ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ ሁለት – ክፍል አራት)

በዝነኛው እንግሊዛዊ የእግርኳስ ፀኃፊ ጆናታን ዊልሰን የተደረሰውና በእግርኳስ ታክቲክ ዝግመታዊ የሒደት ለውጦች ላይ የሚያተኩረው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የተሰኘውን መጽሃፍ በትርጉም እያቀረብንላችሁ እንገኛለን። በዚህ ሳምንትም የምዕራፍ ሁለትን አራተኛ ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

የስቶኮልሙ ኦሊምፒክ በ1924 ከተካሄደ አራት ዓመታት በኋላ አርጀንቲና በሆላንዱ ስፖርታዊ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ  አምስተርዳም በረረች፡፡ በፍጻሜውም ተቀናቃኟ ዩሯጓይን አገኘችና በመልሱ ጨዋታ 2-1 ተሸነፈች፡፡ ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላ ደግሞ ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው የአለም ዋንጫ ፍጻሜ ላይ ተፋጠጡ፡፡ ዩሯጓይ በድጋሚ 4-2 ድል አድርጋ አርጀንቲና ላይ የነበራትን የበላይነት መልሳ አሳየች፡፡ ከዚያን ጊዜ ዘገባዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ዩሯጓይ ከያዘችው ማራኪ የጨዋታ አቀራረብ በላይ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀቷን በወጥነት ማስቀጠል መቻሏ የበለጠ ተጠቃሚ እንድትሆን አስችሏታል፡፡ በዚያ ላይ አሰልጣኙ ቪየራ የሚያሳዩት ተፈጥሯዊ እና ገደብየለሽ ቁጡነት በቡድኑ ውስጥ ለሚኖር ስርዓት የማስጠበቅ ሒደት የራሱን ድርሻ አበረከተ፡፡ በአንጻሩ ግለኝነት የሚንጸባረቅበት የአርጀንቲና ቡድን ደግሞ አልፎአልፎ ግራ መጋባት ውስጥ ይዳክር ነበር፡፡  አንጋፋው ጋዜጠኛ ጂያኒ ብሬራ በ<ስቶሪያ ክሪቲካ ዴል ካልቺዮ ኢታሊያኖ> ላይ “አርጀንቲና እግርኳስን ጠለቅ ባለ ስሜትና ግርማ ሞገስ ትጫወታለች፡፡ ይሁን እንጂ ቴክኒካዊ የበላይነት ብቻውን ታክቲክን ችላ በማለት የሚከፈል ዋጋን አያካክሰውም፡፡ ከእነዚህ ሁለት <ራዮፕላተንሴ> (ሪዮ ዴ ላፕላታ ተብሎ በሚታወቀው ሸለቆ አካባቢ የስፓኛ ዘዬ ያለውን ቋንቋ ከሚናገሩ ሃገራት አርጀንቲናና ዩሯጓይ ዋነኞቹ ናቸው፡፡) ብሄራዊ ቡድኖች መካከል ጉንዳኖቹ ዩሯጓውያን ሲሆኑ ፌንጣዎቹ ደግሞ አርጀንቲናውያኑ ነበሩ፡፡” ሲል በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረውን ልዩነት አመላከተ፡፡  በዚህ ገለጻ መሰረት የ1930ው የአለም ዋንጫ ” አጠቃላዩ የእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት እና የፍሰት ሒደቱን በጠበቀ የማጥቃት እንቅስቃሴ መካከል ሊኖር የሚችለውን እጅግ ስኬታማ ሚዛን የማግኘት ዘላቂ ትግል ያሳያል፡፡” የሚለውን መሰረታዊ የእግርኳስ ታክቲክ መርህ ማረጋገጫ ሆነ፡፡ ይህ ጽንሰ-ሐሳብም <ላ-ጋራ-ቻሩዋ> በመባል የሚታወቀውን እግርኳሳዊ አተያይ  አሳደገ፡፡

