“በኢትዮጵያ ቡና ማልያ የመጀመርያ ጎሌን ማስቆጠሬ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል” ዊልያም ሰለሞን

በቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና ጅማ አባ ጅፋርን በረታበት ጨዋታ በሁሉም ጎሎች ላይ ተሳትፎ ከነበረው እና የሊጉ ክስተት መሆን ከቻለው ዊልያም ሰለሞን ጋር ቆይታ አድርገናል። 

ከወራት በፊት ስለዚህ ድንቅ ተጫዋች በሶከር ኢትዮጵያ የተስፈኛ አምዳችን ነግረናችሁ እንደነበር ይታወሳል። ጊዜው ደርሶ በአሰልጣኝ ካሣዬ እና ረዳቶቹ ክትትል ይህ ወጣት በኢትዮጵያ ቡና ማልያ መድመቁን ቀጥሏል። ሀረር ከተማ የተወለደው ዊልያም በፕሮጀክት ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በመግባት በስልጠና አልፏል። በአንድ ወቅት እግርኳስን እስከማቆም ያደረሰ ተስፋ አስቆራጭ ጊዜ አሳልፎ የነበረው ዊልያም ዳግም ወደ ኳስ ከተመለሰ በኋላ በመከላከያ ተስፋ እና ዋናው ቡድን ሲጫወት ቆይቶ ዘንድሮ ቡናማዎቹን ተቀላቅሏል። በኢትዮጵያ ቡና መለያ ተቀይሮ በመግባት ጀምሮ በየጨዋታው ባሳየው መሻሻል ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የገባው ዊልያም በዛሬው ዕለት በፕሪምየር ሊጉ የመጀመርያ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል። የሊጉ ክስተት በመሆን ላይ የሚገኘው ወጣቱ ሁለገብ ተጫዋች ዊሊያም ከጨዋታው በኃላ አግኝተነው ተከታዩን ሀሳብ ሰጥቶናል።

” ወደ ኢትዮጵያ ቡና ስመጣ በፍጥነት የመሰለፍ እድል አገኛለው ብዬ አላሰብኩም። ተቀይሮ በመግባት በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ እሰለፋለው ብዬ ነበር የማስበው። ምስጋና ለአሰልጣኞቹ ይሁንና በኔ አምነውብኝ አሁን መጫወት ችያለው። ይህ ለኔ በጣም ትልቅ ዕድል ነው። በኢትዮጵያ ቡና ማልያ የመጀመርያ ጎሌን ማስቆጠሬ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል። ይህን ማንም ተጫዋች የሚመኘው ነገር ነው። ይህም በመሳካቱ ደስ ብሎኛል። በራስ መተማመኔ እየጨመረ የተሻለ ነገር አውጥቼ ለመጫወት የዛሬው ጎል ይረዳኛል። አብረውኝ እንዲጫወቱ ከምፈልጋቸው ተጫዋቾች ጋር መጫወቴ ነገሮች ቀለውልኛል። ከዚህ በኃላም ከኔ ብዙ ነገር ይጠበቃል።”


ስለ ዊልያም ሰለሞን ከዚህ ቀደም ያቀረብነውን ፅሁፍ ከታች ያለውን ርዕስ በመጫን ያገኙታል። 

ተስፈኛው ወጣት ዊልያም ሰለሞን…


© ሶከር ኢትዮጵያ