በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የምዕራፍ ሦስትን የመጀመርያ ክፍል እነሆ ብለናል፡፡
|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ | LINK |
እግርኳስን በዘላቂነት ሳቢ እና ተወዳጅ ካደረጉት ሁነቶች መካከል በአንደኛው የሜዳ ክፍል የሚፈጠር መጠነኛ ለውጥ በሌላኛው ቦታ ያልተጠበቀና መሰረታዊ ተጽዕኖ እንዲኖር የማድረግ አቅም መያዙና ሁሉን አካታች መሆኑ ነው፡፡ በ1925 ብሪታኒያ ውስጥ የነበሩ እግርኳስ ማኅበራት ከ<ጨዋታ ውጭ> ህግ ላይ ለዘብ ያሉ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ዓለም አቀፉን ቦርድ የመወትወታቸው ምክንያት በጨዋታዎች የሚቆጠሩ አናሳ ግቦችን በሚመለከት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ይሆን ዘንድ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ኖትስ ካውንቲ ቀዳሚነቱን ቢይዝም በጊዜው ሌሎች በርካታ ክለቦች አታካች የመከላከል ዘዴ የሆነውን የ<ጨዋታ ውጭ ወጥመድ> በመስራት ረገድ የተካኑ ነበሩ፡፡ ኒውካስል ዩናይትዶች ደግሞ የስልቱ ባለሟል በሆኑት ጥንድ የመስመር ተከላካዮቻቸው ፍራንክ ሃድስፔዝ እና ቢል ማክራከን አማካኝነት የበለጠ ተጠቃሚዎች ሆኑ፡፡ በዚህ ዘዴ ከሜዳው አጋማሽ መስመር ታችና ላይ ባሉት ሁለቱም ጎኖች በሚገኙ የመጫወቻ ስፍራዎች የጨዋታው ሒደት ቅርጽ ሲጠብና በሜዳው ቁመት የሚለጠጡ እንቅስቃሴዎች ሲታመቁ ተስተዋለ፡፡ በየካቲት 1925 ኒውካስሎች ከበሪ ጋር 0-0 ከተለያዩ በኋላ የነባሩ <የጨዋታ ውጭ> ህግ ጉዳይ መጨረሻው ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ ይህ ጨዋታ ቡድኑ በውድድር ዘመኑ ለስድስተኛ ጊዜ ያለ ግብ አቻ የተለያየበት ሆነ፡፡ ክለቡ ከዚያ ቀደም አሳይቶ በማያውቀው መልኩ በአመቱ መጨረሻ ያስመዘገበው አማካይ 2.58 ግብ የማስቆጠር ንጻሬ እጅግ ደካማ የውድድር አመት ማሳለፉን አሳበቀበት፡፡ የእግርኳሱ አሰልቺ ገጽታ ናረ፤ የተመልካቾች ቁጥርም ቁልቁል ወረደ፡፡ በዚህ የተነሳ ማህበሩ አፋጣኝ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ተረዳ፤ ችግሩን ለመፍታትም ቁርጠኛ አቋም አሳየ፡፡
የ<ጨዋታ ውጭ ወጥመድ> ስልት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሄድ ከ1866 ጀምሮ የተለመደውና ” አንድ የፊት መስመር ተሰላፊ በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገኝ በእርሱና በባላጋራው ቡድን የግብ ክልል መካከል ሶስት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች (ግብ ጠባቂውን ጨምሮ ሁለት የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች) ሊኖሩ ይገባል፡፡” የሚለው ቀዳሚ እግርኳሳዊ ህገ-ደምብ በወቅቱ አመራሮች አማካኝነት መጠነኛ ማሻሻያዎች ሲደረግበት ሰነበተ፡፡ ለአብነት ያህልም በሚያዝያ 1906 በተካሄደው የስኮትላንድ እና የእንግሊዝ ጨዋታ የኮረንቲያንሱ ተጫዋችና