ቻሩዋ’ በዩሯጓይ የሚኖሩና የዘር ግንዳቸው ከወደ ህንድ የሚመዘዝ የሃገሬው ተወላጆችን የሚወክል ስም ሲሆን -ጋራ- ደግሞ <በጥፍር መያዝ> የተሰኘ ቀጥተኛ ትርጉም ቢሰጥም <ወኔ> አልያም <የተጋድሎ መንፈስ> የሚል ይዘት ያለው ፈሊጣዊ ፍቺ የተሻለ ይስማማዋል፡፡ ከሶስት ሚሊዮን ያልበለጠ ህዝብ ያላት ሃገር ሁለት የአለም ዋንጫዎችን ለማሸነፍ ያሳየችው ቁርጠኝነት ከስነ ልቦናዊ እሴት ጋር የተያያዘ ለመሆኑ ይህ የጀብደኝነት ስሜት ጥሩ ማረጋጋገጫን ይሰጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቀጣይ ጊዜያት የመጡት የዩሯጓይ ብሄራዊ ቡድኖች በመጠኑም ቢሆን ታጋይ የመሆን እውነተኛ ተፈካካሪነታቸው ከፍ እንዲል ያደረገው ይኸው ስር የሰደደ አስተሳሳብ ነው።

ንድፈ-ሐሳቡ የቱንም ያህል ቢጋነን እንኳ <ቻሩዋ> እግርኳሱ ውስጥ ቦታ ካገኘ በኋላ ከብሪታኒያ ውጪ ላሉ ሰዎች በአለም ምርጥ የአጨዋወት ስልትን የያዘ እግርኳስ የሚከናወነው ማዕበለ-ገብ ወይም የባህርና ወንዝ ውሃ በሚገናኙባት የሪቨር ፕሌት አካባቢ ስለመሆኑ ግልጽ እየሆነ ሄደ፡፡ አጨዋወቱ በብሪታኒያ በስፋት ከተለመደውና ተገማችነቱ እያየለ ከመጣው የ2-3-5 አቀራረብ ስልትም የተሻለ ሆኖ ተገኘ፡፡ “የእንግሊዞች ተጽዕኖ እየተዳከመ ሄዶ በጥቂት እርጋታና እረፍት-የለሽ በሆነ መንፈስ የሚደረግ እንቅስቃሴ ለሚታይበት የላቲኖች አጨዋወት ቦታ መልቀቅ ጀመረ፡፡” ሲል በ1928 በአርጀንቲና <ኤል ግራፌ> የተሰኘ ጋዜጣ ላይ የወጣ ጽሁፍ የመከራከሪያ ነጥቡን አንስቷል፡፡ “ወዲያውኑም ላቲናውያኑ የጨዋታውን ሳይንስ ወደ ማሻሻሉ ገቡና በድጋሚ የራሳቸው የሚሉትን መለያ ሰጡት፡፡ ተመሳሳይ ይዘት ብቻ ስለማይታይበት፣ ግትርነት ያጠላበት የአጨዋወት ስልትን የያዘ ባለመሆኑና ችክ ያለ የአቀራረብ ዘዴን ስለማይከተል ከብሪታንያዎቹ የተለየ መልክ አገኘ፡፡ በተጨማሪም በጨዋታ ወቅት ከሚታየው ግለኝነት በላቀ ለቡድን መንፈስ ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱ ዘይቤው ተቀባይነት እንዲኖረው ረድቶታል፡፡ የሪቨርፕሌት እግር ኳስ ከተጫዋችቹ በርካታ ጊዜ የሚተገበሩ ድሪብሊንጎችና ራስን የማሻሻል ከፍተኛ ጥረት እጅጉን አትርፏል፡፡ የበለጠ ምርጥና ማራኪ ቡድንም ሆኗል፡፡” ብሏል ጋዜጣው፡፡

