ትውልደ ኢትዮጵያዊው የቀድሞ የኤሲሚላን ተጫዋች በአሳዛኝ ሁኔታ ሕይወቱ አለፈ

በኢትዮጵያ የተወለደውና በታዳጊነቱ ኤሲ ሚላን አካዳሚን ተቀላቅሎ የነበረው ሰዒድ ቪሲን በ20 ዓመቱ ራሱን አጥፍቶ መገኘቱ ተዘግቧል።

መስከረም ወር 2000 ላይ በኢትዮጵያ የተወለደው ሰዒድ በልጅነቱ በጣልያናዊያን ቤተሰቦች በማደጎነት ወደ ሀገሪቱ ካመራ በኋላ በ2014 የኤሲ ሚላን አካዳሚን ተቀላቅሎ የነበረ ሲሆን በመቀጠል ወደ ቤንቬንቶ አምርቶ ነበር። ሆኖም ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ በሚደርሱበት ጥቃቶች ምክንያት በ2016 እግርኳስን መጫወት አቁሞ አትሌቲኮ ቪታሊካ በተባለ አማተር ቡድን (5A Side) እየተጫወተ በአስተናጋጅነት ሕይወቱን መግፋት ጀምሮ ነበር። ሆኖም ከደንበኞች የሚደርስበት የዘረኝነት ጥቃት ሥራውን እንዲተው አስገድዶታል።

ትናንት ምሽት በመኖርያ ቤቱ ሞቶ የተገኘው ሰዒድ ራሱን ማጥፋቱ የተዘገበ ሲሆን ኮሪዬሬ ዴላ ሴራ ደግሞ ወጣቱ ከመሞቱ በፊት ፅፎ ያስቀመጠውን መልዕክት ማግኘቱን ይፋ አድርጓል። የሰዒድ መልዕክት ይህንን ይመስላል:-

“በየሄድኩበት ሁሉ ሰዎች በጥርጣሬ፣ በሥጋት እና በመጠየፍ እንደሚመለከቱኝ ይሰማኛል። እኔ እዚህ ተሰድጄ አልመጣሁም፤ በማደጎ ተወስጄ እንጂ። ልጅ እያለሁ በዙርያዬ ያሉ ሁሉ ይወዱን እንደነበር አስታውሳለሁ። በየሄድኩበት ቦታ ሁሉ ሰዎች በደስታ እና የአክብሮት ስሜት ያወሩኝ ነበር። አሁን ግን ያ ሁሉ ተቀይሯል።

“ከኳስ ራሴን ካገለልኩ በኋላ ሥራ አግኝቼ ነበር። ሆኖም ሰዎች በተለይም በዕድሜ የገፉት በእኔ ለመስተናገድ ፍቃደኛ አልነበሩም። በርካታ ወጣት (ነጭ) ጣልያናዊያን በእኔ ምክንያት (እኔ ቦታውን በመያዜ) ሥራ ማግኘት ላለመቻላቸውም ተጠያቂ ያርጉኛል።

” በውስጤ የሆነ ነገር ተቀይሯል። ጥቁር በመሆኔ የማፈር እና ተሰዶ የመጣ ሰው መባልን የመፍራት ነገር። እኔን የማያውቁ ሰዎችን እንደነሱ (ነጭ እና ጣልያናዊ) መሆኔን ማሳመን እንዳለብኝ ይሰማኛል። እነሱን መምሰሌን ለማሳየት በጥቁሮች ላይ ያነጣጠሩ መጥፎ ቀልዶችን እቀልድ ነበር። ግን ይሄ ፍራቻ ነው። በሰዎች ዓይን ውስጥ የምመለከተውን ለስደተኞች ያለ ጥላቻን መፍራት።

” ሰዎች እንዲያዝኑልኝ አልፈልግም። ለራሴ ማስታወስ የምፈልገው ያሳለፍኩት አስቸጋሪ ጊዜ መሞትን በዚህ ስቃይ ውስጥ ከመቆየት የተሻለ ሆኖ ካገኙት ሰዎች ጋር ሲነፃፀር ከውቅያኖስ ጠብታ ውሀ የመጭለፍ ያህል ትንሽ መሆኑን ነው። ”

በወጣቱ ሞት ብዙሀኑ የጣልያን የእግርኳስ ቤተሰቦች ሀዘናቸውን የገለፁ ሲሆን የቀድሞ ክለቡ ኤሲ ሚላን፣ የከተማ ተቀናቃኑ ኢንተር ሚላን እንዲሁም የህይወቱ የመጨረሻ ጊዜያትን ለመዝናናት ይጫወትበት የነበረው አትሌቲኮ ቪታሊካ ሀዘናቸውን በይፋ ከገለፁት መካከል ናቸው።

የቀድሞ የኤሲሚላን ወጣት ቡድን አጋሩ እና በአዳሪ ትምህርት ቤት ጓደኛው የነበረው ጂያንሉዊጂ ዶናሩማም በቪሲን ሞት ሀዘኑን የገለፀ ሌላው ተጫዋች ነው። “ጓደኛዬ ነበር። ፈገግታውን በፍፁም ልረሳው አልችልም” ሲል የኤሲሚላን እና ጣልያን ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ተናግሯል።

በዘረኝነት ጥቃት ስሟ በክፉ በምትነሳው ጣልያን ትልልቅ ስም ካላቸው ማርዮ ባሎቴሊ እና ኬቭን ፕሪስ ቦአቴንግ እስከ ዝቅተኛ ደረጃ የሚኖሩ ስደተኛ እና በማደጎ የተወሰዱ ግለሰቦች ድረስ የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ቆይተዋል። በቅርቡ እንኳ በጣልያን ለአስር ዓመታት የኖረችው አጊቱ ጉደታ የተባለች ኢትዮጵያዊት በደረሰባት ጥቃት መገደሏ የሚታወስ ነው።


ሶከር ኢትዮጵያ በተጫዋቹ ሞት ጥልቅ ሀዘኗን እየገለፀች ከዚህ ቀደም ተጫዋቹ ወደ ኤሲ ሚላን አካዳሚ ባመራበት ወቅት በድረገፃችን ያስነበብነውን ሊንኩን በመጫን  ያገኛሉ:- LINK