የእንግሊዛውያኑ አምበል ሃሪስ በጉዳት ምክንያት ጨዋታውን መጨረስ ባልቻለው የግራ መስመር አማካዩ ሃሪ ማክፔስ ምትክ ቀደም ሲል መደበኛ የአቀያየር ልማድ የነበረውን (አንድ ተጫዋች ከፊት መስመር ወደኋላ እንዲያፈገፍግ ማድረግ) በመተው የግራ መስመር ተከላካዩን ኸርበርት በርጌስ ወደ ፊት በመግፋት ለተጋጣሚያቸው የሜዳ ክልል የቀረበ <የጨዋታ ውጭ መስመር> እንዲኖር አደረገ፡፡ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ሮበርት ክሮምተን ደግሞ በጥልቀት ወደ ኋላ አፈግፍጎ የስኮትላንዶችን ረጃጅም ቅብብሎች ሲያጨናግፍና ሲያመክን ዋለ፡፡ ሌሎች የቡድኑ ተጫዋቾችም ከስኮትላንዶቹ የግብ ክልል አስራ ስምንት ሜትር ድረስ ቀርበው ተጋጣሚዎቻቸው በነጻነት እንዳይንቀሳቀሱ እዚያው አፈኗቸው፡፡ በ1970 ብሪያን ጄምስ የሁለቱን ሃገራት የጥንት ጨዋታዎች ተተንተርሶ በጻፈው <እንግሊዝ-ከ-ስኮትላንድ> የተሰኘ መጽሃፉ የዚያ ዘመን ዘገባዎችን ጠቅሶ ” ሃሪስ ጥንቃቄን በማስቀደም ወደኃላ አፈግፍጎ ለመጫወት ሲሞክር ጨዋታው ወለፈንዲ ነገር ሆነ፡፡ ተመልካቹም በፊት መስመሩ ላይ የተደረገውን ለውጥ በእጅጉ ተቃወመ፡፡ የክሮምተን ወደኋላ መመለስና የእንግሊዞቹ ተከላካዮች በስኮትላዶቹ አጥቂዎች መሃል እየተሰገሰጉ ተጋጣሚዎቻቸውን በአስራ ስምንት ሜትር ክልል ውስጥ በተደጋጋሚ <ከጨዋታ ውጭ> ማድረጋቸው ደጋፊዎችን ክፉኛ አስቆጣ፡፡” ሲል ያወሳል፡፡
በጨዋታው እንግሊዝ 2-1 ተረታች፤ ለእግርኳሱ ውበት የሚቆረቆሩ አካላትም ከፍተኛ የተቃውሞ ጩኸት አስነሱ፡፡ ” በእንግሊዛውያኑ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘውና በአንድ የኋላ መስመር ተከላካይ ብቻ የሚደረገው የአጨዋወት ስልት በክለብ እግርኳስ ውስጥ ዘወትር ቅሬታ የሚነሳበት አጀንዳ እንደሆነ ታየ፡፡ ብሄራዊ ቡድኖችም የሚቆጠርባቸውን የግብ መጠን ለመቀነስ ሲሉ ተጋጣሚን በወጥመድ ውስጥ ለመክተት የሚያቅዱ ከሆነ ውሳኔያቸው በጨዋታው ተፈጥሯዊ ይዘት ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ አጠያያቂ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡” ሲል ዘገባው በሰፊዉ አብራራ፡፡ በ1906 እንግሊዝ ያደረገቻቸውን ሶስት ግጥሚያዎች በአምበልነት የመራው ሃሪስ ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ሃገሪቱ ባካሄደቻቸው ጨዋታዎች በድጋሚ የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ቀረ፡፡ በቀጣዩ አመት ደግሞ የ<ጨዋታ ውጭ> ህግ መጠነኛ ለውጦች ተደረጉበት፡፡ በዚህኛው ማሻሻያ መሰረት ማንኛውም በራሱ ሜዳ ክልል ውስጥ የሚገኝ ተጫዋች በምንም አይነት መንገድ ከ<ጨዋታ ውጭ> ሊሆን እንደማይችል ተደነገገ፡፡