አንዳንድ ተጫዋቾች የተለያዩ ክህሎቶችን እንዳሳዩና የተወሰኑ አብዶዎችን እንደፈጠሩ እየታሰቡ እጅጉን የጀገኑበትና ትልቅ ውዳሴ ያገኙበት ሐሳበ-ሰፊ እይታቸው ጥሩ ክብር እያገኘላቸው፣ ተቀባይነታቸውም እያደገ ሄደ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሁዋን ኢቫሪስቶ የ<ማሪያኔላ> ወይም ኳሷ አየር ላይ እንዳለች በተረከዝ ወደ ኋላ የመምታት ጥበብ ፈጣሪ ነበር፡፡ ፓብሎ ባርቶሎሲ ደግሞ አየር ላይ ተወርውሮ ኳስን በግንባር የመግጨት ጀማሪ ሆነ፡፡ የግኝቱ ባለቤትነት አወዛጋቢ  ቢሆንም ፔድሮ ካሎሚኖም በተለምዶ የመቀስ ምት ተብሎ የሚጠራውን ማራኪና አክሮባቲክ ምት አመጣ፡፡ በእርግጥ አንዳንዶች <የመቀስ ምት> የተጀመረው በአስራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መባቻ በፔሩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በቢልባኦ የተወለደውና በስደት በቺሊ ይኖር የነበረው ራሞን ኡንዛጋ አስላ በ1914 ለመጀመሪያ ጊዜ ምቷን መተግበር በመቻሉ ቀዳሚው የዚህ ምት አስተዋዋቂ ስለመሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ (በደቡብ አሜሪካ የስፓኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሃገራት <ቺሌና> የሚል መጠሪያ የተሰጠው በዚህ ምክንያት ይመስላል፡፡ ይህ ካልሆነም በ1920 የስፔን ጉዞው ይህን ቴክኒክ በህዝቡ ዘንድ እንዲታወቅ ላደረገው ቺሊያዊው ዴቪድ አሬሊያኖ ” ‘ክሬዲቱ’ ሊሰጥ ይገባል!” የሚሉም አልጠፉም፡፡  ሌሎች የ1930ዎቹ ብራዚላዊ አጥቂ ሊዮኒዳስ ተከታዮች ደግሞ የአመታት ዘይቤው  የፔትሮሊንሆ ደ ብሪቶ እንደሆነ ይመሰክራሉ፡፡ የቀድሞው የአስቶን ቪላ ክለብ ሊቀመንበር ዳፍ ኤሊስ ግን “በጀርባ ተገልብጦ ኳስ የመምታትን ስልት ያመጣሁት እኔ ነኝ፡፡” የሚል የይገባኛል ቅሬታ ባልተለመደ መልኩ አቅርቧል፡፡ የሚገርመው ኤሊስ እግርኳስን በየትኛውም ደረጃ አለመጫወቱ  ብቻ ሳይሆን የመጀሪመያው የኡንዛጋ ቴክኒክ ከተመዘገበ ከአስር አመት በኋላ መወለዱ ነው፡፡

በዚህ አግባብ ውስጥ “ማን በትክክል ቴክኒኩን ፈጠረው?” ከሚለውም በላይ ክርክሩ በሪቨርፕሌት ባህር ዳርቻ ዙሪያ በ1920ዎቹ አካባቢ ከሃሰበ-ሰፊነትና ምናባዊ እይታ አንጻር ሊያመጣ የቻለው ለውጥ ወይም እሴት የበለጠ ጠቃሚ ነበር፡፡ ሆኖም ለብሪታንያ እግርኳስ ሀፍረትን የሚፈጥረው በጨዋታው ትውልድ ሃገር ግኝት ወይም ፈጠራ የማይወደድና የማይበረታታ ነገር መደረጉ ነው፡፡ ልክ ” ኤሊስ በብሪታኒያ ምድር የመቀስ ምትን በመተግበር ቀዳሚነቱን ይይዛል፡፡” እንደሚለው ልማዳዊ ንግግር ማለት ነው፡፡

የአርጀንቲና እግርኳስም የራሱ የሆነ የምስረታ አፈታሪክ አለው፡፡ በተለይም የሃንጋሪው ቡድን <ፌሬንክቫሮስ> በ1922 ያደረገው ጉብኝት ለሃገሬው ተጫዋቾች የ<ዳኑቢያን> እግርኳስ አጨዋወት ዘይቤን ፍንትው አድርጎ ካሳየ በኋላ በጨዋታው ላይ የነበራቸውን አስተሳሰብ ከስር መሰረቱ ለውጦታል፡፡ ምናልባትም የቋንቋ መወራረስ ሒደቱ ቢያንስ ለአስር አመት የመቆየት እድል ቢገጥመው ኖሮ ጉዞው ቀድመው የተጀመሩትን ስር ነቀል ለውጦች በቀላሉ የማስቀጠል ሁኔታ የሚፈጠር ይመስል ነበር፡፡ በተለይም በጅማሮ ወቅት የዳኑቢያኑና የራዮፕላተንሱ ጨዋታዎች ተመሳሳይ አቀራረብን ከመያዛቸው በተጨማሪ ለተክለ ሰውነት ጉዳዮች ቅድሚያ ይሰጥ ከነበረው የእንግሊዞች አጨዋወት ዘዴ ወዲያው በተጫዋቾች የግል ቴክኒካዊ ብቃት ላይ ወደሚያመዝነው ስልት ለውጥ አደረጉ።

