ሶከር መፅሀፍት | ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ (ምዕራፍ ሶስት – ክፍል ሁለት)

በእንግሊዛዊው የእግርኳስ ጸኃፊ ጆናታን ዊልሰን ደራሲነት በ2008 ለንባብ የበቃው Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics ን በሶከር ኢትዮጵያ በተከታታይ ክፍሎች እያቀረብንላችሁ እንገኛለን፡፡ በዛሬው መሠናዶም የምዕራፍ ሦስትን ሁለተኛ ክፍል እነሆ ብለናል፡፡

|| ያለፈውን ሳምንት ለማንበብ ይህን ይጫኑ LINK

ኸርበርት ቻፕማን

በሼፊልድ እና ወርክሶፕ ከተሞች መካከል የምትገኝ በከሰል ማዕድን ምርቷ የምትታወቅ ኪቪተን ፓርክ የተሰኘች ከተማ አለች፡፡ ኸርበርት ቻፕማን የተወለደው በዚህች አነስተኛ መንደር ውስጥ ነው፡፡ ቻፕማን በልጅነቱ ለእግርኳስ ባያደላ ኖሮ እንደ አባቱ በማዕድን ቁፋሮ ስራ ይሰማራ ነበር፡፡ በመጀመሪያ ለስታሊብሪጅ በመቀጠል ለሮችዴል ከዚያም ለግሪምሲ፣ ሲውንደን፣ ሺፒ ዩናይትድ፣ ወርክሶፕ፣ ኖርዛምፕተን ታውን፣ ኖትስ ካውንቲ እና በመጨረሻም ለቶትንሐም እግርኳስ ክለቦች ተጫወቶ አሳለፈ፡፡ በተጫዋችነት ዘመኑ ከችግሮች በቶሎ የሚላቀቅበትን ዘዴ በአግባቡ የሚፈጥር ብልህ ሰው የነበረ ከመሆኑም በላይ በምስጉን የታታሪነት ባህሪውም ይታወቅ ነበር፡፡  በጨዋታ ወቅት የቡድን አጋሮቹ በቀላሉ ሊለዩት እንዲችሉ ከወይፈን ቆዳ የተሰራና ገርጥቶ ወደ ቢጫነት የተቀየረ ጫማ ተጫምቶ የመጫወቱ ውሳኔ ቀድሞም ቢሆን በፈጠራ ሃሳብ የነበረው ችሎታ ኋላ በአሰልጣኝነት ህይወቱ እንዳገዘው ማሳያ ይሆናል፡፡

ቻፕማን የአሰልጣኝነት ሙያው በሞቀ ተቀባይነት አልጀመረለትም፡፡ በ1907 የጸደይ ወቅት ለቶተንሐም ወጣት ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ካደረገ በኋላ በገላ መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ጋደም ብሎ ሳለ የቡድን ጓደኛው ዋልተር ቡል በኖርዛምፕተን ክለብ ተጫዋች-አሰልጣኝ ለመሆን መቃረቡን እርሱ ግን የሙሉ ጊዜ ተጫዋችነት ህይወቱን ማራዘም እንደሚፈልግ ገለጸለት፡፡ ቻፕማን እድሉን ቢያገኝ የማሰልጠን መሻት እንዳለው ለቡል አልሸሸገውም፡፡ ቡልም ለኖርዛምተኖች ጓደኛውን ይቀጥሩ ዘንድ ሃሳብ ሰጣቸው፡፡ ኖርዛምፕተኖችም የቀድሞው ስቶክና ማንችስተር ሲቲ ክለቦች የመሃል አማካይ ሳም አሽዎርዝን በቦታው ለመሾም ያደረጉት ጥረትና   የማሳመን ምኞት ሳይሳካ ሲቀር የማሰልጠን ስራውን ለቻፕማን ሰጡት፡፡

