የአሰልጣኞች ገጽ | ክፍሌ ቦልተና [ክፍል 2 – የኢትዮጵያ ቡና እና የኢትዮጵያ መድን ቆይታ]

የሀገሪቱ ውጤታማ እና አንጋፋ አሰልጣኞችን የሥራ ህይወት፣ ተሞክሮ እና አስተሳሰብ የሚዳስሰው “የአሰልጣኞች ገፅ” ክፍሌ ቦልተናን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እያቀረብን እንገኛለን። በዛሬው የክፍል 2 ዝጅታችንም አሰልጣኝ ክፍሌ በኢትዮጵያ ቡና እና መድን ስላሳለፉት የሥራ ጊዜ ቆይታ አድርገናል


ከአየርመንገድ በመቀጠል ወደ ኢትዮጵያ ቡና ነው የሄድከው?

በ1996 ክረምቱ ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ተካሂዶ አየርመንገድ እና ቡና ተጫውተን ነበር፡፡ ቡናዎች ቢያሸንፉንም በወጣቶች የተገነባው የእኛ ቡድን ጥሩ ይጫወት ስለነበር በ1997 እነርሱ አብርሃም ተክለሃይማኖትን በዋና አሰልጣኝነት ሲቀጥሩ የደጋፊ ማህበሩ ሰዎች በቀጥታ ” አንተ ምክትል ሁን፡፡” አሉኝ፡፡ አሁን በሃገረ አሜሪካ የሚገኘው የወቅቱ የደጋፊዎች ማህበሩ ፕሬዘዳንት አቶ ብዙአየሁ ስለኳስ ጥልቅ እውቀት ነበረው፡፡ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው ነዳጅ ማደያው የማህበሩን አባላት ስብሰባ ጠርቶ ” እኛ ለአሰልጣኝ አብርሃም እንነግርልሃለን፤ ቡና የሚከተለው የራሱ አጨዋወት አለ፡፡ አንተን አየርመንገድ ሳለህ አይተንሃል፤ ስለዚህ አብርሃምን እንድትረዳው እንፈልጋለን፡፡” አለኝ፡፡ አሰልጣኝ አብርሃምን ሳናግረው እርሱም ፈቃደኛ ሆነ፡፡ በዚሁ ቡናን ተቀላቀልኩ፡፡

በአሰልጣኝነት ሙያ አንዳንዴ ውጤት አልመጣ ይላል፥ ያው የሥራው ባህርይ ነውና አብርሀምም ውጤት እምቢ አለው፤ በመጨረሻ በራሱ ፍቃድ ክለቡን ለቀቀ፡፡ የክለቡ ሰዎች ሥዩም አባተን አመጡ፤ ቡና ውስጥ ብዙ ጊዜ አሰልጣኝ ሲለቅ ስዩም ነበር የሚመለሰው፡፡ ያኔ እኔ የሥዩም ምክትል ሆኜም አስራት አዱኛ ወደያዘው ወጣት ቡድን እየሄድኩ አልፎ አልፎ አግዘው ነበር፡፡ አንድ ረቡዕ ዕለት ኮሚቴዎች መጡና ” ኢትዮጵያ ቡና እሁድ ቀን ላለበት ጨዋታ ስዩም በህመም ምክንያት ወደ አዋሳ መሄድ ስለማይችል አንተ ቡድኑን ይዘህ ትሄዳለህ፡፡” አሉኝ ፡፡ ቡና በጊዜው በርካታ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ያካተተ፣ እነ አሸናፊ ግርማ እና አንዳርጋቸው ሰለሞንን የመሳሰሉ አንጋፎችን የያዘ ቡድን ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ገና ጁኒየር አሰልጣኝ ነኝ፡፡ ያም ሆኖ ኃላፊነቱን አልፈራሁም፡፡ አሰላለፍ ለማውጣት በነበረኝ አጭር ጊዜ ውስጥ የተጫዋቾችን ወቅታዊ ብቃትና ልምምድ ላይ ያሳዩትን ትጋት በመመልከት ለቡድኑ የሚመጥኑትን ለመምረጥ ወሰንኩ፡፡ ያን ጊዜ አንዳርጋቸው ትልቅ የብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ነበር፡፡ ነገር ግን በልምምድ ወቅት የሚፈለግበትን አላሳየም፡፡ በድፍረት እርሱንና ሌሎች መስፈርቴን የማያሟሉትን እዚሁ ትቼ በጊዜው ብቁ የነበሩትን ይዤ ወደ አዋሳ ሄድኩ፡፡ በጨዋታው ታፈሰ ተስፋዬ አግብቶ ቡና አዋሳን ከረዥም ጊዜ በኋላ በአዋሳ ሜዳ አሸነፈ፡፡ ከዚያ በተከታታይ ወደ ስምንት ጨዋታዎች ማሸነፍ ቻልን፡፡

ዓመቱ መጨረሻ ላይ ” ቡናን ራስህ ያዝ፡፡” ተባልኩ፡፡ ከዚያ በፊት በአየር መንገድ የአስራት ኃይሌ ምክትል ሆኛለሁ፤ በኢትዮጵያ ቡና የአብርሃም ተክለሃይማኖት እና የስዩም አባተ ምክትል ነበርኩ፤ በተጫዋችነት ዘመኔ ካሳሁን ተካ በደንብ አሰልጥኖኛል፤ ጋሽ ሐጎስ ደስታም በወጣትነት የሥልጠና ህይወቴ አልፈዋል፡፡ በእነዚህ ባለብዙ ልምድና ሰፊ እውቀት ያላቸው ትልልቅ አሰልጣኞች ሥር ሰርቻለሁ፤ በእግርኳስ አጨዋወት በራሴ የማምንበት አካሄድ አለኝ፡፡ ስለዚህ ኃላፊነቱ ብዙ አልከበደኝም፡፡ እንዲያውም ክለቡን እንደተረከብኩ ወደ ወጣቶቹ አማተርኩ፡፡ እነ መስፍን (ቻይና) እና ምንያህልን ጨምሮ ወደ አስራ ሁለት የሚጠጉ ልጆችን ወደዋናው ቡድን አሳደግሁ፡፡ ለምሳሌ፦ እኔ ዋና አሰልጣኝ ከመሆኔ በፊት ምንያህል በአብርሃምም ሆነ በስዩም ጊዜ ከቡድኑ ጋር ዝግጅት እየሄደ ይመለስ ነበር፡፡ እኔ ኃላፊነቱ እንደተሰጠኝ አስራት አዱኛን “ምንያህልስ?” ብዬ ስጠይቀው እርሱም  ” ‘ምንያህል ቡና ውስጥ በ<B> ደረጃ ለመጫወት እድሜው አልፏል፡፡’ ተብሎ ወደ ቤቱ ሄዷል፡፡”  አለኝ፡፡ እኔም ‘ በል ቶሎ ጥራልኝ፡፡’ አልኩት፡፡ ከዚያ ቡና ዋናው ቡድን ገባ፤ እስከ ብሄራዊ ቡድን የደረሰ ትልቅ ተጫዋች ሆነ፡፡ ቡና ለሁለት ዓመት ሰራሁ፡፡