የ<ጨዋታ ውጭ ወጥመድ>ን የሚመለከተው አከራካሪ ሐሳብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄ ከተበጀለት በኋላ ጎታች እክል እንዳይገጥመው ከፍተኛ ጥረት ተደረገ፡፡ ከአንደኛው የአለም ጦርነት በፊት በነበሩት አመታት የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በጥልቀት የታሰበባቸውና ጥንቃቄ የታከለባቸው አዳዲስ የ<ጨዋታ ውጭ> ህግጋት በቀጣይ ጊዜያትም መደበኛ ሆነው ጥቅም ላይ የመዋላቸው አዝማሚያ እየጎለበተ ሄደ፡፡ የኖትስ ካውንቲዎቹ ተጣማሪ የመስመር ተከላካዮች ኸርበርት ሞርሊ እና ጃክ ሞንጎመሪ የሒደቱ ጠንሳሾች ቢሆኑም የተጋጣሚ ተጫዋቾችን ከጨዋታ ውጭ ወጥመድ ውስጥ በመክተት የማክራከንን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪና ታዋቂ ሰው አልነበሩም፡፡ በዚያ ዘመን በሚወጡ የካርቶን ምስሎች ላይ ማክራከን የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾች የጨዋታው እንቅስቃሴ አካል እንዳይሆኑ በሚያደርግበት ወጥመድ ውስጥ ሲገቡ ደስተኛ ሆኖ ሲያጨበጭብ ይታይ ነበር፡፡ ተጫዋቹ በተደጋጋሚ ጊዜና በራሱ መንገድ እንቅስቃሴው ከጨዋታ ውጭ ስለመሆኑ አቤቱታ ሲያቀርብም ይስተዋላል፡፡
የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን በዘመናዊ የ<ጨዋታ ውጭ ወጥመድ> ውስጥ የማስገባት ዘዴን በጆርጅ ግርሃም ስር የሰለጠነው አርሰናል በሚገባ አሳይቷል፡፡ የቡድኑ የኋላ መስመር ተሰላፊዎች ምትሃታዊ ክስተት በሚመስል መልኩ በአንዲት ቅጽበት ውስጥ ሁሉም ተከላካዮች በአንድ የአግድሞሽ መስመር ላይ በመገኘት እጆቻቸውን ወደ ላይ ከፍ ያደርጉና የተጋጣሚ ቡድንን ተጫዋቾች ወጥመዳቸው ውስጥ ይጥሏቸው ነበር፡፡ በእርግጥ ከ1925 በፊት በነበሩት ጊዜያት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾችን ከጨዋታ ውጭ ወጥመድ ስር የማስገባቱ ስልት ከዘመነኛው ዘዴ ፍጹም ለየት ባለ መርህ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ በዚያ ጊዜ ሁለቱ የመስመር ተከላካዮች በተመሳሳይ ሰዓት በአንድ የጎንዮሽ መስመር ላይ የመገኘት እድላቸው እጅጉን ጠባብ ነበር፡፡ ይህንን የማጥቃት ጨዋታ አደናቃፊ ስርዓት በዋናነት የተገበሩት ከአንደኛው የአለም ጦርነት በፊት ለእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በጋራ ወደ ሃያ ሶስት ጨዋታ ያደረጉት የዌስትብሮሙ ጄሲ ፔኒንግተን እና የብላክበርኑ ቦብ ክሮምተን ነበሩ፡፡ “ክሮምተን ወደኋላ ሲያፈገፍግ የዌስትብሮሚቹ ደጀን ብዙውን ጊዜ አራተኛው የመሃል አማካይ እስኪመስል ድረስ ርቀቱን ጠብቆ ወደፊት ይገፋል፡፡” ሲል የቀድሞው የአስቶንቪላ አጥቂ ቻርሊ ዋላስ ስለዚያ ጊዜ ሁኔታ ያብራራል፡፡ “የፔኒንግተን አጨዋወት የደፋር መስመር ተከላካይ ባህሪ መገለጫ ነው፡፡ ጨዋታውን የሚከውንበት ብልሃት እንዲሁም ከክሮምተን ጋር የሚፈጥረው የተሳካ የታክቲክ ጥምረት የተጋጣሚን የማጥቃት እቅድ ገና ከጅምሩ በማጨናገፍ ረገድ የበቁ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ሁሌም ቢሆን ፔኒንግተን አንድ አጥቂ ሊንቀሳቀስ በሚችልበት የመጨረሻው መስመር ላይ ይገኛል፡፡” በማለት ዋላስ የሁለቱን ጥምረት አድናቆት ይቸረዋል፡፡
