ምዓም አናብስት ቡርኪና ፋሷዊ አማካይ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል

ፕሪምየር ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታዎች ሙሳ ዳኦን ለማስፈረም ተቃርበዋል።

በክረምቱ ከቡድናቸው ጋር ለሳምንታት ልምምድ ሰርቶ በጥቅማ ጥቅም ሳይስማማ የተመለሰው ቡርኪና ፋሷዊው አማካይ ከዚህ ቀደም የግብፆቹ አስዋን እና አልመስሪን ጨምሮ ለአል ሐማም እና አል ጃሀራ ክለቦች ተጫውቷል። ሙሳ ባለፈው ሳምንት መቐለ ሰበታን ባሸነፈበት ጨዋታ ከግብፃዊው ወኪሉ አብዱራህማን መግዲ ጋር በመሆን ጨዋታውን የተከታተለ ሲሆን ከመቐለ ጋር ዝውውሩን ካጠናቀቀ በሁለተኛው ዙር ቡድኑን ማገልገል ይጀምራል።

በክረምቱ ጋብርኤል አሕመድ ወደ ፋሲል ከነማ በማምራቱ እንዲሁም አምበሉ ሚካኤል ደስታ በጉዳት ከሜዳ መራቁ ተከትሎ በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ የአማራጭ እጥረት የገጠማቸው አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ አማካዩ ወደ ቡድኑ ከተቀላቀለ ክፍተቱን ይሸፍንላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት ያገለገለው ፍሊፕ ኦቮኖ፣ ላውረንስ ኤድዋርድ እና ኦኪኪ ኦፎላቢን በቡድናቸው የያዙት 70 እንደርታዎቹ ይህን አማካይ የሚያስፈርሙ ከሆነ የውጭ ሀገር ተጫዋቾቻቸውን ቁጥር ወደ አራት ከፍ ያደርጋሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