አቶ ተስፋዬ ካህሳይ ትልቅ የእግርኳስ እውቀት ያለው ሰው ነው፡፡ ” ክፍሌ ወጣቶች ላይ በደንብ ሰርቷል፡፡” በማለት ደጋፊ ማህበሩን አስተባበረልኝና የትምህርት ዕድል እንዳገኝ ረዳኝ፡፡ በሆላንድ ከአያክስ ክለብ ጋር ተጻጽፎ ” በአሰልጣኝነት ብትማር ሃገራችንንም ሆነ ክለባችንን ትጠቅማለህ፡፡” ብሎ ሁኔታዎች አመቻቸልኝ፡፡ “ኢትዮጵያ ቡና ስፖንሰር የሚሆንልህ ከሆነም ጠይቅ፡፡” አለኝ፡፡ የሚገርመው የትምህርት ዕድሉን ራሱ ነው ያመጣልኝ፡፡ እኔ የቡና ኃላፊዎችን ስፖንሰር ጠየቅሁኝ፡፡ መቶ አለቃ ፈቃደ፣ አቶ አብድራዛቅና አቶ ስንታየሁ ወዲያው ፈቃደኛ ሆነው ከመቶ ሺህ ብር በላይ አውጥተው ኮርሱን እንድከታተል አደረጉ፡፡

ከአውሮፓ ተመልሼ ከመጣሁ በኋላ ግን ሶስት ጨዋታዎች ላይ ውጤት ማምጣት አልሆነልኝም፤ በእርግጥ ደጋፊዎች ብዙ አልተቃወሙኝም፤ ግን መቀጠል አልቻልኩም፤ ለቀቅሁ፡፡ በወቅቱ ዳዊት እስጢፋኖስን እና ዳዊት ፍቃዱን ለክለቡ ለማስፈረም ብጥርም ክለቡ ደጋፊ እንጂ ከፍተኛ በጀት ስላልነበረው እንደ ሌሎቹ ክለቦች ተጫዋቾቹ የሚፈልጉትን ገንዘብ አይከፍልም ነበር፡፡ ስለዚህ ደጋፊዎች ትዕግስት እንዲኖራቸው ቦርዱ መሥራት እንዳለበት እወተውት ገባሁ፡፡ በሶስትና አራት ዓመት እቅድ ሰርቼ፣ በራሴ ፍልስፍና ተመርቼ፣ ወጣቶችን አሳድጌ፣…..  ጠንካራ ቡድን ለመገንባት ነበር እቅዴ፡፡ በዚህ እምነቴ የያዝኳቸው ልጆች ወጣቶች ነበሩ፥ ውጤት ጠፋ፤ ጫና በዛ፡፡ ከዚያ ከክለቡ ወጣሁ፡፡ ቡና በአሰልጣኝነት ህይወቴ ባለ ውለታዬ ክለብ ነው፡፡ ለማንም ያላደረገውን ነገር ለእኔ አድርጓል፡፡

በ1997 የአብርሃም ተክለሃይማኖት ምክትል አሰልጣኝ ሆነህ ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቀልክ፡፡ ከ1998 ጀምሮ እስከ 2000 አጋማሽ ድረስ ደግሞ በተለያዩ ወቅቶች የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ሆነህ የመሥራት አጋጣሚ አገኘህ፡፡ በኢትዮጵያ ቡናም እንዲሁ በወጣቶች ላይ መሥራትህን ቀጥለሃል፡፡ በወቅቱ ከተለያዩ ክለቦች ያለ ፊርማ ክፍያ ወጣቶችን በማዘዋወር እንዲሁም ከ<B> ቡድኑ በማሳደግ ከአንጋፎቹ ጋር እያዋሃድክ ጥሩ ቡድን ማዘጋጀትህ ይታወቃል፡፡ የ1998ቱ ቡና ደግሞ በጣም ጥሩ የሊግ ጉዞ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ብዙ በሚጠብቅ ክለብ ውስጥ ወጣቶች ሰብስቦ ቡድን የመገንባቱን ውሳኔ እንዴት ደፈርክ?

በእርግጥ እኔ በወጣቶች ላይ እምነት አለኝ፡፡ ጊዜ ተሰጥቶኝ ተሰጥኦ መገምገም ደስ ያሰኘኛል፡፡ በዚያን ጊዜም በርካታ ወጣት ተጫዋቾች እንዲታዩ አድርገናል፡፡ በወቅቱ የክለቡ የገንዘብ አቅም ይህን እንድናደርግ ያስገድደን እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ያኔ ዳዊት እስጢፋኖስን አምጥተነው አስር ሺህ ብር መክፈል አቅቶን መከላከያ ገብቷል፡፡ ይህን ራሱ ተጫዋቹ መናገር ይችላል፤ ልምምድ ሰርቶ አብሮን ምሳ በልቷል፡፡ ክፍያው አልተቻለምና ወደ ሌላ ክለብ አመራ፡፡ ዳዊት ፍቃዱም ከአየር ኃይል ሊቀላቀለን መጥቶ ነበር፡፡ በገንዘብ ጉዳይ መስማማት አልተቻለም፡፡ ስለዚህ በዚያ መንገድ ልሰራ ችያለሁ፡፡ ስብሰባ ላይም ወጣቶችን እንድይዝ ድጋፍ ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ባህርዳር ላይ በሙገር በወዳጅነት ጨዋታ ሽንፈት ሲመጣ ቁጣ ተከተለኝ፡፡ ” ይሄ’ኮ ትልቅ ቡድን ነው፡፡ እንዴት?” ተብዬ ተጠየቅሁ፡፡

‘ አይ እኔ ቡድን እየሰራሁ ስለሆነ ነው፡፡’ የሚል ምላሽ ሰጠሁ፡፡ ከዚያ ውድድሩ ሲጀመር ጥሩ ጉዞ አደረግን፡፡ እንዲያውም ክለቡ ወጣቶች ላይ በሰራሁት ሥራ ነው ሆላንድ ሃገር ድረስ ልኮ የማስተማር ውለታ የዋለልኝ፡፡

ገና ወጣት አሰልጣኝ ሆነህ አንጋፋውን ስዩም አባተ ለመተካት መመረጥህ አልከበደህም?

