚያ ተደብቆ እንዲኖር አግዞታል፡፡ እርግጥ ጉትማን ውሃ አጣጩን የተዋወቃት በሲውዘርላንድ ቢሆንም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ያሳለፈውን ህይወት ለመናገር ሁሌም “እምቢኝ!” እንዳለ ጸንቷል፡፡ በ1964 በታተመው ግለ ታሪክ መጽሃፉም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አንድ አንቀጽ ብቻ ሰፍሮበት ይታያል፡፡ “ባላፉት አስራ አምስት ዓመታት በእነዚያ የጥፋት ጊዜያት ከሞት አምልጦ በህይወት ለመቆየት ስለተደረጉት ትግሎች በርካታ መጽሃፍት ተጽፈዋል፤ ስለዚህም እያንዳንዱን ስቃይ በዝርዝር እያቀረብን አንባቢዎቻችንን ማሳቀቅ አይኖርብንም፡፡” ይላል ቁንጽል ሐሳቡ፡፡

በ1945 <ቫሳስ>ን ለማሰልጠን ወደ ሃንጋሪ ሄደ፤ ቀጣዩ የጸደይ ወቅት ላይ ደግሞ የሩማኒያው <ሲዮካኑል>ን ተረከበ፡፡ በወቅቱ በአብዛኛው የአውሮፓ ክፍል ተከስቶ የነበረውን የምግብ እጥረት እና የዋጋ ግሽበት በዘዴ ማለፍ ይችል ዘንድ በሲዮካኑል የሚበሉ ነገሮች በአግባቡ እንዲቀርቡለት ተደራደረ፡፡ አንድ ቦታ ላይ ተረጋግቶ መቆየት የተሳነው ጉትማን ይህ የመቅበዝበዝ ችግሩ መለያው ሆኖበት ከዛም ለመልቀቅ ተዘጋጀ፡፡ የሩማኒያው ክለብ ስራ አስኪያጅ በተጫዋቾች ምርጫ እጃቸውን ማስረዘም ሲዳዳቸው የተመለከተው ጉትማን ፊቱን ወደ ሰውየው አዙሮ ” አሁን መሰረታዊ መመሪያዎችን እያከበርክ ያለህ ትመስላለህ፤ ክለቡን መምራትም ትችላለህ፡፡” በማለት የምጸት ንግግሩን አጠናቆ ክለቡን ለቀቀ፡፡

በቀጣዩ የውድድር ዘመን ጉትማን ከሃንጋሪው <ኧጅፔስት> ጋር ሆኖ ሊጉን አሸነፈ፡፡ ከዚያም የፌሬንክ ፑሽካሽ አባት ያሰለጥኑ የነበረው <ኪስፔስት> የአዛውንቱ አሰልጣኝ ተተኪ አድርጎ ቀጠረው፡፡ ተጋጣሚው በዝነኛው ፑሽካሽ የሚሰለጥነው <ጊዮር> ቢሆንም ጉትማን መረር ያለ ጸብ ውስጥ ከገባው አሰልጣኝ ጋር ሲገናኝ ምንም አይነት የበታችነት አልያም የማፈር ስሜት እንደማይሰማው እርግጥ ነበር፡፡ “እግርኳስ በትክክለኛው መንገድ መተግበር ይኖርበታል፡፡” የሚል አቋም ያለው ጉትማን የጨዋታውን የመጀመሪያ አጋማሽ የመስመር ተከላካዩ ሚኻይል ፓቲን ኃይል እና ጉልበት ያመዘነበት አጨዋወት እንዲተው ሲወተውተው ቆየ፡፡ ያን ሁሉ ምክር ችላ ባለው ፓቲ የተበሳጨው ጉትማን ቡድኑን በአስር ተጫዋቾች ብቻ የሚያስቀር ብያኔ ቢሆንም ተከላካዩን በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ሜዳ እንዳይገባ አዘዘው፡፡ ፑሽካሽ ደግሞ አያገባው ገብቶ ፓቲን እንዲጫወት ነገረው፤ በመሃል ተጫዋቹ የመወላወል አዝማሚያ አሳየ፤ የጉትማንን ቁጣ ለመቀበል አመነታ፤ በመጨረሻ የአሰልጣኙን ትዕዛዝ ጥሶ ወደ ሜዳ ገባ፡፡ ጉትማንም ሁለተኛውን አጋማሽ በአሰልጣኞች መቆሚያ ሆኖ ጨዋታውን ላለመምራት ወሰነ፤ እስከ ማገባደጃው ሰዓትም ስለመኪኖች እሽቅድድም የተጻፉ ጋዜጦችን እያገላበጠ ጠበቀ፤ ኪስፔስት 4-0 ተረታ፡፡ ጨዋታው እንደተጠናቀቀም በኤሌክትሪክ የሚሰራ የከተማ ውስጥ ባቡር ተሳፍሮ ወደ ቤቱ ነጎደ፤ ከዚያ በኋላ ወደ ክለቡ አልተመለሰም፡፡