ከቴክኒካዊ የግኝት ሙከራዎች ጎን ለጎን ቀስ በቀስም ቢሆን ታክቲካዊ ጥገናዎችን የማድረግ ዝንባሌዎች ይታዩ ጀመር፡፡ በመጀመሪያው የአለም ዋንጫ ፍጻሜ ለአርጀንቲና ቡድን በቀኝ መስመር አጥቂነት የተሰለፈው ፍራንሲስኮ ቫራሎ ” የደቡብ አሜሪካ ቡድኖች ኳሷን በደንብ ይንከባከቧታል፡፡ የበለጠ ታክቲካዊ አመለካከትና ቀረቤታም  ይታይባቸዋል፡፡ አምስት የፊት መስመር ተሰላፊዎች የሚገኙበት፣8-ቁጥሮችና 10-ቁጥሮች ወደ ኋላ የሚያፈገፍጉበት እንዲሁም የመስመር አማካዮች ቅብብሎችን የሚያቀርቡበት ዘመን ነበር፡፡” ብሎ ስለወቅቱ የተጫዋቾች ሚና ያስረዳል፡፡ በሜዳው ስፋት በአንድ የአግድመት መስመር ከሚደረደሩት አምስት ተጫዋቾች መካከል ከሁለቱም ጎኖች ብንነሳ ሁለተኛና አራተኛ ቦታ ላይ የሚገኙት የፊት መስመር ተሰላፊዎች ቁልፍ የፈጠራ ምንጭ ተደርገው መታሰብ ጀመሩ፡፡ በጨዋታ ወቅትም ጠመዝማዛ በሆነ ሁኔታ <ድሪብል> የማድረግ ሒደት ወይም <ጋምቤታ> ከፍተኛ አድናቆት ይቸረው ገባ፡፡ በአርጀንቲናም ሆነ በዩሯጓይ ግቦችን ለማስቆጠር የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን ባልተለመደ አስገራሚ ብቃት አብዶ እየሰራ አልፎ ከሄደ በኋላ ወደ ራሱ ቦታ ሲመለስ የትኛውም ሌላ ተጫዋች በጭራሽ የእርሱን ዘዴ እንዳይኮርጅበት ሲል የእግሩ ዱካዎች ያረፉበትን የሜዳ ክፍል በአቧራ እየሸፈነ የሚመጣ ተጫዋች እንደነበር የሚያወሳ ታሪክም ይነገራል፡፡ በእርግጥ ነገሩ አፈታሪክ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግን እየተስፋፋ የሄደው የአጨዋወት ስርዓትን ተቀባይነት ማሳያ ይሆናል፡፡ ” የአርጀንቲናውያን እግርኳስ ስልት ወደ መገለል አመራ፡፡” የሚለውን አስተሳሰብም ያወጀ ነበር።

ከ1934ቱ የአለም ዋንጫ በፊት በተጫዋቾች ወደ አውሮፓ መሰደድ የተዳከመው የሃገሪቱ ቡድን በውድድሩ የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በሲውዲን ተረታና ከአለም ዋንጫው ውጪ ሆነ፡፡ (ጣልያን ይህን ሁለተኛ የአለም ዋንጫ ስታሸንፍ አራት አርጀንቲናውያን ተጫዋቾች የብሄራዊ ቡድኗ አባላት የነበሩ መሆናቸውን ልብ ይሏል!) የ1938ቱን ሶስተኛ የአለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ያቀረበችው ጥያቄ ውድቅ ሲደረግባት ደግሞ ብሄራዊ ቡድኗን ወደ አስተናጋጇ ሃገር ፈረንሳይ ላለመላክ ወሰነች፡፡ ከዚያም ሁለተኛው የአለም ጦርነት ተጀመረ፡፡ ሁዋን ፔሮንም ሃገሪቱን የመነጠል አመራር ይከተሉ ጀመር፡፡ አርጀንቲና እስከ 1950 ድረስ በአለምአቀፍ መድረኮች ሳትታይ ርቃ ቆየች፡፡ ሆኖም ግን ራሷን ከአለም በነጠለችባቸው ጊዜያት የእግርኳስ ወርቃማ ዘመኗን አሳለፈች፡፡

