የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቀጣይ ወር በአፍሪካ ሴቶች ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ለሚጠብቃቸው የሉሲዎቹ ዋና እና ረዳት አሰልጣኞች ውላቸውን ሊራዘም ነው።
ፌዴሬሽኑ የሴካፋ የሴቶች ዋንጫ እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያን አስመልክቶ ጥቀምት ወር ላይ የሉሲዎቹ ዋና አሰልጣኝ እንዲሆኑ አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛውን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙ ይታወቃል። አሰልጣኝ ብርሀኑም በምክትልነት አሰልጣኝ መሠረት ማኒ እና የግብጠባቂ አሰልጣኝ ሽመልስ ጥላሁንን መሾማቸው ይታወሳል። ጥር 17 ቀን የመጀመርያ የውል ዘመናቸው የሚጠናቀቀው አሰልጣኞቹ በቀጣዩ ቀናት ለተጨማሪ ወራት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሚያቆያቸውን አዲስ ውል ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በቅድመ ማጣሪያ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከጁቡቲ ጋር የተደለደሉት ሉሲዎቹ ይህን ዙር ካለፉ ሁለተኛ ማጣርያቸውን ከሞሮኮ አቻቸው ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።
አሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ወደ ታንዛኒያ የሴካፋ ውድድር ከማቅናታቸው በፊት ይህን ለመገናኛ ብዙሀን መናገራቸው የሚታወስ ነው
“ላረጋግጥላችሁ የምወደው በቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ብሔራዊ ቡድኑን ማሳለፍ ይጠበቅብኛል፤ በእቅዴ መሠረት ይህን የማላሳካ ከሆነ ቃል የምገባላችሁ ነገር ቢኖር በነጋታው በገዛ ፍቃዴ ሥራዬን እንደምለቅ ነው፡፡”
ከዚህ ቀደም ስለ አፍሪካ ዋንጫው ድልድል የሰራነውን ዘገባ ለማንበብ ሊንኩን ይጫኑ | LINK
© ሶከር ኢትዮጵያ