የግል አስተያየት | ተግባራዊ ሥራ ላይ ቢተኮር…

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚሁ ዓምድ ሥር “ለእግርኳሳችን የማይጠቅመው የባለሞያዎቻችን ንትርክ” በሚል ርዕስ አስተያየቴን አስፍሬ ነበር፡፡ ይህንን ግላዊ ዕይታዬን ተንተርሰው የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሥነ-ልቦና እና የእግርኳስ መምህር የሆኑት አቶ ሳሙኤል ስለሺ ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ እኚህ ባለሞያ የጀማሪ ኢንስትራክተርነት ስልጠና በወሰድኩበት ጊዜ የሥነ-ልቦና ትምህርትን ግሩም በሆነ መንገድ አስተምረውኛል፡፡ በግል የኢትዮጵያን እግርኳስ በአዎንታዊ መልኩ የመቀየር እምቅ አቅም አላቸው ብዬ ከማስባቸው ሰዎችም ውስጥ አንዱ እርሳቸው ናቸው፡፡

የሳሙኤል ስለሺ ፅሁፍ | LINK

ሃሳብን-በ-ሃሳብ የመሞገት ልማድ እምብዛም ባልሰፈነበት የሃገራችን እግርኳስ ከባቢ ቀደም ሲል ባነሳሁት ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ የእርሳቸውን አስተያየት ግሩም በሆነ ብዕራቸው- ስፋትና ጥልቀት ያለውን ማራኪ ሃሳብ አስፍረዋል፡፡ እኔም ከእርሳቸው ፅሁፍ በመነሳት ተጫማሪ ሦስት ሃሳቦችን ለመሰንዘር ወድጃለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን የግል አስተያዬቴን በአፅዕኖት በማንበብ እኔን ከማሸመቀቅ እና ከማስደንገጥ ይልቅ ሃሳባቸውን አስተማሪና ጨዋ በሆነ መንገድ ስለገለፁ አቶ ሳሙኤል ስለሺን ሳላመሰግን አላልፍም፡፡

★ ዕውነት ክርክሩ “በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች”ብቻ የሚያደርጉት ነውን?

ይህ “ክርክር” ሥር የሰደደ፣ መቋጫ ያልተበጀለት፣ የማያባራና በየጊዜው የሚደጋገም እንዲሆን ያደረጉት አቶ ሳሙኤል እንዳሉት “ተጫውተናል!” ብለው ራሳቸውን ከሚኮፍሱት ወገኖች “በጣት የሚቆጠሩቱ” ቢሆኑም ችግሩ ሥር ሰዶ በሁለቱ ጎራ ያሉ ሰዎች የጎሪጥ እንዲተያዩ እና ተባብሮ መስራትን ቸል አንዲሉ ካደረገ ሰንበትበት ብሏል፡፡ ይህን ሃሳቤን በአንባቢውም ይሁን በአስተያየት ፀሃፊው ላይ ለማስረፅ ሩቅ አልሄድም፡፡ የስልጠና ኮርሶች በተካፈልኩባቸው አንዳንድ አጋጣሚዎች በሁለቱ ወገኖች ዘንድ አለመተማመን እንደነገሰና መረዳዳት የሚለው ሃሳብ ፈፅሞ እንደማይታይባቸው አለፍ ሲልም አንደኛው ወገን “…እነርሱ (በስፖርት ሳይንስ የተማሩትን) እኮ ሜዳ ላይ አይችሉም፡፡” ሲል ሌላኛው ወገን ደግሞ “…(በአሰልጣኝነት እየሰሩ ያሉትን) በትምህርት በሚገኝ የንድፈ-ሃሳብ እውቀት ‘ዜሮ’ ናቸው፡፡” እየተባባሉ የመናናቅ ሃሜቶች ሲሰናዘሩ በተለያዩ ጊዜያት ለመስማት ችያለሁ፡፡ ክፍል ውስጥ በሚሰጡ በጋራ የሚሠሩ የቡድን ሥራዎች ላይም ቢሆን አብዛኛውን ጊዜ በዚሁ የቡድን ክፍፍል መንገድ ጎራ ተመዳድበው ማየት የቅርብ ጊዜ ገጠመኜ ነው፡፡ ይህንን ኹነት ከሁለቱም ጎራ ውጪ የሆንን አሰልጣኞች ደግመን-ደጋግመን ያስተዋልው ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ክርክሩ ላይ በቀጥታ ተሳትፎ የሌላቸው አንዳንድ በሁለቱም የሥራ ዘርፎች ውስጥ የሚገኙ ባለሞያዎች በመገናኛ ብዙሃን እና በማኅበራዊ ድረ-ገጾች አልፎ አልፎም ቢሆን ይህንን ሃሳብ ሲያንፀባርቁ ተመልክቻለሁ፡፡ ይህኛው የእኔ አተያይ ስህተት ቢሆን እንኳ ጉዳዩ ሌሎችም ላይ ተመሳሳይ ውዥንብር መፍጠሩ አልቀረምና እንደ እርሶ ያለ የብዙ እውቀት ባለቤት የሆነ ሰው ዕውነታውን በግልፃ ማስረዳት ይጠበቅበታል፡፡ “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲሉ ይህ አሳሳች ግንዛቤ ቀስ በቀስ እየተንሰራፋ ነውና ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዳይሸጋገር ማድረግ የእርሶ እና የመሰሎችዎ ባለሙያዎች ሃላፊነት ነው እላለሁ፡፡