ከስዩም ጋር አንድ ዓመት አብሬው ስለሰራው እንዲያውም ደፋር አደረገኝ፡፡ ከስዩም እጅግ በርካታ ትምህርት ወስጃለሁ፤ እኔ ራሴን ሆኜ ብጓዝም እርሱ ብዙ ነገር ሰጥቶኛል፡፡ ከዚያ ቀደም ከአስራት ኃይሌ፣ ከሐጎስ ደስታ፣ ከካሳሁን ተካ፣ ከአብርሃም ተክለሃይማኖትና ከሌሎችም የተማርኩት ብዙ ነው፡፡ ይበልጡን ግን ከስዩም አባተ ተምሬያለሁ፡፡ ስዩሜ (ነፍስ ይማር፡፡) እጅግ ሲበዛ የሥራ ሰው ነበር፡፡ እርሱ ለሥልጠና የተፈጠረ ነው፡፡ ያው ይናደዳል፤ ቁጣውንና ኩርፊያውን ከቻልክ ብዙ እውቀት ትቀስምበታለህ፡፡  ከእርሱ ጋር መስራት በትልቅ የአሰልጣኞች ት/ቤት እንደመማር ነው፡፡ እኔ በአሰልጣኝነት ህይወት እዚህ ለመድረሴ አብሬው መቆየቴ ጠቅሞኛል፡፡ ለአንድ ዓመት አብሬው በመሥራቴ በጣም እድለኛ ነበርኩ፡፡

ያኔ አንተ ወጣት አሰልጣኝ ነበርክ፡፡ ሁሉም እንደሚያውቀው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ ባለቤት ነው፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ጫና ያመጣል፡፡ ይባስ ብሎ ክለቡ በ1998 ከፌዴሬሽኑ ጋር እሰጣገባ ውስጥ ገብቶ በፎርፌ ነጥቦች ተቀነሰውበትም ነበር፡፡ ይህኛው ደግሞ ተጨማሪ ጫና ይፈጥራል፡፡ ይሁን እንጂ አንተ አንጋፎቹንና ወጣቶቹን አጣምረህ ሊጉን ለማሸነፍ ተቃርበሃል፤ በጥሎ ማለፉም ፍጻሜ ደርሰሃል፡፡ እነዚያን ፈተናዎች አልፈህ ለስኬት ጫፍ ደርሰህ የነበረው በምን መልኩ ተዘጋጅተህ ነው?

የማምንበትን ልምምድ በደንብ አዘጋጃለሁ፤ አሁንም የምሰራው እንደዚህ ነው፡፡ አሰላለፍን ፍጹም ወገናዊ አላደርግም፡፡ ተጫዋቾችን <Performance Based> በሆነ መንገድ እመርጣለሁ፡፡ ልምምድ ላይ ያለ አሳማኝ ምክንያት የማይገኝ፣ የሚቀርና የሚያረፍድ ተጫዋች አላስተናግድም፡፡ እኔ የጨዋታ ቀን እስኪደርስ ድረስ የመጀመሪያ አሰላለፌ ምስጢር ሆኖ ይቆያል፡፡ ልምምድ ላይ ያላቸውን በሙሉ ለመሥጠት የተዘጋጁ ልጆችን እመለከትና በማምንበትና ትክክለኛ ብዬ በወሰንኩት እዘጋጅና እጠብቃለሁ፤ ይህን ሳደርግ የትኛውንም ጨዋታ አልፈራም፡፡ አንዳንድ አሰልጣኞች ጨዋታ ይፈራሉ፤ ምግብ አልበላ ይላቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው በራስህ ሳታምን ቀርተህ ያንንም ይሄንንም ስታማክር ነው፡፡ ያኔ ተጠራጣሪ ትሆናለህ፡፡ በቡናም እያለሁ ሁሌም በአግባቡ እዘጋጅና ‘ ትክክለኛ ልምምድ አሰርቻለሁ፤ ተገቢ ተጫዋቾችን መርጫለሁ፤ የሚመጣውን ውጤት በጸጋ እቀበላለሁ፡፡’ የሚል ቃል ለራሴ እነግራለሁ፡፡ በወቅታዊ ብቃት እንጂ ‘እገሌ አንጋፋ ነው፡፡’ በሚል ተጫዋች አላሰልፍም ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ቡናን እንደተረከብኩ ለራሴ ያልኩት ‘ በቅድሚያ ራሴን ማስከበር አለብኝ፡፡ አለበለዚያ የማሰለጥነው ቡድን የረባ ቡድን አይሆንም፡፡’ ነው፡፡ በተለይ ትልልቅ ስም የነበራቸው ተጫዋቾች አሰልጣኝ፣ ተጫዋች፣ ሥርዓት፣ የቡድን አንድነት፣… እንዲያከብሩ ማድረግ ግድ ይላል፤ ወጣቶቹ አያስቸግሩም፡፡ በምክትልነት ስትሰራም ዋናውን አሰልጣኝ የምትገዘግዝ፣ አብረህ ከተጫዋቾች ጋር የምታድም፣ ነገ ተጫዋቾቹ ያግዙኛል በሚል አንድ ላይ የምትዶልት ከሆነ ራስህን ታስንቃለህ፡፡ እኔ ከሥዩም ጋር ብዙ ጊዜ ተጣልቻለሁ፡፡ “ካምፕ ሄደህ ምግብ ተቆጣጠር፡፡” ሲለኝ ‘ አልሄድም፡፡’ እል ነበር፡፡ ከሱሉልታ ልምምድ መልስ እኔ ፒያሳ ወርጄ ወደ ጦር ኃይሎች ነበር የምሄደው- ወደ ቤቴ፡፡ የጨዋታም ቀን እንደዚያ ነው የማደርገው፡፡ ምክንያቱም ለፓስታ አብረህ ስትጋፋ ወሬ ትጀምራለህ፤ የሚያከብርህ ይጠፋል፤ መናናቅ ይከተላል፡፡ ‘ ካምፕ ኃላፊ ይቀጠርና እርሱ ይቆጣጠር፡፡’ እል ነበር፡፡ ኃላፊው የቀረውን ተጫዋች፣ ከካምፕ ውጪ ያደረውን፣ የአመጋገብ ሥርዓቱን ይቆጣጠር፤ ከዚያ ሪፖርት ያቅርብ፡፡ እኔ የሥልጠና ባለሙያ ነኝ፡፡ ሥራዬ ሜዳ ላይ ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ ጭቅጭቅ ተነስቷል፤ ” ወደ ካምፕ ሂድ ስለው እርሱ ግን አይሄድም፡፡” በሚል ስዩም ቅሬታ ያቀርብብኝ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ጊዜ እየተኮራረፍን ሰዎች አስታርቀውናል፡፡ ሰዎችን ለማስደሰት ብዬ ሳይሆን ትክክለኛውን ሥራ ስለሰራሁ ጫና መቋቋም ችያለሁ፡፡ ሁሌም ለተጫዋቾቼ ‘ እኔ ማንንም ለማስደሰት ብዬ አልጥርም፤ ይህ አይነቱ አካሄድ ቡድን ያፈርሳል፤ በወገናዊነት አልሰራም፡፡ አሰላለፌም በልምምድ ላይ በምታሳዩት ትጋት፣ ሥነ-ሥርዓት አክባሪነትና ወቅታዊ ብቃት ላይ የተመረኮዘ ብቻ ነው፡፡ ቡድኔ ውስጥ ወሬ አመላላሽ አልፈልግም፤ ምክንያቱም ወሬ ለሚያቀብል Biased መሆን አልሻምና፡፡ ነገ ለወሬኛው ማድላቴን ካወቃችሁ የቡድን መንፈሳችን ይበጠበጣል፤ ክለባችንም ውጤት አያመጣም፡፡’ በማለት ይህን መልዕክት አስተላልፋለሁ፡፡ ተጫዋቾች በሞራል ወይም በወኔ የሚጫወቱት አሰልጣኙ ከአድልኦ የራቀ ከሆነ ነው፡፡ ‘እገሌ የደጋፊ ፍቅር አለው፡፡’ በሚል ከአቋሜ ዝንፍ አልልም፡፡

