የአሜሪካ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነችው ናኦሚ ግርማ የ2020 የአሜሪካ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ሆና ተመርጣለች።
በዚህ ዓመት ለዋናው ብሔራዊ ቡድን መመረጥ የቻለችው የተከላካይ መስመር ተጫዋቿ በ2019 የኮሌጅ ቡድኗ ስታንፎርድ የNCAA ቻምፒየንሺፕ ዋንጫ እንዲያነሳ የረዳች ሲሆን የ PAC-12 ምርጥ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ተብላ ተመርጣም ነበር። ከ20 ዓመት ብሔራዊ ቡድኑ በኮንካካፍ ውድድር ቡድኑን በአምልነት እየመራች በስድስት ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ አንድ ጎል ብቻ እንዲያስተናግድ ከመርዳቷ ባሻገር በኮሮና ምክንያት በተሰረዘው የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር እንዲያልፍ እና ሜክሲኮን 4-1 አሸንፎ የውድድሩ ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ይህን ተከትሎም ናኦሚ የአሜሪካ ምርጥ ወጣት ተጫዋች ተብላ ለመመረጥ በቅታለች። በ23 ዓመት የሽልማቱ ታሪክም ሁለተኛዋ የተከላካይ ተጫዋች ሆናለች።
በ1980ዎቹ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ካቀኑት ወላጆቿ ግርማ አወቀ እና ሰብለ ደምሴ በአሜሪካ 2000 ላይ የተወለደችው የ20 ዓመቷ ወጣት ናኦሚ ” አስገራሚ ዓመት ነበር። አሜሪካን መወከል ትልቅ ክብር ነው። ምንም እንኳ የዓለም ዋንጫው ቢሰረዝም ቡድናችን ባሳካው ስኬት ሁሉ ትልቅ ኩራት ተሰምቶኛል። ዓመቱ በታሰበው መልኩ መጓዝ ባይችልም ለአሰልጣኞቼ እና የህክምና ክፍሉ መጫወት እንድንቀጥል ስላደረጉ አመሰግናለሁ። ካለፉ የውድድሩ አሸናፊዎች ተርታ መሰለፍ እጅግ አስደሳች ነው። ለዚህ ቤተሰቦቼ፤ በተለይ ወንድሜ ሲያግዘኝ ነበር። የስታንፎርድ እና የብሔራዊ ቡድን ቤተሰቦቼንም እንደ ተጫዋች እና እንደ ግለሰብ ላበረከቱልኝ መልካም ነገሮች በሙሉ አመሰግናለሁ።” ስትል ከሽልማቱ በኋላ ለዩኤስ ሶከር አስተያየቷን ሰጥታለች።
የአሜሪካ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ላውራ ሀርቬይ ናኦሚን ” ምርጥ ግለሰብ እና መሪ” ሲሉ አሞካሽተው “በቡድን ጓደኞቿ የተከበረች እና ቡድኑን ከፊት የምታስቀምጥ አይነት ተጫዋች ናት። በሜዳ ላይ ብልጥ፣ ደፋር እና ለመሻሻል የምትተጋ ናት። ለተከላካይ ሽልማት መውሰድ ከባድ እንደሆነ አውቃለሁ። ግን ይሄ ሽልማት በሜዳ ላይ እኛ በዙርያዋ በሚገኙ ሰዎች ሰዎች ላይ ለፈጠረችው በጎ ተፅእኖ እውቅና ነው።” ሲሉም አክለዋል።
በዚህ ሽልማት ምርጫ ላይ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች፣ በ2020 ለብሔራዊ ቡድን የተጠሩ ተጫዋቾች፣ የእግርኳስ ማኅበሩ ቦርድ ዴሬክተሮች፣ የሴቶች ሊግ፣ የሜጀር ሊግ ሶከር እና የመሳሰሉ የሀገሪቱ የእግርኳስ አካላት የሚሳተፉት ሲሆን ይህ ሽልማት በ1998 ሲጀመር የመጀመርያው አሸናፊ የነበሩት የወቅቱ የአሜሪካ ሶከር (የሀገሪቱ እግርኳስ ማኅበር) ፕሬዝዳንት ሲንዲ ፓርሎው ናቸው።
ስለ ናኦሚ ግርማ የእግርኳስ ህይወት ከአራት ዓመታት በፊት ያዘጋጀነውን ፅሁፍ ተከታዩን ሊንክ በመጫን ይመልከቱ :- LINK | ኢትዮ-አሜሪካዊቷ በዓለም ዋንጫ… |
© ሶከር ኢትዮጵያ