የቤላ ጉትማን እንክርት ማቆሚያ አልነበረውም፡፡ መንገላታቱ ቀጠለና በጣልያን ፓዶቫ እና ትርስቲናን፣ በአርጀንቲና ቦካ ጁኒየር እና ኩዉልሜስን፣ በቆጵሮስ አፖዔል ኒቆሲያ፣ በ1953-54 የውድድር ዘመን አጋማሽ ላይ ደግሞ ኤሲ ሚላንን አሰለጠነ፡፡ በሚላን የግማሽ ዓመት ቆይታው ክለቡን በሊጉ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ አስቻለው፤ በ1954-55 የውድድር ዘመን ከአስራ ዘጠኝ ጨዋታዎች በኋላ ሚላን የሊጉ መሪነትን ተቆናጠጠ፤ ነገር ግን ጉትማን ከክለቡ የቦርድ አመራሮች ጋር በፈጠረው ተደጋጋሚ እሰጣ’ገባ ከቡድኑ ተሰናበተ፡፡ በድንጋጤ ክው ብለው የእርሱን መልቀቅ ለማወጅ ለተሰባሰቡ የብዙሃን መገናኛዎችም “ወንጀለኛ ሆኜ ሳልገኝ፥ የግብረ ሰዶማዊነት ባህሪም ሳላሳይ ተባርሬያለሁ፤ ለማንኛውም ደህና ሁኑ!” አላቸው፡፡ ከዚያ በኋላ ከክለቦች ጋር ሲደራደር የስምምነት ውላቸው ላይ በየትኛውም የሊግ እርከን እርሱ የሚያሰለጥነው ቡድን እየመራ ከሆነ ማባረር እንደማይቻል የሚጠቅስ ህግ እንዲካተት አደረገ፡፡

እዚያው ጣልያን ውስጥ ማሰልጠኑን ዘለቆበት የቪቼንዛን የአሰልጥንልን ጥያቄ ተቀበለ፡፡ በ1956ቱ የውድድር ዘመን ቡድኑን ለሃያ ስምንት ጨዋታዎች ከመራ በኋላ “በቃኝ!” ብሎ የዓመቱን አመዛኝ ጊዜ ካለ ስራ ተቀመጠ፡፡ የቡዳፔስት ህዝባዊ አመጽ ግን ለእርሱ በጎውን ይዞለት ከተፍ አለ፤ የስራ እድልም ፈጠረለት፡፡ ( <ኪስፔስት> በወታደራዊው ጁንታ ቁጥጥር ስር ሲገባ <ኻኖቭድ> የሚል ስያሜ ማግኘቱን ልብ ይሏል፡፡) ኻኖቭዶች ተጫዋቾቻቸው ለውጊያ ወደ ጦር ሜዳ እንዳይላኩ ስለሚፈልጉ ክለቡ ወደ ብራዚልና ቬኔዝዌላ የሚደረጉ፣ ለረጅም ጊዜ የሚቆዩና ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ልምድ ለመለዋወጥ የታቀደባቸው የጉብኝት ጉዞዎች ግብዣን ተቀበሉ፡፡ በወቅቱ ከፑሽካሽ ጋር እርቀ ሠላም አውርዶ የነበረው ጉትማን ቡድኑን እንዲመራ ኃላፊነቱ ተሰጠው፡፡ ከርታታው የእግርኳስ ልሂቅ ራሱን በደቡብ አሜሪካ እጅግ ተፈላጊ ሰው ሆኖ አገኘው፤ ስለዚህም እዚያው ለመክረም ወጠነ፤ የሳኦፖሎን ጥሪ አጤነና ውል ተፈራረመ፡፡ እውነታው እጅጉን ውስብስብ ቢሆንም ቅሉ ዘወትር ጉትማን የሚያነሳውና የሃንጋሪያኑ 4-2-4 ፎርሜሽን ወደ ብራዚል እንደሄደ የሚወተውትበት ሐሳብ ያኔ የስረ-መሠረቱን ጅምር አገኘ፡፡