ከዋናው የቡና ቡድን አሰልጣኝነትህ ስትለቅ የክለቡን <B> ቡድን አሰልጥነሃል? 

አላሰለጠንኩም፡፡ በእርግጥ ” <B> ቡድኑን ያዝና አሰራ!” ተብያለሁ፡፡ ነገርግን ‘ አይ እኔ ለዋናው ቡድን እንጂ ለዚያ ቡድን አልተቀጠርኩም፡፡ ስለዚህ የ<B> ቡድኑን አላሰራም፡፡’ የሚል ምላሽ ሰጠሁ፡፡

“በቃ እንግዲያውስ እንስማማ!” ተባልኩ፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ያስተማረኝ ክለብ ስለሆነ ተስማምቼ የሶስት ወር ደመወዝ ተሰጠኝ፤ በሰላምና በፍቅር ለቀቅሁ፡፡  የአብርሃም ምክትል ሆኜ ግን የአስራት አዱኛን ቡድን እየሄድኩ እመለከት ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ነው እነ ምንያህልን ላሳድግ የቻልኩት፡፡ ምንያህልን ከቤቱ አስጠርተነው ነው ለዋናው ቡድን ያሰለፍነው፡፡ ከዚያ ባንክ ላይ ጎል አስቆጠረ፡፡

ኢትዮጵያ ቡናን ስትለቅ በክለቡ መልበሻ ክፍል የተጫዋቾች መከፋፈል እንዳስቸገረህ ገልጸሃል፡፡ በወቅቱ ያን ችግር መቆጣጠር ይከብድ ነበር?

አይ! እኔ እንኳን እቆጣጠራለሁ፡፡ ይሁን እንጂ ከአንዳንድ አንጋፋ ተጫዋቾች ጋር አልስማማም ነበር፡፡ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ነካህ ማለት ከደጋፊው ጋር ተጣላህ ማለት ነው፡፡ ያ ነገር ገጥሞኛል፡፡

በተለያዩ ክለቦች የተጫዋቾች አድማ ሰለባ ነበርክ? 

አይ! እኔ በቡና አንድ ስብሰባ ላይ ብቻ ትልልቅ ስም የነበራቸው ተጫዋቾች ብዙም እምነት ስላላሳደርኩባቸው የሃሳብ ልዩነት አንስተውብኛል፡፡ የዚያኔ ስብሰባውን ጥዬ ወጥቻለሁ፡፡ በመድንም የተወሰኑ ተጫዋቾች ከምርጫ ጋር በተያያዘ መጠነኛ ችግር ገጥሞኛል፡፡ እዚያም ከሁለት-ሶስት ነባር ተጫዋቾች አይበልጡም፡፡ ትንሽ በጥብጠውኝ በስሜታዊነት ተናግሬያቸዋለሁ፡፡ በተረፈ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ለእኔ ጥሩ ነገር እንዳላቸው አስባለሁ፡፡ እኔ በጣም ዴሞክራት ነኝ፡፡ በአምባገነንነትም አልታሰብም፡፡ ተጫዋቾች ውስጣቸውን አውቄ አብሮ የመስራት ልምድ አዳብሬያለሁ፡፡ በተለይ ኳስ የሚችሉ ተጫዋቾች በጣም ይወዱኛል፡፡ ኳስ ላይ ትንሽ ችግር ካለባቸው ጠላት ይሆኑኛል፡፡ ይህ ችግር ቡና ውስጥም ገጥሞኛል፡፡ እኔ ጎን ተቀያሪ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ልክ ጎል ስናገባ ሩቅ ሚስማር ተራ ድረስ ሄደው የአጥሩን ሽቦ እየነቀነቁ የሚጨፍሩ ነበሩ፡፡ ‘ ተዉ! አታጭበርብሩ! ሜዳ ላይ የሚጠበቅባችሁን ብቻ ሥሩ፤ ደጋፊ ማነሳሳት ምንም አይሰራም፡፡ ደጋፊ ማጣላት ምን ዋጋ አለው፡፡?’ እላቸዋለሁ፡፡ አንዳንዶች ደጋፊ እንዲወዳቸው የማያደርጉት ነገር የለም፡፡ ሜዳ ላይ ጥቅም የማይሰጡና <ዲሲፕሊንድ> ያልሆኑትን ስለምነቃባቸው ይጠሉኛል፡፡ እኔም ወጣትና እልኸኛ ስለነበርኩ ግትርነት አበዛለሁ፡፡ አሁን አሁን ግን ተጫዋቾችን አስቀምጬ በስርዓት እነግራቸዋለሁ፡፡ ‘ግልጹን ንገሩኝ፡፡ በአሰላለፍ ምርጫዬ የማታምኑ ከሆነ መለያየት እንችላለን፤ ከእናንተ የሚጠበቀው “ልውጣ!” ብቻ ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ ጸብ ውስጥ ፍጹም መግባት የለብንም፡፡ ልክ እንደ ውጪዎቹ “አሰልጣኙ እያሰለፈኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ መልቀቅ እፈልጋለሁ፡፡” በሉ፡፡ እኔ እፈርማለሁ፡፡’ ነው የምላቸው፡፡

