በዝነኛው እንግሊዛዊ የእግርኳስ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና በእግርኳስ ታክቲክ ዝግመታዊ የሒደት ለውጦች ላይ የሚያተኩረው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የተሰኘውን መጽሃፍ በትርጉም እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። በዛሬው መሰናዶም የምዕራፍ አንድ አራተኛ ክፍልን እነሆ ብለናል፡፡ መልካም ንባብ!
|| የመፅሀፉን ክፍል ሁለት ለማንበብ ይህን ይጫኑ | ምዕራፍ አንድ- ክፍል ሶስት |
በ1880ዎቹ በእንግሊዝና ስኮትላንድ የሚገኙ ወግ አጥባቂ እግርኳሰኞችን ስጋት ላይ የጣለና ቆይቶም ተስፋ ያስቆረጠ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ቅብብሎችን መሰረት አድርጎ በሚካሄደው ጨዋታ ከሁለቱ የመሃል አጥቂዎች የአንደኛውን የሜዳ ኃላፊነት በድጋሚ ሲተገብር የሚስተዋለው ሌላኛው የፊት መስመር ተሰላፊ በሜዳው ቁመት በጥልቀት ወደ ኋላ በማፈግፈግ ቀስ በቀስ በ2-3-5 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ ግትር አደራደር የመሃል አማካይነት ሚናን መወጣት ጀመረ፡፡ በዚህም ሒደት ፒራሚድ መሳዩ ቅርጽ እውን ሆነ፡፡
ሃንጋሪያዊው አሰልጣኝ አርፔድ ኬሳናዲ በወቅቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ በነበረው እንዲሁም ይዘቱ ሰፋ ባለው <ሶከር> የተሰኘ የስልጠና መመሪያው 2-3-5 ፎርሜሽን በቅድሚያ ጥቅም ላይ የዋለው በ1883 በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ ገለጸ፡፡ ሆኖም በአሰልጣኙ የተጠቀሰው መረጃ በብዙዎች ተቀባይነት እንዳገኘ ቢታመንም የአደራደር ስርዓቱ ከስድስት ዓመታት ቀደም ብሎ ተግባራዊ ስለመደረጉ የሚያወሱ ሌሎች አስረጅ ማረጋገጫዎችም ተገኙ፡፡ ከተጫዋቾች ትጥቅ ግብዓት አንዱ የሆነውን የቅልጥም ሽፋን ወይም የእግር ጉዳት መከላከያ መጋጫን ቀድመው የፈጠሩት ኖቲንግሃም ፎረስቶች በ1870ዎቹ መባቻ አምበላቸው ሳም ዊዶውሰንን ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ አድርገው በጨዋታዎች ከሞከሩት በኋላ ባዩበት ጥሩ ብቃት ተበረታታው የዚሁ ሲስተም /2-3-5 ፎርሜሽን/ አቀንቃኞች ሆነው ብቅ አሉ፡፡
በ1878 በተካሄደው የዌልስ ዋንጫ ፍጻሜ ሬክስሃሞች ድሩይድሶችን ሲገጥሙ ወደ ኋላ ያፈገፈገ አማካይ ለመጠቀም ቻሉ፡፡ በከተማዋ የመሬት ጉዳዮች ኃላፊ ሆኖ የሚሰራው ቻርለስ ሙርለስ ቡድኑን በመስመር ተከላካይነት የሚያገለግል አምበል ነበር፡፡ ሙርለስ በዚሁ ጨዋታ ላይ ቀደም ሲል በፊት መስመር ተጫዋችነት የሚታወቀውን ክሮስ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ቢያደርግ በቦታው የሚቀረው ሌላኛው የመሃል አጥቂ ጆን ፕራይስ ፍጥነት በማጥቃት ወረዳው ሊከሰት የሚችለውን ጉድለት ለመሸፈን በቂ እንደሆነ አሰበ፡፡ ይህ ውጥረት የነገሰበት ጨዋታ ከመገባደዱ ሁለት ደቂቃዎች በፊት ጄምስ ዴቪስ ያስቆጠራት ብቸኛዋ የማሸነፊያ ጎል ለሬክስሃሞች ድል አስገኝታ የሙርለስን ውሳኔ ተገቢነት አረጋገጠች፡፡
የ2-3-5 ፎርሜሽን ተፈላጊነት እያደገ መሄድ አዲሱ የመሃል አማካይ /ሴንተር-ሀፍ/ ቀድሞ ከሚታወቅበት የአጨናጋፊነት ሚናው በተለየ የአንድ ቡድን ምሰሶ እንዲሆን አስቻለው፡፡ በጊዜ ሒደትም ብዙ ኃላፊነት የሚወጣ፣ ሁለገብ፣ ተከላካይ፣ አጥቂ፣ አነሳሽ፣ መሪ፣ ግብ አስቆጣሪና የተጋጣሚን የጨዋታ እቅድ አምካኝ ሆነ፡፡ ታላቁ ኦስትሪያዊ የእግርኳስ ጸሀፊ ዊሊ ሜይዝልም ” የሜዳው እጅግ ጠቃሚ ሰው!” ሲል ሰየመው፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በጥቅምት 1878 