★ የእግርኳስ ሥራ በተግባር የሚታይ ነው

ክርክሩ “መቼ ተጀመረ?”፤ “ማን ጀመረው?”፤ “ጥፋተኛ ማነው?” የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎችን በአስተያየቴ ለመመለስ አልሞከርኩም፡፡ ይህንን ያላደረኩት ግን አቶ ሳሙኤል እንዳሉት ስላደረብኝ ሳይሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከሥራ ይልቅ ወሬ ስለሚበረታ “ሥራው ላይ እናተኩር” ለማለት ነው፡፡ በእግርኳስ ተገቢውን ሥፍራ ስለመነፈግ ከተነሳማ በዚሁ ዓምድ “ወጣት አሰልጣኞች እና መዳረሻችን” በሚል ርዕስ እንዳሰፈርኩት “የተጫወተ ያሰልጥን!” በሚለው ሃሳብና አግላይ ውሳኔ ከተጎዱት ውስጥ አንደኛው ነኝ፡፡

እርስዎ እንደገለፁት መብታችሁን ለማስከበርና በእግርኳሳችን ላይ “አታስፈልጉም” መባላችሁን ለመቃወም “ተጫውተን አልፈናል” ከሚሉት አንዳንዶች ጋር በሃሳብ ከተፋለማችሁት ውጪ በተለያዩ አጋጣሚዎች “እግርኳሱን እኛ ካልመራነው አይለወጥም” የሚሉ ከተማሩት ውስጥ አሉ፡፡ እንዲሁም “እግርኳስን ተጫውተን ያለፍነው ቦታውን ካልያዝነው እግርኳሳችን አያድግም፡፡ ስፖርት ሳይንስ የተማሩት አያስፈልጉም፡፡ ከእኛ በላይ ላሳር!” የሚሉም እንዳሉ በአስተያየቴ አንስቻለሁ፡፡ የአስተያየቴ ዋነኛ ሃሳብ ሁለቱም ወገኖች ይብዛም-ይነስ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የመሥራት እድል አግኝተው እንዳልተጠቀሙበት ማሳየት ነው፡፡ የሁለቱንም ወገኖች ውጤት አልባ ጉዞ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ ምናልባት እርስዎ እንዳሉት የስፖርት ሳይንስ ባለሞያዎች ሆነው የመሥራት ዕድል ያገኙት ሰዎች በወገንተኝነት፣ በፖለቲካ አቋም፣ በብሔር፣ በጥቅም ወይም እርስዎ በጽሁፍዎ በጠቃቀሷቸው ሌሎች ምክንያቶች ሥፍራውን ይዘው ከሆነ ይህን ማጋለጥ እና መሞገት እንዳለብዎ አምናለሁ፡፡ በዚህ ዙሪያ በቂ ማስረጃ እንዲሁም እውቀት ስለሌለኝ ምንም ማለት አልችልም፡፡ አሁንም ግን ክለብ ጭምር ይዘው እየሰሩ ያሉ የስፖርት ሳይንስ ባለሞያዎች እንዳሉ ማንም መመስከር ይችላል፡፡ እነዚህ ባለሞያዎች በዘመናዊ ስልጠና፣ በጨዋታ አቀራረብ እንዲሁም እግርኳሳዊ በሆኑ ሌሎች ጉዳዮች የሚታይ ለውጥ ማሳየት አለባቸው፡፡ ከዚህ በፊት በሰጠኋቸው አስተያቶች ደጋግሜ እንዳነሳሁት የኢትዮጵያ እግርኳስ አንድ ዘርፍ ላይ ብቻ በሚሰራ ሥራ አያድግም፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ጫና ወስጥም ተሁኖ የሚታይ አስተዋፅኦ ማበርከት እና እምቅ አቅምን ማሳየት ይቻላል ባይ ነኝ፡፡

በሌላ በኩል ቀደም ባለው አስተያየቴ ለመጠቆም እንደሞከርት በዩንቨርሲቲ አካባቢ ያለውን ጥልቅ እውቀት፣ እምቅ አቅም፣ ሰፊ የእሳቤ አድማስ በመጠቀም የረጅም ጊዜ ስልታዊ እቅድ በማዘጋጀት፣ እዚያው በሰለጠኑ ባለሞያዎች ውጤታማ ሥራ መስራት ይቻላል፡፡ አሁንም ደግሜ መጥቀስ የምፈልገው በሁለቱም ‹ጎራዎች› በሚወዛገቡት ወገኖች ዘንድ በአደባባይ የሚታይ እግርኳሳችን ላይ በጎ ተፅእኖ የፈጠረ ሥራ አልተሰራም፡፡ የእግርኳስ ፍሬውም ገለባውም የሚለየው ደግሞ በአደባባይ ነው፡፡