በ2000 የካቲት ከቡና ለቀህ ወደ 2001 መድን ከመግባትህ በፊት የትኛውን ክለብ አሰለጠንክ? 

ወንጂን፡፡ ወንጂን የለቀቅሁት ኮንትራቴ ሳይገባደድ ነበር፡፡

ከዚያ መድንን ያዝክ?

አዎ! የወንጂ ኮንትራቴን ሳልጨርስ ወደ መድን መጣሁ፤ ትክክለኛ ሰዓት አልነበረም፡፡ አንደኛ ነገር ገ/መድህን ኃይሌ መድንን አለቀቀም፤ ለትምህርት ወደ ውጪ ቢሄድም ቀደም ብሎ ተጫዋቾችን መልምሎ ነበር፡፡ አዲስ የፈረሙም አሉ፤ ከነባሮች ደግሞ ያልተቀነሱ ነበሩ፡፡ እኔ ጥቅምት አካባቢ ነው መድንን የተቀላቀልኩት፡፡ “ገ/መድህን ውጪ ሃገር ቢሆንም ቡና ፈርሟል፡፡” የሚል ወሬ ይናፈሳል፡፡ የክለቡ ሰዎች ደግሞ ከገብሬ ጋር ኮንትራት እያላቸው “አንተ ቡድኑን አሰራ፡፡” አሉኝ፡፡ ጨዋታዎች ተጀምረው እንኳ በስታዲየም ውስጥ የመድን አሰልጣኝ ሲጠራ ገ/መድን ኃይሌ ነው የሚባለው፡፡ ከእርሱ ጋር ፍርድ ቤት ድረስ የዘለቀ መካሰስ ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ እንግዲህ እኔም የገባሁት “በማይሆን ሁኔታ ውስጥ ሆኜ ነው፡፡” ማለት ነው፡፡ ቡድኑን ራሴ ሰርቼ፣ ተጫዋቾቹን አደራጅቼ፣ በህጋዊ መንገድ ተቀጥሬ፣ ውሌ ለፌዴሬሽኑ ገብቶ፣ ….. ሥራውን መጀመር ሲገባኝ እኔ ግን ያንን ሳላደርግ ነው መድንን የያዝኩት፡፡ በመጨረሻ ላይ አራት ቡድን ሲወርድ መድንም ወረደ፤ በመጀመሪያው ዙር እኮ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የነበረ ቡድን ነው፡፡ ለሲቲ ካፑም ከጊዮርጊስ ጋር ለዋንጫ ቀርበን ነበር፡፡ ተጫዋቾቹ በአብዛኛው እኔ ያላሰባሰብኳቸው ነበሩ፡፡ በአሰልጣኝነት ህይወቴ መጥፎው ጊዜ ያ ነበር፡፡

በ2001 ከገ/መድህን ኃይሌ መልቀቅ በኋላ የተረከብከው መድን በሌሎች አሰልጣኞች ሥርም ከፕሪምየር ሊጉ ወርዷል፡፡ በ1996 እና በ2006፡፡ የአንተ ጊዜ ለምን ከሁሉ የከፋ ትችት አስከተለ? 

አዎ! የእኔ ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ እኔ ወደ ክለቡ ስገባ 95% ተጫዋቾች አልመለመልኩም፡፡ ገ/መድህን ውጪ ሄዶ ነበር፡፡ በእርሱ ጊዜ የነበሩ ተጫዋቾች አልተቀነሱም፡፡ እርሱ ሲመጣም በቀጥታ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ነው የሄደው፡፡ እኔም በወንጂ ኮንትራት እያለኝ ነው የመጣሁት፡፡ ነገርግን “ገ/መድህን አለለቀም፡፡” ይባል ነበር፡፡ በሲቲ ካፕ ለዋንጫ ስንደርስ ነው ለምርጫ ብለን ተጫዋቾች ያየነው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ያ ቡድን ቢቆይ እንዴት ደስ ባለኝ፡፡ መድን ለሶስት ጊዜያት ከፕሪሚየር ሊጉ ሲወርድ ” ክለቡ ጋር ችግር የለም እንዴ?” ተብሎ
ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በ2001 ቡድኑ በመጨረሻ ጨዋታው በሁለት ግብ ልዩነት ማሸነፍ ቢችል አንወርድም ነበር፡፡ እዚህ ደግሞ መብራት ኃይል ከጠንካራውና ለዋንጫ ከሚፋለመው መከላከያ ጋር ይጫወታል፡፡ የመውረድ ስጋት ያለብን ክለቦች በእኩል ሰዓት መጫወት ሲገባን እኛ ከአዋሳ ጋር ቀድመን እንድንጫወት ተደረገ፡፡ ቅሬታ ብናቀርብም የሚሰማን አጣን፡፡ እዚያ እኛ 2-1 ተሸነፍን፤ መብራት እዚህ 4-1 አሸነፈ፡፡ ነገር ግን የእኛ ጨዋታ ቀድሞ ስላለቀ እነርሱ ምን ያህል ግብ እንደሚያሳልፋቸው አውቀው ተጫወቱ፤ እኛ ወረድን፤ እነርሱ ተረፉ፡፡ ጉዳዩን መነጋገሪያ ያደረገው ያ ሁኔታ ነው፡፡ በእግርኳስ ህይወቴ በጣም ያዘንኩበት አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ከዚያ በኋላም ብዙ መላቀቆች ነበሩ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተጎዱ ብዙ ክለቦች አሉ፡፡