ብዙዎች ለጨዋታ ይዘት የትኛውም አይነት ግምት አልያም አመለካከት ይኑራቸው ቻፕማን የስኮትላንዳውያኑ በቅብብሎች ላይ ያመዘነ አጨዋወት ደጋፊ እንደመሆኑ እርሱ የሚያሰለጥነው ቡድንም ይህ የብልሃትና በራስ የመተማመን ደረጃ ማሳያ የሆነ አቀራረብ እንዲኖረው ተመኘ፡፡ አሰልጣኙ የዚህ አይነቱ አቀራረብ መሰረታዊ እሳቤ ለእግርኳሱ እጅግ አስፈላጊ መላምት ማፍለቂያ ግብዓት እንደሆነ አመነ፡፡ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ከተመዘገቡ  መልካም የመነሻ ውጤቶች በኋላ ኖርዛምፕተኖች ቁልቁል መውረዱን ተያያዙት፡፡ በህዳር ወር መጀመሪያ በሜዳቸው በኖርዊች የተሸነፉበት ጨዋታ ውጤትም በደቡብ ሊግ ከሰንጠረዡ ግርጌ ወደ ላይ አምስተኛ ደረጃ ላይ ጣላቸው፡፡  የቻፕማን ቀዳሚው የስኬት ቀውስም ይህ ሆነ፡፡  ነገርግን ውድቀቱ ቻፕማንን ወደ ላቀ የሜዳ ላይ ተግባር መራው፡፡ ” አንድ ቡድን በጨዋታ በርከት ላሉ ደቂቃዎች ሊያጠቃ ይችላል፡፡” ለሚለው መነሻ ሐሳብ እውቅና ቸረ፡፡ የተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎችን ከመቆጣጠር ይልቅ ተከላካዮቻቸው ቦታቸውን ለቀው እንዲወጡ በማስገደድ ለማጥቃት አመቺ የሆኑ ክፍተቶችን መፍጠር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ታክቲካዊ እቅድ መሆኑን በመገንዘብ የእርሱ ቡድን ወደ ኋላ አፈግፍጎ እንዲጫወት ማበረታታት ጀመረ፡፡ በ1908 የገና በዓል ሰሞን ኖርዛምፕተኖች የደቡብ እንግሊዝ ሊግን ይመሩ ጀመር፤ በውድድር አመቱ መጨረሻ ደግሞ ሪከርድ በሆነ መጠን ዘጠና ግቦችን አስቆጥረው የሊጉን ዋንጫ አሸነፉ፡፡

በ1912 ቻፕማን ወደ ሊድስ ከተማ አቀና፡፡የአንደኛው የአለም ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በነበሩት ሁለት የውድድር ዘመናት ክለቡን ከሁለተኛ ዲቪዚዮን የደረጃ ግርጌ ውራነት አንስቶ ወደ ላይ በማውጣት አራተኛ ደረጃ ላይ አስቀመጠው፡፡ በዚህ ክለብ በትልቁ ከሚታወስባቸው የእግርኳስ ግኝቶች መካከልም አንዱን አሳካ፡፡ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ ተጫዋቾች ተሰባስበው ጥልቅ በሆነ ስሜት   በማስጠንቀቂያ ካርዶች ዙሪያ ክርክሮችን ሲያደርጉ ተመልክቶ የቡድን ውይይቶች በየትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ግንዛቤ  መስጠትና መመሪያዎችን ማስተላለፍ ጀመረ፡፡ ዳሩ ግን ጦርነቱ የሊድሶችን እግርኳሳዊ እድገት አስተጓጎለ፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ለቻፕማንም ሆነ ለቡድኑ የከፋው መዓት ተከተለ፥ “ሊድስ ለተጫዋቾች ተገቢና ፍትሃዊ ያልሆነ ክፍያ ፈጽሟል፡፡” የሚለው ክስ ክለቡ ላይ ቀረበ፡፡ ቻፕማንም የተጫዋቾች መረጃ የያዘውን ሰነድ እንዲያስረክብ ሲጠየቅ “አሻፈረኝ!” በማለቱ ክለቡ በሊግ ውድድሮች እንዳይሳተፍ እገዳ ተጣለበት፡፡ እርሱ ደግሞ ከጥቅምት 1919 ጀምሮ ከየትኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ ውጪ እንዲሆን የህይወት ዘመን ቅጣት ተላለፈበት፡፡