በ1931 የሃገሪቱ ፕሮፌሽናል ሊግ ተጀመረና ትልልቆቹ ስታዲየሞች በበርካታ ሰዎች ይታጨቁ ጀመር፡፡ የሬድዮ ስርጭትና የጋዜጦች ሽፋንም ሙሉ ትኩረታቸው ሃገርአቀፉ የእግርኳስ ፍላጎት ላይ መስራት ሆኖ ተገኘ፡፡ በጊዜ ሂደት እግርኳስ የአርጀንቲናውያን ህይወት ዋነኛ መገለጫ ሆነ፡፡ ፖለቲከኞችም ጨዋታውን ሊጠቀሙበት አሰፈሰፉ፡፡ በተለይ ስፖርቱን የሚጠላው ሆርጌ ሉዊዝ ቦርጌስ እና እግርኳስ ወዳዱ አዶልፊዮ ባዮይ ካሴሬዝ እውነታን የመቀበል ችሎታን በምን መልኩ ማሳት ወይም ማዛባት እንደሚቻል ለማስረዳት እግርኳስን ምርጫቸው አደረጉ፡፡ ሁለቱ ሰዎች አንድ ላይ በተጣመሩበት <ኢዜ ኢስት ፔርሲ ፒ> የተሰኘ አጭር ታሪክ ያለው ትዕይንት ውስጥ አንድ ደጋፊ ከሚደግፈው ክለብ ሊቀመንበር ጋር ካደረገው ውይይት በኋላ “ሁሉም የእግርኳስ ጨዋታዎች ቀድሞ ውጤታቸው የተሰራና ቅድመ-ትዕዛዝ የተደረገባቸው ናቸው፡፡ ተጫዋቾ የሚጫወቱትም እያስመሰሉ እንጂ ከልባቸው አይደለም፡፡”  ከሚል የተሳሳተ ሀሳብ እንዴት እንደሚመለስ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

በ1920ዎቹ ብቅ ማለት የጀመረው አዲሱ የአቀራረብ ዘይቤ እያደገ ሄዶ <ላ ኑዌስትራ>  “-የኛ- የራሳችን አጨዋወት ዘዴ-” ወደሚባል አስደናቂ ደረጃ ደረሰ፡፡ <ክሪዮላ ቪቬዛ> ወይም “በሃገሬው ተወላጅ ጥበብ የተገኘ” የተባለለት ስልት በሃገሪቱ መስፋፋቱን ቀጠለ፡፡ በ1953 እንግሊዝን የወከሉ አስራ አንድ ተጫዋቾች በአርጀንቲና የ3-1 ሽንፈት ከደረሰባቸው በኋላ ይህ ስያሜ ይበልጡን እየታወቀ ሄደ፡፡ ላኑዌስትራ በእርግጥም አርጀንቲናውያኑ “መጤዎችን” የሚያሸንፉበት የአጨዋወት ስርዓት ስለመሆኑ ታየ፡፡ (ለነገሩ ያ ጨዋታ የተወካዮች ግጥሚያ እንጂ ሙሉ በሙሉ እንግሊዝ ለአለም አቀፍ ጨዋታዎች ያዘጋጀችው ቡድን አልነበረም፡፡) ሆኖም ድሉ አርጀንቲና ቀደም ብላ አጠቃላይ የእግርኳስ አቀራረብ ላይ የነበራት እና ከማጥቃት የሚገኝ ደስታን የማስቀደም ፍልስፍና ማሳያ ሆነላት፡፡ በመስከረም 1936 እና በሚያዝያ 1938 መካከል በነበሩት አስራ ዘጠኝ ወራት ውስጥ በአርጀንቲና ሻምፒዮና ላይ ግብ ያልተቆጠረበት የአቻ ውጤት አልተመዘገበም፡፡ ይሁን እንጂ ግቦቹ የታሪክ አካል ከመሆን የዘለለ ፋይዳ አልነበራቸውም፡፡ <ኦን ሂሮይስ ኤንድ ቶምብስ> ከተሰኘው  ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሃፉ (የእንግሊዘኛ ትርጉም ያልተሰራለት በመሆኑ ያስቆጫል!) ውስጥ ኤርኔስቶ ሳባቶ አንዲት ቁንጽል ሐሳብ የያዘች ተረት ለይቶ ያወጣና ስለ “ላ ኑዌስትራ መንፈስ” ያወጋናል፡፡