የመድን መውረድ የአሰልጣኝነት ህይወቴ እድገት ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖብኛል፡፡ ‘ መጀመሪያውኑ እንደ አሰልጣኝ ግራ ቀኙን በደንብ አይቼ ነበር መግባት የነበረብኝ፡፡’ የሚል ቁጭት ፈጥሮብኛል፡፡ አንዳንዴ ቤተሰብን፣ ደመወዝና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን ስናስብ በእንደዚህ አይነት መልኩ የምንጎዳበት ሁኔታ ይገጥማል፡፡ ከተገባ በኋላ እንኳ ነገሮችን አጢኖ መልቀቅ አንድ ነገር ነው፡፡ እኔ እንዲያውም ቡድኑ ጥሩ ሳይሆንም ውጤት ፍለጋ እስከ መጨረሻው ቀጠልኩ፡፡ እውነቱን ለመናገር በመጨረሻው ጨዋታ ከስታዲየም ወደ ሆቴል በእግር ነበር የሄድኩት፤ የሆነ ቦታ ላይ ስቅስቅ ብዬ አልቅሻለሁ፡፡ ‘ እግዚአብሄር ሆይ ለምንድን ነው የፈረድክብኝ?’ ብዬ አማርሬያለሁ፡፡ መድን በሃገሪቷ ጥሩ ኳስ የሚጫወት ትልቅ ቡድን ነው፡፡ ራሴ ተጫዋቾች ሰብስቤ፣ በራሴ እምነትና ፕሮግራም ባላዘጋጀሁት ቡድን ውስጥ ለምን ገባሁ?’ ብዬ ራሴን ወቀስኩ፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ከውጭ ፍትሃዊ ያልሆኑ ነገሮች ነበሩ፡፡ እኛ ጨዋታ ጨርሰን ቁጭ ብለን፥ እዚህ ተቀናቃኛችን ላለመውረድ ” አንድ ግብ ይቀረናል፤ አንድ ግብ ይቀረናል፤…..” እያሉ ለመትረፍ የሚጠበቅባቸውን አውቀው ይጫወታሉ፡፡

ክለቡ የመውረድ አፋፍ ላይ ከመድረሱም በፊት ቡድኑ የተከፋፈለ እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ እንዲያውም “መድን ለሶስት የተሰነጣጠቀ የተጫዋቾች ጎራ ይዟል፡፡” ተብሎ ታምቷል፡፡ ተጫዋቾቹ አንጋፋና ነባሮች፤ ገ/መድህን ያመጣቸውና ክፍሌ የመለመላቸው ተብለው የራሳቸውን ህብረት ፈጥረው ነበር፡፡ ይህ እውነት ነው?

አዎ! ትክክል፡፡ እኔ እነ ዓለማየሁ ዲሳሳ (ዴልፒዬሮ) ያሉበት ሶስት ልጆች አስፈርሜያለሁ፡፡

ታዲያ እኮ ይህ ዓመቱን ሙሉ የዘለቀ ችግር ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ እንዴት “መድን ይተርፋል፡፡” ብለህ አሰብክ? 

አይ! ወደ መጨረሻ ላይማ እኮ አሰባስቤያቸው ነበር፡፡ በስልጠናው ዓለም ውስጥ ከባዱ ፈተና የገጠመኝ መድን ውስጥ ነው፡፡ እኔ ምንም ላስተባብል አልፈልግም፡፡ እንደተባለው ለሶስት የተከፋፈለ የተጫዋቾች <ግሩፕ> ነበር፡፡ አርፍጄ መግባት አልነበረብኝም፡፡ ስብስቡ ሙሉ በሙሉ እኔ ያመንኩበት መሆን ነበረበት፤ ከነባሮቹንም ቢሆን እኔ አይቻቸው የመረጥኳቸው ብቻ መቀጠል ነበረባቸው፡፡ ተጫዋቾቹ ጎራቸውን ለይተው ቁጭ ያሉ ናቸው፡፡ ከነባሮቹ ውስጥ ግማሾቹ መቀነስ የሚገባቸው ነበሩ፡፡ ነገርግን እነዚህን ተጫዋቾች ወደ አንድ አምጥቼ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ሁሉ ደርሰን ነበር፡፡ ዘላቂ ግን አልሆነም፡፡

ክለቡን የተቀላቀልከው ውድድሩ ተጀምሮ ነው? 

ሊጀመር ሲል ዘግይቼ ነው መድን የገባሁት፡፡ወድድሩ እንደተጀመረ ሰሞን እኮ የተጫዋቾችና የአሰልጣኞች ስታፍ አባላት ስም ዝርዝር ለተመልካች ሲተዋወቅ “የመድን አሰልጣኝ- ገ/መድን ኃይሌ” ነበር የሚባለው፡፡

ለወጣቶች ተፈጥሯዊ ክህሎት ቅድሚያ የምትሰጥ፣ በጠንካራ ዲሲፕሊን የምትመራና ጎበዝ አሰልጣኝ እንደሆንክ የሚነገረውን ያህል በአሉታዊ ጎን የሚጠቀሱ ባህርያትም ይነሱብሃል፡፡
ምናልባት በተጫዋቾቹ በማዘን በምሬት የምትሰጠው አስተያየት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገርግን ክፍሌ ተጫዋቾቹን ” ቆይ-አጠፋችኋለሁ፡፡” እያለ ይዝትባቸዋል፡፡ የሚል አስተያየት የቀድሞ ጋዜጣ ላይ ማንበብ ችያለሁ፡፡ እውነት ይህንን ትል ነበር?

አዎ እናገር ነበር፡፡ የሚያቃጥሉኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው እንዲያውም እኔና ቡድን መሪውን ያስፈራራናል፡፡ እኔ ወደ ልምምድ ሜዳ ቀድሜ ነበር የምደርሰው፡፡ አሁን ስሙን መጥቀስ አልፈልግም፤ ግን ሜዳ ላይ ይሳደባል፡፡ ‘አጠፋሃለሁ!’ እንዳልኩት ደመወዙን ከ2000 ብር ወደ 50 ብር አድርሼዋለሁ፡፡ ከአሰላለፍ ውጪም አድርጌዋለሁ፡፡ የሚፈራ ተጫዋች ነበር፡፡ እኔም ቀጥቼዋለሁ፡፡ ዛሬ ሥርዓት ያልያስያዝከው ነገር ነገ የሚፈትንህ ችግር ይሆንብሃል፡፡ በሲቲ ካፕ ላይ የተለያዩ ዕድሎችን ሰጠሁት፤ ጥሩ አልነበረም፡፡ በውድድር ላይም አየሁት፤ አላሳመነኝም፡፡ ጭራሽ ሌላ ነገር ውስጥ ገባ፤ ማስፈራራትና ትዕቢት፡፡

‘የቡድን መንፈስ የሚያደፈርስ፣ ቡድን የሚከፋፍል፣ እኔ በምለው መንገድ የማይጓዝና የሥልጠና ሒደቱን የሚያደናቅፍ ተጫዋች ይወገዳል፡፡’ ይህ አምባገነናዊ ትዕዛዝ ከየት የመጣ ነው? የቀድሞ አሰልጣኞችህ ያሳረፉብህ ተጽዕኖ ይሆን? የተበላሹ ነገሮችን ለማስተካከልስ ሰርቷል ዘዴው?

