ምሽት በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ መከላከያ በመለያ ምቶች ጅማ አባ ጅፋርን አሸንፏል።
ቀዝቀዝ ባለው አየር የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ጅማ አባ ጅፋርን እና ከኢትዮጵያ ዋንጫ ባለድሉን መከላከያ ያገናኘው ጨዋታ በጥቂት ተመልካች ታጅቦ በመደበኛው ደቂቃ በተቆጠሩት የኤልያስ ማሞ እና ሳሙኤል ታዬ ግቦች 1-1 ሲጠናቀቅ ለ64 ደቂቃዎች በ10 ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደደው መከላከያ በመለያ ምቶች ተጋጣሚውን መርታት ችሏል። በውጤቱም መከላከያ ኢትዮጵያ ቡና 2000 ላይ ካስመዘገበው ታሪክ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሎማለፉን አሸንፎ የአሸናፊዎች አሸናፊ መሆን የቻለ የመጀመሪያው ክለብ ሆኗል።
ከጅምሩ መሀል ሜዳ ላይ ብርቱ ፉክክር ሲደረግበት የታየው ይህ ጨዋታ በቁጥር የበዙ ሙከራዎች ሳይታዩበት ነበር 23ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ያስተናገደው። ጎሏ ለጅማ አባ ጅፋር የተቆጠረች ስትሆን ኤርሚያስ ኃይሉ እና ዐወት ገብረሚካኤል በፈጠሩት ቅብብል በቀኝ መስመር ገብተው ኤርሚያስ ወደ ሳጥን የላካትን ኳስ ኤልያስ ማሞ ነበር በድንቅ አጨራረስ አጋጥሚውን ወደ ግብነት የቀየረው። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የመከላከያው አማካይ ቴዎድሮስ ታፈሰ አስቻለው ግርማን በክርን በመማታቱ በቀጥታ ቀይ ካርድ በእንባ ታጅቦ ከሜዳ ወጥቷል። በቀጣይ ደቂቃዎች በነበረው እንቅስቃሴ ግን ቦታውን ለመሸፈን ፍፁም ገብረማርያምን መስዕዋት አድርገው በሀይሉ ግርማን ያስገቡት መከላከያዎች ተሽለው ታይተዋል። በአንፃሩ የቁጥር ብልጫ ያገኙት ጅማዎች ዲዲዬ ለብሪን ወደ ሜዳ አስገብተው የአጥቂዎቻቸውን ቁጥር ቢጨምሩም የነበራቸው የበላይነት ሲቀንስ ታይቷል።
ጅማዎች ከእረፍት በኋላ ተነቃቅተው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመያዝ እና ተጭነው በመጫወት በመከላከያ የሜዳ አጋማሽ ላይ ለመቆየት ችለዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ከሳጥን ውጪ የሞከራት ኳስም በአዲሱ ተጨርፋ ከመረብ ተገናኘት ተብሎ ሲጠበቅ ጎል ከመሆን የታደጋት የግቡ አግዳሚ ነበር። ሆኖም ለምንይሉ ወንድሙ ቀጥተኛ ኳሶችን ሲልኩ የቆዩት መከላከያዎች 59ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። ከሳጥን ውጪ የተሻገረችው ኳስ ተጨርፋ የጅማ ጎል አፋፍ ላይ ስትደርስ ከአዳማ ሲሴኮ ቀድሞ ያገኛት ሳሙኤል ታዬ ወደ ግብነት ቀይሯታል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ይሁን እንዳሻው እና ዲዲዬ ለብሪ በመከላከያ በኩል ደግሞ ተመስገን ገብረኪዳን ያደረጓቸውን ሙከራዎች ያስመለከተን ጨዋታ ግን ተጨማሪ ጎል ሳያቆጠርበት በዛው ውጤት 1-1 የተጠናቀቀ ነበር። በመሆኑም ባሳለፍነው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ዋንጫ የደረጃ ጨዋታ በመለያ ምት የተለያዩት ሁለቱ ቡድኖች ዛሬም በተመሳሳይ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት አምርተዋል።
መከላከያዎች ከመቷቸው አምስት መለያ ምቶች ውስጥ ሽመልስ ተገኝ አንድ ከመሳቱ በቀር ሌሎቹን ከመረብ ጋር ተገናኝተዋል። በጅማዎች በኩል ግን ከድር ኸይረዲን እና ንጋቱ ገብረስላሴ ሁለት መለያ ምቶችን አምክነዋል። በመሆኑም መከላከያዎች በመለያ ምቶቹ ጅማ አባ ጅፋርን 4-2 በመርታት የአሸናፊዎች አሸናፊ የዋንጫ ሽልማትን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዘዳንት ኮ/ል ዐወል አብዱራሂም እጅ ወስደዋል።
የመከላከያው አጥቂ ተመስገን ገብረኪዳን አምና ፕሪምየር ሊጉን ከጅማ አባ አባጅፋር ጋር ፣ የኢትዮጵያ ዋንጫ እና የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫን ደግሞ ከመከላከያ ጋር በማንሳት ሶስቱን ክብሮች ከሁለት ክለቦች ጋር ሆኖ ያሳካ ታሪካዊ ተጫዋች ሆኗል።