በተሻሻለው የ<ጨዋታ ውጭ> ህግ አንድ አጥቂ የጨዋታው እንቅስቃሴ አካል እንዲሆን የሚከላከለው ቡድን ሶስት ተጫዋቾች (በረኛው እና ሁለት ተከላካዮች) በግቡ ውቅሮችና በፊት መስመር ተሰላፊ ተጫዋቹ መካከል እንዲገኙ ያስገድድ ስለነበር አጥቂዎች እጅጉን ወደ ፊት ከተጠጋው የተጋጣሚያቸው መስመር ተከላካይ ቦታውን መንጠቅ ተጠበቀባቸው፡፡ አንደኛው የመስመር ተከላካይ ከሌላኛው ጀርባ በመገኘት ሽፋን የመስጠትና ከቡድን አጋሩ ያለፉ ኳሶችን የማጽዳት አመርቂ ብቃት ማሳየት ነበረበት፡፡ ማክራከን ለብዙ አመታት አብረውት የተጣመሩ ብዙ ተጫዋቾችን አይቷል፡፡ ሆኖም ከሃድስፔዝ ጋር ያሳየው ውህደት ከሁሉ የላቀው እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ” ያለምንም ጥርጥር የማክራከን አጨዋወት ስልት ሃሳቦች ለአንድ ጨዋታ ብቻ የታለሙ እንዳልሆኑ እገምታለሁ፡፡ አዳዲስ ሃሳቦችን የመፍጠር ብቃቱ የጨዋታውን መልክ የማሳደግ አቅም ነበረው፡፡ ሲል ሃድስፔዝ በጨዋታ ውጭ ወጥመድ ዙሪያ የሚሰጡ አሉታዊ አስተያየቶች ላይ የድጋፍ መከራከሪያውን <ሼፊልድ ቴሌግራፍ ኤንድ ስታር ስፖርትስ ስፔሻል> ላይ ጽፎ አቅርቧል፡፡ ” ያም ሆኖ እዚሁ ደንብ ላይ ስህተት ተፈጥሯል፡፡ የማክራከን ዘዴ ጨዋታዎችን የማበላሸት እቅድ አልነበረውም፡፡ እንዲያውም ጨዋታዎች የተበላሹት የተጋጣሚ አጥቂዎች እንደዚህ አይነቶቹ የጨዋታ ደንቦች ስለሚያስከትሏቸው ተግዳሮቶች እና የጨዋታ ውጭ ወጥመድ ታክቲኳችን አቅም ሊያሳጡ የሚችሉ እቅዶችን ማበጀት ሲያቅታቸው ነው፡፡ በእርግጥ ይህንን የጨዋታ ውጭ ህግ በሚመለከት የፊት መስመር ተሰላፊዎች በተደጋጋሚ ሆን ብለው የሚዘነጉት በጣም ጥሩ የሆነ አንድ ማምለጫ መመሪያ አለ፡፡ ማክራከን ሲያሻው ወደ ፊት ይሩጥ አልያም ሌላ ውሳኔ ያድርግ አጥቂዎች ከኳሱ ጀርባ ከሆኑ የጨዋታው እንቅስቃሴ አካል ይሆናሉ፡፡” በማለት አጥቂዎች ከዚህ ደንብ በተጻራሪ ማሳየት ስላለባቸው ብልሃት ይናገራል፡፡
የወቅቱ የእግርኳስ ባለስልጣናት ስጋት ገባቸውና በ1921 የጨዋታ ውጭ ህጉ ላይ ሌላ ለውጥ አመጡ፡፡ ማህበሩ ከእጅ ውርወራ በሚነሳ ኳስ ተጫዋቾች ከጨዋታ እንቅስቃሴ ውጪ የማይሆኑበትን መመሪያ አወጣ፡፡ በ1925 ደግሞ ይበልጥ ተጽዕኖ የሚፈጥር ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ታመነበት፡፡ በዚህም መሰረት የእግርኳስ ማህበሩ መፍትሔዎች ይሆናሉ ብሎ ያመነባቸውን ሁለት የተለያዩ አማራጮች ይዞ ብቅ አለ፡፡ የመጀመሪያው፥ “አጥቂው ከጨዋታው ውጪ እንዳይሆን በእርሱና በተጋጣሚው የጎል ክልል መሐል ሁለት ተጫዋቾች ብቻ መገኘታቸው በቂ ይሆናል፡፡” የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፥ ” በሁለቱም የሜዳው አጋማሾች ከተጋጣሚ የግብ ክልል አርባ ያርድ (36.576ሜትር) ያህል የሚርቅ የጎንዮሽ መስመር ኖሮ አጥቂው በዚያ ክልል ውስጥ ካልሆነ ከጨዋታ እንቅስቃሴ ውጪ አይሆንም፡፡” በሚል የቀረበው ነበር፡፡ እነዚህ <ከጨዋታ ወጭ> ህግን የሚመለከቱ ማሻሻያዎች ለህዝብ በተከታታይ የሚቀርቡ ትዕይንቶች ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች በመጀመሪያው አጋማሽ አንደኛው፣ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ሌላኛው አማራጭ በሙከራነት እንዲገመገሙ ስምምነት ተደረገባቸው፡፡