በመድን አልሰራም፡፡ አስቸጋሪዎቹን ቀንሰህ በሌሎች የተሻሉ ተጫዋቾች በመተካት የተበላሹ ነገሮችን ለማስተካከል ጊዜው አልነበረም፡፡ ራስህ የመረጥካቸው ተጫዋቾች አያስቸግሩም፡፡ ሥልጠናህን ያውቃሉ፤ የምትፈልገውን ይረዳሉ፡፡ የቆዩት ግን ይፈታተኑሃል፤ ከኮሚቴዎች ጋር ቅርበት አላቸው፡፡ በመድን ትልቁ ችግር ነባሮቹ ተጫዋቾች ቢሮ ይሄዳሉ፡፡ ‘ አንድ ወደ ቢሮ የሚሄድ ሰው ይኑርና አጠፋሃለሁ፡፡’ ብያለሁ፡፡ ‘ ከእኔ በፊትም ቢሮ ትሄዳላችሁ፤ ወይ ቢሮውን አልያም ሜዳውን ምረጡ!’ እላቸዋለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ የመድን ኮሚቴዎች ብዙ ናቸው፡፡ አስራ ምናምን ይደርሳሉ፡፡ ተጫዋቾቹ አራት- አምስት ይሆኑና የኮሚቴ አባላቱ ጋር ይሄዳሉ፡፡ በዚያ ላይ ጉዳዮች በቶሎ እንዲፈጸሙ የትራንስፖርት ክፍል ኃላፊው- የትራንስፖርት ኮሚቴ፣ የፋይናንስ ክፍል ኃላፊው-የፋይናስ ኮሚቴ፣ የቴክኒክ ኮሚቴው- ከቀድሞ ተጫዋቾች፣….. አመራረጡ እንዲህ ነበር፡፡ የቡድን መሪው የቀድሞ የክለቡ ተጫዋች አብርሃም ነበር፡፡ እርሱ እንዲያውም በደንብ ያግዘኝና ይረዳኝ ነበር፡፡ ምን ያህል እለፋ እንደነበር ያውቃል፡፡ እና ተጫዋቾቹ አንተን የማይደግፍህ ኮሚቴ ኃላፊ ጋር ሄደው ነገሮች ይቆላለፉብሃል፡፡ ለምሳሌ ከግዢ ኮሚቴው ጋር ችግር ካለብህ ኳሶች እንዲገዛ ሲታዘዝ ተፈጻሚ ሳያደርገው ሐሙስ-ሐሙስ የሚካሄደው ስብሰባ ያልፋል፡፡ መድን ሁሉም ነገር የተሟላለት ክለብ ነበር፡፡ አቅሙ ከፍተኛ የሆነ፣ የራሱ ጥሩ የልምምድ ሜዳ ያለው፣ አመቺ የተጫዋቾች ካምፕ የያዘ፣….. ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችል ክለብ ነው፡፡ ነገርግን ሥር-ነቀል የአደረጃጀት ለውጥ ይፈልጋል፡፡ አሁንም ያለው በፊት የነበረው ነው፡፡ በተጫዋቾች አስቸጋሪ ባህርያት የተፈተንኩበት ክለብ መድን ነው፡፡

በ2001 መጨረሻ ከመድን ለመልቀቅ ስትቃረብ ግን ” ለክለቡ መውረድ ተጠያቂው እኔ ነኝ፡፡” በማለት ሙሉ ኃላፊነት ወስደሃል፡፡ የአለቆችህን ሆድ ለማራራትና መልቀቂያህን ለመውሰድ ስትል በጣም ዲፕሎማት ሆነህ ነበር እንዴ?

እውነት ለመናገር ያን ያልኩት መልቀቂያ ለማግኘት ብዬ አልነበረም፡፡ በየትኛውም የሊግ እርከን የመሥራት አቅም እንዳለኝ አምናለሀ፡፡ በራሴ ትልቅ እምነት አለኝ፡፡ በመድን “መጀመሪያውኑ እዚህ ክለብ መግባት አልነበረብኝም፡፡” የሚለው ሰበብ አይሰራም፡፡ ምክንያቱም በገዛ ፈቃድ ኃላፊነቱን መልቀቅ ይቻላልና፡፡ ከሰራሁ በኋላ “ኮሚቴው ያበሳጨኛል፤ የምፈልገውን አያቀርቡልኝም፤….” ብል ምን ትርጉም ይሰጣል? የዚያን ጊዜ ትክክል ያልሆኑ ምልክቶችን ሳይ እንደ አሰልጣኝ Resign ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ያን ላለማድረጌ ተጠያቂው እኔ ነኝ፤ በቃ የራሴ ጥፋት ነው፡፡ ሰራሁ፤ ከዚያ በኋላ ምክንያት ማቅረብ አልፈልግም፡፡ ቡድኑ ወርዷል፤ ኃላፊነቱ የእኔ ነው፡፡ በቃ! ትዝ ይለኛህ- ጋዜጠኛ አበበ ግደይ ቀጥታ በስልክ ጠይቆኝ ‘ ኃላፊነቱ የእኔ ነው፡፡’ አልኩ፡፡ ብዙ ሰው ነው የተገረመው፡፡ ‘መግባት አልነበረብኝም፤ መሃል ላይም መልቀቅ ነበረብኝ፤ ነገርግን አልሆነም፡፡ ከነችግሩ ኃላፊነቱ የእኔ ነው፡፡’ ብዬ በሚዲያ መናገሬን ሲሰሙ የመድን ሰዎች ደስ አላቸው፤ መልቀቂያዬም ወዲያው ተሰጠኝ፤ የሶስት ወር ደመወዝም በተጨማሪ ተቆረጠልኝ፡፡

መድን በወረደበት ክረምት ድምጽህ ጠፍቶ ሰነበትክ፡፡ በእርግጥ በወቅቱ <መድፈኛ ሜዳ> የተሰኘ ጋዜጣ ላይ የሶስት ሳምንት ትምህርት እየተከታተልክ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ የምን ትምህርት በመከታተል ያን አስከፊ ክረምት አሳለፍክ? የሥነልቦና ግንባታ፣ የቋንቋ፣ የኮምፒዩተር፣..?