በመድረክ መብራቶች በተንቆጠቆጠ ድባብ በቀዮቹ እና በሰማያዊዎቹ መካከል የኤግዚብሽን ግጥሚያ ተደረገ፡፡ ጨዋታውን አስመልክቶ ሼፊልድ ኢንዲፔንደንት በሰራው ዘገባም ሁለቱ ቡድኖች ባልተለመደ መልኩ በተመሳሳይ አራት-የኋላ መስመር ተከላካዮች፣ አንድ-አማካይ (ሴንተር-ሀፍ) እንዲሁም አምስት-አጥቂዎችን እንዳሰለፉ የሚያሳይ ዝርዝር አወጣ፡፡ ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ለቀጠሉት ሶስት አስርት አመታት ሌሎች ቡድኖች ከሁለት ተከላካዮች በላይ መጠቀማቸውን የሚያሳይ ምንም አይነት መረጃ አልተገኘም፡፡ በጋዜጣው በተመለከተው 2-3-5 ፎርሜሽን ውስጥ በተጋጣሚ ቡድን ሁለቱ የመሃል አጥቂዎች ግራና ቀኝ በኩል የሚጫወቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎችን እንቅስቃሴ መመከት ቀዳሚ ተግባራቸው ያደረጉ እና ወደ ራሳቸው ክልል ያፈገፈጉ የክንፍ አማካዮችን (ዊንግ-ሃቭስ) እንደ ኋላ መስመር ተከላካዮች(ባክስ) መታሰባቸው የሚና ቅይይርን የፈጠረ ሒደት መሰለ፡፡
በህዳር ወር 1882 ስኮቲሽ አትሌቲክ የተሰኘው መጽሔት በመከላከል አጨዋወት ዙሪያ የሚነሱ ሐሳቦችን የሚያወግዝ እና ቁጣን የሚቀሰቅስ ጽሁፍ ይዞ ወጣ፡፡ ጸሃፊውም “የአንዳንድ ሃገራት ክለቦች ከግብ ክልላቸው 18 ሜትር ርቀት ውስጥ የሚጫወቱ ሁለት ተከላካዮችን የማቆማቸው ፋይዳ እንዲያው ዝም ብሎ ግብ ጠባቂውን ለማውጋት ብቻ ነው፡፡” በማለት አፌዘ፡፡ በተመሳሳዩ ለጋር ቦስዌል ቲስትል የተባለ የአይርሻየር ክለብም በጨዋታዎች ወቅት ዘጠኝ ተጫዋቾችን ብቻ በማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ለማሳተፍ በመወሰኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ነገር ግን በቀጣዩ አመት አድሃሪያኖቹ (ለውጡን የሚቃወሙትና እድገቱን የማይሹት አካላት) የሚታገሉት ድል በማያገኙበት ጦርነት ላይ እንደነበር ተረጋገጠ፡፡ በ1883 የስኮትላንድ ዋንጫ ፍጻሜ ደምባርተን የተባለው ክለብ 2-3-5ን ተጠቅሞ የሌቨን ከተማ የሆነውን ቫሌ ቡድን በመርታት ዋንጫውን ወሰደ::
የፕሪስተን ኖርዝ ኢንድ የ1880ዎቹ ስኬታማ ጉዞ 2-3-5 ከሁሉ የላቀውና ተመራጩ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር መሆኑን አሳየ፡፡ የፎርሜሽኑ ተቀባይነትም ከፍ እያለ እንዲሄድ በር ከፈተ፡፡ ከምስረታው ጀምሮ ለጥቂት አመታት የክሪኬትና ራግቢ ክለብ የነበረው ይህ ቡድን በማህበሩ የጨዋታ መመሪያ መሰረት በ1878 ኢግሊ ከተሰኘ ቡድን ጋር ‘አንድ ጊዜ ብቻ የሚደረገውን’ ግጥሚያ አካሄደ፡፡ በዚህኛው ጨዋታ የተጋጣሚያቸው ተጫዋቾች በሜዳ ላይ የነበራቸውን የቦታ አያያዝና የቡድን ቅርጽ የሚያሳየው መረጃ ባይመዘገብም በቀጣዩ አመት ህዳር ወር ላይ በመደበኛነት ሁለት ተከላካዮች፣ ሁለት የመሃል አማካዮች፣ ሁለት የቀኝ መስመር አማካዮች፣ ሁለት የግራ መስመር አማካዮች እንዲሁም ሁለት የመሀል አጥቂዎችን የሚጠቀምና በ2-2-6 ፎርሜሽን የተዋቀረ ሃሊዌል የተባለ ቡድን ጋር ተገናኙ፡፡ ፕሪስተኖች በ1880-81 የውድድር ዘመን የላንክሻየር እግርኳስ ማህበርን ተቀላቀሉ፡፡ በጅማሮ ወቅት ቢቸገሩም የስኮትላንድ ተጫዋቾች ማህበር መቋቋም ክለቡን ከስሙ ውጪ ባሉ ነገሮች በሙሉ ቀየረው፡፡ በ1883 ለመጀመሪያ ጊዜ የቡድኑን ቋሚ አሰላለፍ የሚያሳየው መረጃ ፕሪስተን የሚጠቀመው 2-3-5 ፎርሜሽን መሆኑን አመለከተ፡፡ ዳቪድ ሃንት የክለቡን ታሪክ በሚዘከርበት መጽሐፍ ላይ ” ሀሳቡ በእርግጥም የየትኛው አካል እንደሆነ ማረጋገጫ ባይገኝለትም በግላስኮው ከተማ የህክምናና መምህርነት ጥምር ባለሙያ የነበረው ጄምስ ግሌድሂል -በምርጥ ተጫዋቾች የተደራጀ ቡድን ሊሰራ ስለሚችለው ነገር- በጥቁር ሰሌዳ ላይ በማሳየት ተከታታይ ትምህርቶችን ሰጥቷል፡፡” በማለት ጠቅሷል፡፡ ይህን ሲስተም በመጠቀምም ክለቡ የመጀመሪያዎቹን ሁለት የሊግ ዋንጫዎች ማንሳት ቻለ፡፡ በቀዳሚው ስኬታማ አመት እና የ1887-88 የውድድር ዘመን ድሉን ሲያሳካ አንድም ጨዋታ አልተሸነፈም፡፡