በዚያው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ለንደን በተደረገው ጉባኤ የእግርኳስ ማህበሩ አንድ የማጥቃት ሒደቱን እየመራ ያለ የፊት መስመር ተሰላፊ ከፊቱ ሁለት የሚከላከሉ ተጫዋቾች ካሉ አጥቂው በጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ መገኘቱን የሚቀበል ማሻሻያ እንደሚመርጥ ውሳኔ አሳለፈ፡፡ የስኮትላንድ እግርኳስ ማህበርም ወዲያውኑ ማሻሻያውን በይሁንታ ተቀበለና ለአለም አቀፉ ቦርድ ሊቀየር ስለታሰበው <የጨዋታ ውጭ> ህግ ማብራሪያ አቀረበ፡፡ ለቀጣዩ የ1925/6 የውድድር ዘመንም በተግባር ላይ ለማዋል እንደታቀደ አክሎ ገለጸ፡፡ ከዚያ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተጋጣሚዎች ላይ የ<ጨዋታ ውጭ ወጥመድ>ን እንደ አንድ የማሸነፊያ ዘዴ የሚጠቀም ቡድን አንዱ የመስመር ተከላካይ የተጋጣሚ የፊት መስመር ተሰላፊ እንቅስቃሴን ሊገታ ወደ ፊት ሲሄድ ሌላኛውን ሽፋን ሰጪ አድርጎ ይይዝ ነበር፡፡ አዲሱ ህግ ግን በረኛውን ከተጋጣሚው አጥቂ ጋር አንድ-ለ-አንድ በሆነ ግንኙነት የሚያጋፍጥ አደጋ ላይ ይጥላል የሚል የተዛባ ግምት እንዲወሰድ አደረገ፡፡
ለጊዜው የህግ ማሻሻያው ስኬታማ የሆነ መሰለ፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በጨዋታ የሚቆጠር አማካይ የግብ መጠን ወደ 3.9 አሻቀበ፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ በነበረው የእግርኳስ አጨዋወት ዘይቤ ላይ ትልቅ ለውጥን ፈጠረ፡፡ በለውጡ ምክንያትም የሜዳ ላይ መዋቅራዊ እርከን ኸርበርት ቻፕማን ወዳጎለበተው “ሶስተኛው ተከላካይ” ወይም “WM ፎርሜሽን” የተሰኘ አዲስ ቅርጽ ከፍ አለ፡፡ ይህም ነባሩን የእንግሊዝ እግርኳስ አጨዋወት መንገድ አሉታዊ ገጽታ ከፍ አድርጎ ውደቀቱን አፋጠነው፡፡
እንግሊዝ በ1953 ደጋፊዎቿ ፊት በሃንጋሪ የ6-3 አስደንጋጭ ሽንፈት ከገጠማት በኋላ በሑጎ ሜይዝል ታናሽ ወንድም ዊሊ ሜይዝል የተጻፈው <ሶከር ሪቮሊውሽን> የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ክርክሩ ጠንከር ብሎ ቀርቧል፡፡ በእርግጥ ሜይዝል በኦስትሪያ የነበረውን ጸረ-አይሁድ ዘመቻ አምልጦ ወደ ለንደን ከመሰደዱ በፊትም እንግሊዝ-ነክ ነገሮችን በጽኑ የሚያወድስ ሰው በመሆኑ መጽሀፉ ያለፈበትን የመጤነት ውጣ ውረድ በመንገብገብ ስሜት የሚገልጽና እንግሊዛዊነትን ደግሞ ፍጹም አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ ይንጸባረቅበታል፡፡ ሆኖም ሜይዝል በውጭ ሀገር የህትመት ስራዎች ስለ እንግሊዝ እግርኳስ በመጻፍ በስፖርት ጋዜጠኝነት የተከበረ ባለሙያ ሆነ፡፡ <ሶከር ሪቮሊውሽን> በጥሩ የቃላት አመራረጥ ስልት የቀረበ ከመሆኑም በላይ ከዘመናዊ አተያይ አንጻር እንኳ በደማቅ ሁኔታ ነጥሮ የወጣ ስራ ሆኖ ተገኘ፡፡ ለሜይዝል የተቀየረው የ<ጨዋታ ውጭ> ህግ ከእግርኳስ በየዋህነት አሉታዊ ምላሽ የማግኘት እና ከዋሾ ባህሪ አሸናፊ መሆን የሚቻልበትን የዘቀጠ ውድቀት አመላካች ነበር፡፡