በ1957 ጉትማን ሳኦፖሎ የፓውሊስታን ዋንጫ እንዲያነሳ አደረገ፤ ግን ደግሞ ወዲያው የብራዚሉን ክለብ ለቆ ወደ አውሮፓ ተሻገረ፤ የፖርቱጋሉ ፖርቶም ማረፊያው ሆነ፡፡ “የእግርኳስ አሰልጣኝ ልክ አንበሳን እንደሚገራ ሰው ነው፡፡ በከፍተኛ የራስ መተማመንና ያለምንም ፍርሃት አናብስቱን በማጎሪያቸው ሲያለምዳቸውና አብሯቸው ሲጫወት ገዢያቸው እሱ ይሆናል፡፡ አራዊት አልማጁ ስለያዘው የማደንዘዝ ሥነ ልቦናዊ ኃይል እርግጠኝነት ባልተሰማው ቅጽበት ግን ስጋት ዓይኑ ላይ መነበብ ይጀምራል፤ ያኔ ያበቃለታል፡፡” ይላል የአሰልጣኝነት ሕይወትን በተመለከተ ፍልስፍናውን ሲያስቀምጥ፡፡ ጉትማን ሁሌም የተናገረውን ይኖራልና ተጫዋቾቹ ዓይኑ ላይ ፍርሃት እስከሚያዩ ድረስ ጠብቆ አያውቅም፡፡

ከቤኔፊካ በአምስት ነጥቦች አንሰው የዋንጫ ህልማቸው አብቅቶለት የነበሩት ፖርቶዎች ከኋላ ተነስተው ከባላንጣቸው የበላይ እንዲሆኑና ድል እንዲጎናጸፉ ጉትማን ረዳቸው፡፡ ይሄኔ ቤኔፊካዎች  ዓይናቸውን ጣሉበት፤ በፍጥነትም አሰልጣኛቸው አድርገው ሾሙት፡፡ ጉትማንም በክለቡ ሥራ እንደጀመረ ሃያ ነባር ተጫዋቾች አባረረ፤ አዳዲስና ብቁ ወጣቶችን በመያዝ እነርሱን ለእውቅና ክለቡን ደግሞ ለ1960 እና 1961 የሊግ ድል አበቃ፡፡ ከሁሉ የሚያስገርመው ቡድኑ የሚከለተው ፍሰቱን የጠበቀ ማራኪ አቀራረብ (Free Flowing Football) ውጤታማነት ነበር፡፡ ቤኔፊካ በዚሁ ስልት በ1961 የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ (የአሁኑ ቻምፒዮንስ ሊግ) ፍጻሜ ባርሴሎናን 3-2 በመርታት ሪያል ማድሪድ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ዋንጫውን በማሸነፍ ውድድሩን በራሱ ቁጥጥር ሥር ያኖረበትን ሒደት እንዲያከትም አደረገ፡፡

ለጉትማን ያ ሁሉ ጀብዱ አንጀት የሚያርስ አልነበረም፡፡ በበርን ከተካሄደው የፍጻሜው ጨዋታ አንድ ሳምንት በኋላ በክለቡ ታሪክ ታላቁ ተጫዋች ለሚሆነው ወጣት የመጀመሪያ የመሰለፍ እድል ሰጠ፦ ለዩዞቢዮ፡፡ ጉትማን በሳኦፖሎ ተጫዋቹ ከነበረው ካርሎስ ባወር ጋር ሊዝበን በሚገኝ ጸጉር አስተካካይ ቤት ውስጥ አለመግባባት ባይፈጥር ኖሮ ምናልባትም ትውልደ ሞዛምቢካዊው ኮከብ ስፖርቲንግን ይቀላቀል ነበር፡፡ ባወር የብራዚሉን ክለብ እየመራ በአፍሪካ ለአምስት ሳምንት የሚቆይ ጉዞዎችን ሊያካሂድ እንደሆነ ለጉትማን አወጋው፤ ጉትማንም አዳዲስ ክህሎት ባላቸው ተጫዋቾች ላይ አይኑን እንዲያሳርፍ፣ ንቁ ክትትል በማድረግ መረጃ እንዲያደርሰውና የምልመላ ስራ እንዲሰራለት መከረው፡፡ ይህን ውይይት ካደረጉ አምስት ሳምንታት በኋላ ሁለቱም ሰዎች እዚያው የሊዝበኑ የወንዶች ጸጉር ቤት ይገናኛሉ፡፡ ባወር የስፖርቲንግ ወጣት ተጫዋቾች አቅራቢ በሆነው የሞዛምቢኩ <ሎሬንኮ ማርኩዌስ> ክለብ (የዚያን ጊዜ ማፑቶ የምትሰኘው ከተማ) ሊያስፈርመው አጥብቆ የሚሻው ተጫዋች እንዳየ ነገር ግን ዋጋው ከአቅማቸው በላይ እንደሆነበት አሳወቀው፤ በዚህም ምክንያት ባለክህሎቱን ወጣት እንዳያጣው ስጋቱን ገለጸለት፡፡ ጉትማን ጊዜ መፍጀት አላስፈለገውም፤ በቶሎ ወደ ሞዛምቢኩ ክለብ ስልክ መታ፤ በሒደት ላይ በሚገኝ ውል የማሰር ስምምነት መሃል ገብቶ ድርድሩን ጠለፈ፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ዩሶቢዮ የቤኔፊካ ንብረት ሆነ፡፡ ጉትማን ስለ ሁኔታው ሲናገር ” ዩሶቢዮን በማስፈረሜ ማሪዮ ኮሉናን ወደኋላ እንዲያፈገፍግ እና ከመሃል አጥቂው ጎን ከሚጫወት የፊት መስመር ተሰላፊነት (Inside Forward) ይልቅ የመስመር አማካይነት (Wing Half) ሚና እንዲወጣ አደረኩ፤ ሲጀምር አካባቢ ብዙ ግቦች ማስቆጠር ስላልቻለ በቦታው ምቾት አልተሰማውም፤ እያደር ግን የቡድኔ ምርጡ ተጫዋች እርሱ ሆነና አረፈው፤ እንዲያውም “የቤኔፊካው ኼጁኩቲ” ሆነ፡፡” ይላል፡፡