“ዩሊየን ዲ’አርካንጌሎ የተባለው ገጸባህሪ ለጀግናው ማርቲን በ1920ዎቹ ስለነበሩ ሁለት የኢንዲፔንደንቴ መስመር አጥቂዎች ወግ ያጫውተዋል፡፡ አልቤርቶ ላሊን (ላ ቻንቻ) እና ማኑዌል ሲዎኔ (ኤል ኔግሮ) የሚባሉት እነዚህ ወጣቶች እግርኳስን መጫወት የሚኖርብን “በዚህኛው መንገድ ነው፡፡” ብለው የተቃረኑትን  ሁለት የአጨዋወት አስተሳሰቦች የሚወክሉ ተጫዋቾች ነበሩ፡፡ ዲአርካንጌሎም ማርቲንን ” በጥሩ ሁኔታ ማብራሪያ የሚሰጥ ተረት አጋራህና እነዚያ ሁለት ዘዴዎች ግልፅ ይሆኑልሃል፡፡” ይለዋል፡፡ “በአንድ የቀትር ጨዋታ እረፍት ሰዓት ላይ ኤል ኔግሮ ላሊንን ” ሰውየው ኳሷን ብቻ አቀብለኝ! እኔ ሄጄ ግቧን ማስቆጠር እችላለሁ!” ይለዋል፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ ተጀመረና ላሊን ለኤል ኔግሮ  ኳሷን አቀበለው፡፡ ኤል ነግሮም ኳሷን አገኛትና እንዳለውም ግቧን አገባ፡፡ ሲዎኔም እጆቹን ወደ ላይ ዘርግቶ በደስታ ወደ ላሊን እየከነፈ “አየህ አይደል ላሊን! አየህ?” ብሎ ጮኾ ጠየቀው፡፡ ላሊንም “አዎ አየሁ፤ ግን ምንም ደስታ አላገኘሁበትም፡፡ አንተ ግን ሐሴት እያደረግህ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ የመላው አርጀንቲናውያን እግርኳስ ችግር ነው፡፡” የሚል መልስ ሰጠው፡፡

በተጫዋቾች የግል ቴክኒካዊ ክህሎት ላይ የተመረኮዙና ለተመልካቾች ተዝናኖትን የሚፈጥሩ አብዶዎች ወይም ፊንታዎች ተጋጣሚን የማሸነፍ ያህል ጠቀሜታ ኖራቸው፡፡ ከግማሽ ምዕተ አመት ቀደም ብሎ ብሪታኒያ ራሷ እግርኳስን “ትክክለኛ” በሆነ መንገድ መጫወቷን ስለመቀጠል፣ (ማራኪነቱ እምብዛም ቢሆንም) ድሪብሊንግ ላይ ማተኮር አልያም ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የሚያስችል ዘዴን መከተል በሚሉ የሐሳብ ክፍፍሎች መሃከል ነበረች፡፡ በ<ቪቬዛ> ባህል ተሸብቦ አልፎአልፎም ቢሆን ከውጪ በሚመጡ ተጋጣሚ ቡድኖች ሽንፈት ሲገጥመው ታክቲካዊ ጥገናዎች እያደረገ ሃያ አመት የከረመው አስደሳቹ የአጨዋወት ዘይቤ እያበበ ሄደ፡፡ የጨዋታው  አቀራረብ የአርጀንቲናን እግርኳስ ረዘም ላለ ጊዜ ባይጠቅምም በሌላ ስልት እየተተካ ማራኪነቱ ልዩ ሆኖ ቀጠለ፡፡

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

-Sunderland: A Club Transformed (2007)

-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

-The Anatomy of England (2010)

-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

-The Anatomy of Liverpool (2013)

-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)


ቀደምት ምዕራፎች
መቅድም LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሶስት LINK