በነበረው ሩቅ አሳቢነት ከወንድሙ የማያንሰው ዊሊ ሜይዝል ሁኔታዎችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚመለከቱ ስራ አስኪያጆች የሒሳብ ማወራረጃ ሰነዳቸውን ከማስተዳደር ያለፈ ተግባር ሳይከውኑ ለእግርኳሱ ውድቀት ህገ-ደንቦቹን ተወቃሽ ሲያደርጉና ጨዋታው እያሳየ ላለው ትክክለኛ ያልሆነ አቀራረብ ራሳቸውም ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ አለማሰባቸውን ተረዳ፡፡ እነዚህ በእግርኳሱ አመራር ቦታ ላይ የነበሩ ሰዎች “የጨዋታው ህግጋት ለተራው ተመልካች ግልጽ ሆነው እንዲቀርቡ የሚያስችሉ መጠነኛ ማሻሻያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡” በሚል አቋማቸው ገፉበት፡፡ ይሁን እንጂ እያንዳንዱን መመሪያ ለማቅለል የተወሰደው የቃላት ስንጠቃና ብዛት ነገሩን ይበልጥ አወሳሰበው፡፡
የክርክሩ ጡዘት “በቀላሉ ጥሩ ጨዋታ የሚያሳዩ” እና “ማሸነፍን ቅድሚያ የሚሰጡ” በሚሉ ሁለት ተጻራሪ ጎራዎች የመከፋፈል ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ በዚያ ጊዜ የተካሄዱት ክርክሮች የጥልቀት እይታ ለሚሹ ጉዳዮች እምብዛም ትኩረት የማይቸሩ “የግብር ይውጣ” አይነት ይዘት ያላቸው ነበሩ፡፡ የሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመኖቹ ውይይቶች ግን ተጽዕኖአቸው ላቅ ወዳለ ደረጃ ተሸጋገረ፡፡ “ሊግ የመመስረት ጥያቄዎች መነሳት ጀመሩ፤ ሃሳቡ እረፍት የሚነሳ ጉዳይም ሆነ፡፡” ሲል ብሪያን ግላንቪል አውስቷል፡፡ “ጨዋታዎች የመጨረሻው ግባቸውና ዋነኛ ጠቀሜታቸው የግድ ውጤት እንዲሆን ካልተፈለገ አማካዩ የአጨዋወት ደረጃ አስገራሚ እድገት ይኖረዋል፡፡” የሚለውን ሐሳብ ኸርበርት ቻፕማን ተቀበለው፡፡ “የሽንፈት ፍርሃት እና በጨዋታ ነጥብ የመጣል ስጋት የተጫዋቾችን በራስ መተማመን ይሸረሽራል፡፡ ሁኔታዎች ሲመቻቹ <ፕሮፌሽናሎቹ> ከሚታሰቡትም በላይ የበቁ ይሆናሉ፡፡ <ጥሩ እግርኳስ> ካለን ደግሞ ቀስ በቀስ የአሸናፊነትን ግዴታዊ ግብ እና ለነጥቦች የምንቸረውን ግምት የምንቀንስበት መንገድ ይኖረናል፡፡” የሚል እምነት ያራምድ ነበር ቻፕማን፡፡ ከዚያ በኋላ በእግርኳስ ማሸነፍና መሸነፍ የሞትና የሽረት ጉዳይ አልሆነም፡፡
በ2009 በ<ዘ ታይምስ> መጽሔት የምንጊዜውም የቶተንሃም ሆትስፐር ምርጡ ተጫዋች ተብሎ የተሰየመው ዳኒ ብላንችፍላወር ስለዚህ ሁኔታ ሲያብራራ “ትልቁ ስህተት የሚጀምረው ‘ዋናው ነገር ጨዋታው ሲሆን አሸናፊነት ተከትሎት የሚመጣ ጉዳይ ነው!’ ከሚለው ሐሳብ ነው፡፡ የእግርኳስ ምሉዕነት ከስኬት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፡፡ እግርኳስ የውበት፣ ድርጊቶችን በዘይቤ የመከወንና የመስፋፋት ሒደትን ይመለከታል፡፡ ” ሲል አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ በዚህ እሳቤ ሙሉ በሙሉ የሚስማሙበት ሰዎች እንኳ በእርግጠኝነት በገምጋሚዎች ነጥቦችን ከአስር እየመዘኑ እንጂ ተቻኩለው አይደመድሙም፡፡ ነገሩ ቀላል ቢመስልም ያለመታደል ሆኖ እያደር ጨዋታን ማሸነፍ ብቻ የሚመርጡት አሉታዊ ጉዳዮችን የሚያሰላስሉበት እውነታ ላይ ይደርሳሉ፡፡ <ላ ኑዌስትራ> ለአርጀንቲናውያኑ ያሸበረቀ የከፍታ ጊዜ ካስገኘላቸው፣ ኦስትሪያኖቹም ውበት ላለው እግርኳስ የሚያሳዩት ልባዊ ፍላጎት ካሻቀበ በኋላ የፋሺስታዊው ስርዓት ባይከተል ኖሮ እግርኳሳዊ ስልቶቹ ዘላቂ እድገት ያሳዩ ነበር፡፡ እንግዲህ ወርቃማዎቹ አመታትም አለፉ፤ እናም አስደሳቹ ውስብስብ ያለመሆን ሒደት በዘላቂነት የሚቆይ አልሆነም፡፡