ቤኔፊካ ዩሶቢዮን የግሉ ባደረገበት ዓመት ሦስተኛ ሆኖ ጨረሰ፤ ቡድኑ በደረጃ ሰንጠረዡ ከበላዩ ሆነው ያጠናቀቁት ፖርቶና ስፖርቲንግ ክለብ ካስተናገዱት ድምር ጎሎች የበለጠ ተቆጠሩበት፡፡ ይህ እንግዲህ ምናልባት የጉትማን የማጥቃት አቀራረብ የስኬታማነት እድሉ የመነመነ መሆኑን ያመላክት ይሆናል፡፡ እርሱ ግን ” ተጋጣሚዎቻችን ጎል ሲያገቡ ብዙ አልሸበርም፤ ምክንያቱም ሁሌም እኛ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር እንደምንችል አምናለሁና፡፡” ይላል፡፡ እንዳለውም በአምስተርዳሙ የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ቤኔፊካ በሪያል ማድሪድ 2-0 እና 3-2 ከመመራት ተነስቶ በመጨረሻ 3-5 አሸንፏል፡፡ ይህን የገመቱ ግን ጥቂቶች ነበሩ፡፡ ሦስት ግቦችን አስቆጥሮም ማድሪድን ከሽንፈት መታደግ ያልቻለው ፑሽካሽ የጨዋታው መገባደጃ ፊሽካ እንደተነፋ ዩሶቢዮን ፈላልጎ መለያውን አውልቆ አቀበለው፤ ሁኔታው የአውሮፓ ታላቁ ተጫዋች የመሰኘት ካባን ፑሽካሽ ለአፍሪካዊው ወጣት የሚያስረክብ አስመስሎታል፤ በብዙዎች አዕምሮም በአብነት የሚጠቀስ የታላቅነት ውርስ ተደርጎ ተተርጉሟል፡፡ በተመሳሳይ የፖርቱጋሉ ክለብ የአውሮፓ ምርጥ ቡድንነት ዘውድን ከማድሪድ ላይ የመውሰዱ ጅምር የተበሰረም መስሏል፡፡ በወቅቱ የዩዞቢዮ እድሜ ሃያ ብቻ የነበረ ከመሆኑ አንጻር ሪያል ማድሪድ በ1950ዎቹ የአውሮፓን ሃያልነት ዘውድ እንደተቆጣጠረው ሁሉ ቤነፊካም የ1960ዎቹን የክለቦች የበላይነት መንበር የመቆናጠጥ አቅም ነበረው፡፡ ሆኖም ግን ክለቡ ሃንጋሪያዊውን አሰልጣኝ ማሰንበት ተሳነውና ያ ሳይሆን ቀረ፡፡