በ1884 እንግሊዝ ከስኮትላንድ ጋር ባደረገችው ጨዋታ 2-3-5 ፎርሜሽንን ተገበረች፡፡ በዚያው አመት ጥቅምት ወር ላይ ኖትስ ካውንቲ ክለብ ለወዳጅነት ጨዋታዎች ወደ ሰሜናዊው የአገሪቱ ክፍል ባመራበት ወቅት ይህ ሲስተም በሁሉም ቡድኖች ዘንድ የተለመደ ሆኖ ጠበቀው፡፡ እንዲያውም ኢምፓየር የተሰኘው መጽሄት ኖትስ ካውንቲ ከሬንፍሪውሻየር ጋር በነበረበት ጨዋታ ላይ 2-3-5ን ስለመጠቀሙ ያለ ምንም አሻሚ አስተያየት ሊዘግብ በቃ፡፡ የስኮትላንድ ብሄራዊ ቡድን አባላት ደግሞ የፒራሚድ ቅርጽ መሳዩን ፎርሜሽንና ቀድሞ የእንግሊዛውያን የነበረውን ታክቲክ በመኮረጃቸው እየተማረሩ በ1887 ለመጀመሪያ ጊዜ 2-3-5ን የአሰላለፍ ምርጫቸው አደረጉ፡፡ ጄምስ ኬሊ በ1889 በስኮቲሽ ሪፈሪ ላይ የሴልቲን አጭር ታሪክ ለመዘከር ባሳተመው ጽሁፍ በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን የመጨረሻዎቹ አስርት አመታት ክርክሩ ያበቃለት ጉዳይ እየሆነ ስለመሄዱ ግልጽ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ እትሙ ” ‘ስኮትላንድ የሴንተር-ሃፍ ባክ/ተከላካይ አማካይ የሜዳ ላይ ቦታና ሚናን ተቀብላ በጨዋታዎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ ስትጀምር በእግርኳሱ የነበራትን ጉልበት አጥታለች፡፡’ ብለው የሚያምኑ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡” ሲል ያስነብባል፡፡ “በእርግጥ ሁላችንም የዚህ ሀሳብ ተጋሪ አይደለንም፡፡ በክለቦቻችን የሚገኙ ይህን ክፍተት የሚደፍኑ ተጫዋቾች በጄምስ ኬሊ የችሎታ መመዘኛ መሰረት የሚገኙ ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ እንኳ በጉዳዩ ላይ የበዛ ልዩነት አይፈጥርም፡፡ እንግሊዝን መከተልም ያን ያህል ለቁጭት የሚዳርግ ውሳኔ አይሆንም ነበር፡፡”
በ1925 በእንግሊዝ የጨዋታ-ውጭ ህግ ተቀይሮ የ<WM>ፎርሜሽን ወደ እድገት እስከሚያመራበት ጊዜ ድረስ ፒራሚድ በአለም እግርኳስ ተዘውታሪው የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ሆኖ ቆየ፡፡ ልክ ቀደም ባለው ዘመን በአንደኛው ወቅት ላይ ድሪብሊንግ እና በሙሉ ተጫዋቾች የማጥቃት አጨዋወት ስልት ትክክለኛ እንዲሁም ብቸኛ የእግርኳስ ጨዋታ አማራጭ እንደነበረው ሁሉ 2-3-5 ፎርሜሽንም የንጽጽር ስረ-ነገር ወይም መስፈርት ሆነ፡፡
ይቀጥላል…
ስለ ደራሲው
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡
-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)
-Sunderland: A Club Transformed (2007)
-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)
-The Anatomy of England (2010)
-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)
-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)
-The Anatomy of Liverpool (2013)
-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)
-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)
ቀደምት ምዕራፎች | |
መቅድም | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት | LINK |