★”ፍቃድ ያለው ሁሉ ያሰልጥን”

ብዙ በለፋንበት፣ ጥረን-ግረን አንጻራዊ ልምድና በቂ እውቀት በቀሰምንበት፣ ያለመታከት  በተመክሮም-በወረቀትም በተማርንበት ሞያ አንዱ “ፈቃጅ” ሌላው “የበዪ ተመልካች” ፥ አንደኛው “ልጅ” ሌላኛው ደግሞ “የእንጀራ ልጅ” የሚሆንበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስፖርት ሳይንስ ተመርቀው ከወጡት ባለሞያዎችም በላይ በከተማችን በርካታ አካባቢዎች እኔን ጨምሮ ሙሉ ጊዜያችንን እና ኑሯችንን ታዳጊዎችን ለማሰልጠን የምናውል ብዙዎች ነን፡፡ ሃገራችን እግርኳሷ እንዲዘምን ከልባችን የምንሻ፣ ይህንንም ለማሳካት ሌት-ተቀን የምንጥር፣ ያለምንም ጥቅም ራሳችንን ለሙያው አሳልፈን የሰጠን ወጣት አሰልጣኞች አለን፡፡ በዘመናዊ አስተሳሰብ የተቃኘ የእግርኳስ አመራር አጥተን- ውስጣችን የሰረጸው ጥልቅ የመሥራት ፍላጎት፣ ዘወትር ለመሻሻል የምናደርገው ያላሰለሰ ጥረት፣ በምንችለው አቅም አሉታዊ ተጽዕኖዎችን  ተቋቁመን ውጤት ለማሳየት የምንተጋ ብዙዎች ነን፡፡ እኛን መሰል ወጣት አሰልጣኞች በተለይ “የተጫወተ ያሰልጥን!” በሚለው አመለካከት የተሸበበው አሰራር የችግሩን ገፈት ቀማሽ አድርጎናል፡፡ ለ”Merit” ቦታ የሌለው እግርኳሰችን
” ከእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወታቸው በኋላ ስራ ለሌላቸው የቀድሞ ተጫዋቾች ስራ መፈጠር አለበት፡፡” በሚል የድጎማ ይዘት ያነገበ ደካማ አመላከከት እንዲሰፍን እድል ፈጥሯል፡፡ ያለ ምንም ስኬት ከአንደኛው ክለብ ወደ ሌላኛው ክለብ  የሚዘዋወሩት አሰልጣኞቻችንም ይህን ለእግርኳሰችን እድገት ጠንቅ የሆነ አመለካከት ከክለብ ውጪ በሆኑ ቁጥር በመገናኛ ብዙሃን እያራገቡ የብዙ ሰዎችን ህልም እያጨናገፉ ነው፡፡እኔም ልክ እንደ አቶ ሳሙኤል “ፍቃድ ያለው ሁሉ ማሰልጠን ይችላል፡፡” የሚል አቋም አለኝ፡፡

የሥራ እድል ማግኘትና በአሰልጣኝነት ሙያ መጎልበት “Merit” ተኮር መሆን አለበት ባይ ነኝ፡፡” የተጫወተ” ፣ “የተማረ” ፣ እንደ እኛ “በታዳጊ ስልጠና አልፎ የመጣ” አሰልጣኝ ሥራው የሚመዘነው በሰራበት ቦታ ባስመዘገበው ውጤት መሆን አለበት፡፡ ይህን የአሰራር መዋቅር ከዘረጋንና ተግባራዊ ካደረግን ለሃገራችን እግርኳስ “ዘየድን!” የምንልበት ጊዜ ይኖረናል፡፡ የማይጠቅም ወሬ እያራገቡ፣ በጥቅማ ጥቅሞች እየተሳሰሩ፣ የራሳቸውን በር ለማስከፈት-የሌሎች እንዲዘጋ እየጣሩ ረብ የለሽ ፕሮፓጋንዳ የሚነዙትን አካላት በቀላሉ ከስዕሉ ማስወገድ ይቻላል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚሁ ርዕስ ጉዳይ ዙሪያ በሰጠሁት አስተያየት ንትርክ ውስጥ የመግባት ሃሳብ ባይኖረኝም አቶ ሳሙኤል እንደሰጡት አይነት ጥልቅ የባለሞያ እይታ እንዲኖረን እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት የታከለበት የሃሳብ ውይይቱ እንዲበረታታ ፍላጎቴ ነው፡፡ አቶ ሳሙኤል የእኔን ፅሁፍ ተንተርስው ለእኔም ይሁን ለሌሎች ሰዎች በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን ጉዳይ በራሳቸው ዕይታ ስላስቀመጡልን በድጋሚ ምስጋናዬን በአንባቢ ስም ማቅረብ እወዳለሁ፡፡


ስለ ፀሐፊው

የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ  ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