ቤትኪንግ ለሁሉም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል

የውድድሩን የስያሜ መብት የገዛው ቤትኪንግ ለሁሉም ክለቦች መልካም ዜና የሆነ አንድ አዲስ ነገር ይዞ እንደመጣ ተሰማ።

የ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ባሳለፍነው ሳምንት በተካሄዱ የመጀመርያ ሳምንት ውድድር መጀመሩ ይታወቃል። ለኢትዮጵያ እግርኳስ በርከት ያሉ ትሩፋቶችን ይዞ የመጣው የዘንድሮ የውድድር ዓመት በጥሩ ሁኔታ የመጀመርያ ሳምንቱ መጠናቀቁ ይታወቃል። አሁን እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ ከዲኤስቲቪ የስያሜ መብት ስፖንሰር በመሆን ውድድሩን ለጊዜው ባልተገለፀ በከፍተኛ ገንዘብ የገዛው ቤትኪንግ 13 ክለቦች የሚለብሱትን ማልያ በተቀመጠው መስፈርት መሠረት በራሱ ወጪ ሊገዛ እንደሆነና በዚህ ጉዳይ ለመነጋገር ታኅሣሥ 12 ቀን 04:00 በአዲስ አበባ ስታዲየም የክለብ ሥራ አስኪያጆች እንዲገኙ ስብሰባ ጠርቷል።

ከትጥቅ አምራቾች ጋር ስምምነት ያላቸው ክለቦች እና ሌሎች የሚነሱ ጉዳዮች በስብሰባው ላይ የመወያያ ርዕስ ይሆናሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ሶከር ኢትዮጵያ በአንደኛ ሳምንት የተመለከተቻቸውን ዐበይት ጉዳዮች በዳሰሰችበት ወቅት የቡድኖቹ የተዘበራረቀ የማልያ አጠቃቀም ጉዳይ ትኩረት እንደሚያሻው የሚያሳስብ ፅሁፍ ማስነበቧ ይታወሳል።


© ሶከር ኢትዮጵያ