ጉትማን ከፍጻሜው ጨዋታ በኋላ ወደ ክለቡ አመራሮች ቀርቦ ላስገኘው ውጤት የጉርሻ  ክፍያ እንደሚሰጡት ሊያረጋግጥ ፈለገ፡፡ የክለቡ ስራ አስኪያጆችም በውሉ ላይ እንዲህ ያለው የማሻሻያ ስምምነት እንዳልሰፈረ ሊያስረዱት ሞከሩ፡፡ “የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫን አሸንፌ የፖርቱጋል ሊግን ድል ሳደርግ ካገኘሁት በአራት ሺህ ዶላር ያነሰ ብር ነበር የተቀበልኩት፡፡ የክለቡ ዳይሬክተሮች ቦርድ ችግሩን ለመፍታት ምንም ጥረት ሊያደርግ አልቻለም፤ ስለዚህ ስለመልቀቅ ማውጠንጠን ጀመርኩ፡፡” ይላል ጉትማን ከቤኔፊካ የለቀቀበትን ሰበብ ሲያብራራ፡፡

ከሁለት ወራት በኋላ የሶስተኛ ዲቪዚዮኑን <ፖርት ቫሌ> ጥሪ ችላ በማለት ወደ ደቡብ አሜሪካ ተመልሶ የፓራጓዩን ፔኛሮል ክለብ ለማሰልጠን ተስማማ፡፡ ፔኛሮልን ኮፓ-ሊበርታዶሬስ የተሰኘውን የደቡብ አሜሪካ ክለቦች ዋንጫ እስከማንሳት የደረሰ ቡድን አድርጎ ሰራው፡፡ ከቦታ ቦታ የመኳተን አባዜ የተጸናወተው ጉትማን ግን የፍጻሜው ጨዋታ ላይ ቡድኑን መምራት አልሆነለትም፤ የኦስትሪያ ብሄራዊ ቡድንን ለመረከብ ወደ ቪየና አቀና፡፡ የጸረ- አይሁዳውያን እንቅስቃሴ በመፋጠኑ ሳቢያ አምስት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ኦስትሪያን መርቶ ወደ ቤኔፊካ ሄደ፤ እዚያም ብዙ ሳይረጋጋ ወደ ጄኔቫዋ ሰርቬቴ አመራ፡፡ በመጨረሻም እጅጉን በሚወዳት ቪየና ከተማ የሚገኘውን ኦስትሪያ ቪዬን ከማሰልጠኑ በፊት በግሪኩ ፓናቲናኮስ እና ፖርቶ መጠነኛ ጊዜያትን አሳለፈ፡፡ ጉትማን ከመጀመሪያው የቤኔፊካ ቆይታ በኋላ ራሱን በቀድሞው ስብዕና ሊያገኘው አልቻለም፡፡ ቤኔፊካም ቢሆን ከባለውለታው ጉትማን በኋላ ኃያልነቱን መልሶ ለማግኘት ተቸግሯል፡፡ ለብዙ ጊዜያት ጉትማን ቤኔፊካዎችን እንደረገመ የሚያስታውስ ታሪክ ሲነገር ቆይቷል፤ ክለቡ የላቡን እስካልከፈለው ድረስም የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫን በጭራሽ እንዳይወስድ ስለት ማድረሱም ይወራበታል፡፡ ነገሩ ብዙም ስሜት አይሰጥ ይሆናል፤ የፖርቱጋሉ ቡድን የእርግማኑ ገፈት ቀማሽ መሆኑ ግን አልቀረም፤ ከዚያ ወዲህ በአውሮፓ የክለቦች ውድድር ከአምስት በሚልቁ የፍጻሜ ጨዋታዎች ላይ ቀርቦ በሁሉም ተሸንፏል፡፡

እውነታው እግርኳስ መቼም ተመሳሳይ ይዘት ኖሮት አለማወቁ ነው፡፡ ጉትማን ምናልባትም ከቻፕማን በኋላ ከማንም በላይ የአሰልጣኞችን ሙያ በአግባቡ ያሳየ ነበር፡፡ የጨዋታ አረዳዱ እጅጉን የተለየ ቢሆንም እርሱን በአርዓያነት ተከትሎ ወደ እግርኳሱ ዓለም ብቅ ያለው ሄሌኒዮ ሄሬራ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ጣልያናዊው አሰልጣኝም ከተጋጣሚ ቡድን በአንድ ግብ የበለጠ ማስቆጠር፣ ተቃራኒ ቡድንን በጥንቃቄ የመከታተል ሒደት (Cynicism)፣ ጥብቅ የመከላከል አጨዋወት (Catennacio) እና ከባላጋራ በአንድ ያነሰ ጎል ማስተናገድ የሚሉ ተወዳጅ እሳቤዎችን በላቀ ሁኔታ የመተግበር አላማን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡


ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም ዘጠኝ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