የ<ጨዋታ ውጭ> ህግ ለውጥን ተከትሎ ወሳኝ የሚባሉ ውጤቶች ታዩ፡፡ የፊት መስመር ተሰላፊዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ሰፋ ያለ ቦታ አገኙ፤ ጨዋታው በሜዳው ቁመት የሚለጠጥበት እድል ተመቻቸ፤ በረጃጅሙ ከሚጠለዙ ኳሶች በላቀ በቅርብ ርቀት የሚደረጉ ቅብብሎች ተመራጭ መሆን ጀመሩ፡፡ አንዳንድ ቡድኖችም ከሌሎች በተሻለ አዲሱን የአጨዋወት ደንብ ተላመዱት፡፡ በ1925/26 የውድድር ዘመን ያልተለመዱ ውጤቶች ተመዘገቡ፡፡ በተለይ አርሰናሎች ቀጣይነት ያለው ስኬት የማሳየት ችግር ገጠማቸው፤ ሊረጋጉም አልቻሉም፡፡ በመስከረም 26 ሊድስ ዩናይትድን 4-0 ካሸነፉ በኋላ በቀጣዩ ሳምንት ጥቅምት 3 በኒውካስል ዩናይትዶች 7-0 ተረመረሙ፡፡
በቀኝ መስመር አጥቂነት የሚሰለፈውና የክለቡ ኮከብ የነበረው ቻርሊ ቡቻንም ቡድኑን በመልቀቅ በሰሜን ምስራቅ እንግሊዝ ቆይቶ ከሰንደርላንድ ጋር ስኬታማ ጊዜያትን ማሳለፍ እንደሚፈልግ በንዴት ለቻፕማን ገለጸለት፡፡ ይህኛው የአርሰናል በድን እቅድ የሌለውና የማሸነፍ እድሉ እጅግ ዝቅተኛ እንደሆነም ለአሰልጣኙ አብራራለት፡፡ ቻፕማንም በስራው ያሰበው የወደፊቱ ትልቅ ትልም ሲናድ ታየው፡፡ ከቡቻን ንግግሮች በአንደኛው ቅር ተሰኘ፡፡ ሌላው ቢቀር አሰልጣኙ በእቅድ የሚመራ ትጉህ ሰው ነበር፡፡
ይቀጥላል...
ስለ ደራሲው
ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡
-Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)
-Sunderland: A Club Transformed (2007)
-Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)
-The Anatomy of England (2010)
-Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)
-The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)
-The Anatomy of Liverpool (2013)
-Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)
-The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)
ቀደምት ምዕራፎች | |
መቅድም | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት | LINK |
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት | LINK |
ምዕራፍ 2 – ክፍል አንድ | LINK |
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሁለት | LINK |
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሶስት | LINK |
ምዕራፍ 2 – ክፍል አራት | LINK |