ቋንቋ እየተማርኩ ነው ከዚያ ሙድ ለመውጣት የጣርኩት፡፡ አሁንም ቢሆን ጠፋ ብያለሁ፡፡ ይታያችሁ እንግዲህ ሰበታን ዓመቱን ሙሉ ያለ ሽንፈት መርቼ አሁንም ግን ከአሰልጣኝነቱ ራቅ ብያለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች በስልክና በማህበራዊ ድረገጾች ይጠይቁኛል፡፡ አንዳንዴ ወጣ ብለህ ማሰብ የሚኖርብህ ጊዜ አለ፡፡ አሁን እኔ የማሰብ ጊዜዬ ላይ ነኝ፡፡ የትኛውንም አይነት መጻህፍት ፖለቲካውን፣ ልቦለዱን፣ የእግርኳሱን፣…..ወዘተ አነባለሁ፡፡ ሁለት ጎረምሳ ልጆች አሉኝ፤ ከእነርሱ ጋር ሻይ-ቡና የመባባያ ጊዜ አሳልፋለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ከሰፈር አልወጣም፤ ነገርግን ኳስ ሲኖር መኪናዬን ይዤ እየሄድኩ የሰፈርም ጨዋታ ቢሆን አያለሁ፡፡ ‘እነዚህን ሁሉ ነገሮች አጥቻለሁ ለካ!’ እላለሁ፡፡ በፊት በልምምድ ሜዳ ሁለትና ሶስት ሰዓታት ነው የምታሰለጥነው፤ ከዚያ በጊዜ ወደ ቤትህ ትመጣለህ፤ ነገርግን የምታስበው ስለ ነገህ ነው፡፡ በዚህ ጊዜህ ግን ስክን ብለህ አዕምሮህን ታሳርፋለህ፤ ለቤተሰብህ ጊዜ ትሰጣለህ፡፡ ደስ ይልሃል፡፡ ራሴን <Charge> እያደረግሁ ነው፡፡ የአሰልጣኝነት ሥራው እኮ ከባድ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ድሮ በጣም ድሮ አስቸጋሪ ነበርኩ፤ የማደርጋቸውን ነገሮች በግልጽ ነበር የማደርገው፤ በእርግጥ ይህ ባህሪዬ ጎድቶኛል፡፡

ከዚህ እውነታ ጋር የተያያዘ ገጠመኜን ላጋራችሁ፡፡ መድን ከመቀጠሬ በፊት ሰላሳ ሰው ተወዳድሮ ነበር፡፡ ለመጨረሻ ቃለመጠይቅ የቀረቡ አሰልጣኞች ” መጠጥ ትጠጣለህ?” ለሚለው ጥያቄ ” አይ! አልጠጣም፡፡” የሚል ምላሽ ነው የሰጡት፡፡ እኔ ግን ግልጹን ነበር የተናገርኩት- ‘አዎ! እጠጣለሁ፡፡ እንዲያውም ህዝብ የሚያየኝ ቦታ ላይ ነው የምጠጣው፡፡’ ነው ያልኳቸው፡፡ ‘ ሥራ አስፈጻሚያችሁ ማታ ዊስኪ ይጠጣ- አይጠጣ ምንድነው ችግሩ ሥራውን በአግባቡ እስከሰራ ድረስ?’ ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ ‘ እኔ በአሰልጣኝነት ዘመኔ ሰክሬ ወደ ሥራ መጥቼ አላውቅም፤ ” ሥራ አይችልም፡፡” ተብዬም አላውቅ፡፡ አርፍጄ እንኳን እኮ አላውቅም፡፡’ አልኳቸው፡፡ መረጡኝ፤ ቀጠሩኝ፡፡ ስትዋሽ በራስህ እምነት እንደሌለህ ነው የምታሳየው፤ ስለዚህ እቅጯን መናገር፡፡ ሰዎች በስታዲየም ዙሪያ ስጠጣ እያዩኝ እንዴት ነው ‘አልጠጣም፡፡’ ብዬ ልል የምችለው? ከጓደኞችህ ጋር ቢራ ይዘህ ስትዝናና ሰዎች እያዩህ ልትዋሽ አይገባም፡፡

እኔ ከፕሮጀክት ጀምሮ፥ በመብራት ኃይል፣አየርመንገድና ኢትዮጵያ ቡና በርካታ ወጣት ተጫዋቾችን አሳድጌ ለትልቅ ደረጃ ማብቃቴ  በራስ የመተማመን ስሜቴን ከልክ በላይ ሳያደርገው አልቀረም፤ ነገር ግን ይህ የ<Over-Confidence> ነገር የጎዳኝ ይመሥለኛል፡፡ አሁን ግን እንዲሁ ዝም ብዬ አልታይም፤ ከሥራ መልስ በጊዜ ወደ ቤቴ ክትት ነው፡፡ ሚዲያ ላይም አልቀርብም፤ ስታዲየምም የምገባው በሚስማር ተራ በኩል ነው፡፡ ስወጣም ወደ ቤት ነኝ፡፡ ስታዲየም ዙሪያ ከታየሁ ስንት ዓመቴ፡፡ ዛሬ እንኳን ይኸው ከብዙ ጊዜያት በኋላ ከእናንተ ጋር ግዮን ሆቴል ተገናኘን፡፡ ስታዲየም አካባቢ እኮ በቃ የድሮ መዋያዬ ነበር፡፡ በየቦታው መታየት ጥሩ አይደለም፤ ሰዉ አዛብቶ ሊያወራብህ ይችላል፤ ስለዚህ እንደ አሰልጣኝም ሆነ እንደ ግለሰብ ጥንቁቅና አርአያ መሆን ይጠበቅብሃል፡፡

ይቀጥላል…


[ክፍል 1 – ቀደምት የአሰልጣኝነት ዓመታት]


©ሶከር ኢትዮጵያ