ከሁለት ዓመታት በኋላ ሲልቢ በተባለ አካባቢ በኦሊምፕያ ዘይት መሸጫና ኬክ መጋገሪያ ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት ላይ ሳለ ሃደርስፊልድታውኖች  ለወቅቱ አሰልጣኛቸው አምብሮስ ላንግሊ ረዳት ይሆነው ዘንድ ቻፕማንን ቀርበው አነጋገሩት፡፡ የላንግሊ ታናሽ ወንድም ሃሪ ከጦርነቱ በፊት ከቻፕማን ጋር አብሮ ስለተጫወተ ከቤተሰቡ ጋር ቀደም ያለ ትውውቅ መስርተዋል፡፡ ግብዣው ቻፕማንን አስደሰተው፡፡ የተጣለበት እገዳ እንዲነሳለትም ለእግርኳስ ማህበሩ አቤቱታውን አሰማ፡፡ ያለ ተጨባጭ ማስረጃ እና ትክክለኛ ማረጋገጫ በህገወጥነት የተፈረጁት ክፍያዎች ሲፈጸሙ እርሱ ከክለቡ ርቆ በባርንቦው የጦር መሳሪያዎች ፋብሪካ ውስጥ ሲሰራ እንደነበር አሳወቀ፡፡ የእግርኳስ ማህበሩ ምህረት አደረገለት፤ ቅጣቱም ተነሳለት፡፡ ከዚያም የሃደርስፊልዶችን ጥሪ ተቀብሎ በረዳት አሰልጣኝነት ስራውን ጀመረ፡፡ ከአንድ ወር በኋላም ላንግሊ የግል መጠጥ ቤቱን ለማስተዳደር ወስኖ ክለቡን ሲለቅ ቻፕማን የዋና አሰልጣኝነት መንበሩን ተረከበ፡፡ ወዲያውም በቡድኑ ውስጥ እምቅ ክህሎት የያዙ በርካታ ወጣት ተጫዋቾች ቢኖሩም እነርሱን የሚመራ ጀነራል እንደሚያስፈልግ ለክለቡ አስተዳደሮች ምክሩን ለገሰ፡፡ የአስቶን ቪላው ክሌም ስቴፈንሰን ደግሞ ለዚህ ኃላፊነት ሁነኛው ሰው እንደሆነ ጠቆማቸው፡፡ ያኔ ሰላሳ ሶስት አመቱ ላይ ይገኝ የነበረው ይህ ተጫዋች ቻፕማን በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ላይ ላሳደረው እምነት ትልቅ ግልጋሎት የሚሰጥበት አቅም ነበረው፡፡ ከቀዳሚ ልምዱ ለማጥቃት ወደ ፊት ከመስፈንጠሩ በፊት ወደ ኋላ ተመልሶ የተጋጣሚ ተከላካዮች መሃል በመገኘት ኳሱ በረጅሙ ሲመታ በድጋሚ በመውጣት ከጨዋታ ወጭ ወጥመድ ውስጥ የሚያመልጥበትን ብልሃት አዳብሯል፡፡ ዘወትር ትልቁን ምስል በሚያየውና ባለራዕይ በሆነው ቻፕማን አማካኝነት ፈጠን ባለ ሁኔታ በክለቡ ጥሩጥሩ መሻሻሎች ታዩ፡፡ በሊድስ ስታዲየም የነበረው የጋዜጠኞች ክፍል እደሳ ተደረገለት፤ መጫወቻ ሜዳውም አዲስ ሳር ለበሰ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በሜዳ ላይ የነበረው ብቃት እድገት አሳየ፡፡ ቀስበቀስ የለውጥ በሮች ገርበብ ማለት ጀመሩ፡፡

በ1922 ሃደርስፊልዶች የኤፍ.ኤውን ዋንጫ አሸነፉ፡፡ በስታምፎርድ ብሪጅ በተደረገው የፍጻሜ ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ የተገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት ቢሊ ስሚዝ ወደ ግብነት ቀይሮት ፕሪስተን ኖርዝ ኢንዶችን ረቱ፡፡ በግማሽ ፍጻሜው ኖትስ ካውንቲዎችን ሲያሸንፉ ድሉን ለማድመቅ ሲጥር የነበረውና በአህያ ቅርጽ ግሳንግሶች ተሞልቶ የታመቀው <ማስኮታቸው> እሳት ከመያዙ ውጪ ክለቡ ስኬታማ የውድድር አመት አሳለፈ፡፡ የቡድኑ አጨዋወት ስልት ማራኪ አልነበረምና የክለቡ ባለስልጠናት ያን ያህል ሊረኩ አልቻሉም፡፡  በቡድኑ የተለመደውና ተገቢ ባልሆኑ አካላዊ ጉሽሚያዎች ላይ የሚያመዝነው አቀራረብ የክለቡን እግርኳሳዊ መልክ አጠለሸ፡፡ የሃገሪቱ እግርኳስ ማህበርም ክለቡ እየተከተለ ባለው የጨዋታ ስልት ላይ ጠንከር ያለ ቅሬታ አቀረበ፡፡ ለወደፊቱ ቡድኑ በአጨዋወት ዘዴው እርማት እንደሚያደርግና በተለይ ደግሞ በፍጻሜዎች የአካል ንክኪ የሚበዛበትን አቀራረብ ሊያሻሽል  እንደሚችል ተስፋ ስለማድረጉ ገለጸ፡፡ ከዚያም ቻፕማን ከአማካይ ተጫዋቾቹ መካከል ቶም ዊልሰንን ወደ ኋላ በመሳብ ከተከላካዮቹ መሃል እንዲጫወት በማድረጉ <ሃደርስፊልድ ኤግዛማይነር> በተባለ ጋዜጣ ላይ “ታላቁ ፍጥነት ቀናሽ ” የሚል አስተያየት ተሰጠበት፡፡ አሰልጣኙም በዚህ ምክንያት ራሱን በመውቀስ ሒደት ውስጥ ስለመሆኑ ብዙዎች አመኑ፡፡ ቀደም ሲል ማህበሩ “በእግርኳሱ የሚታዩ ህገወጥና እንግዳ ተግባራትን ማሳወቅ አለባችሁ፡፡” ባለው መሰረት ክለቡ በዚህም ጉዳይ የተብራራ ምላሽ ይሰጠው ዘንድ ተማጸነ፡፡

በዚህ የሐሳብ ክፍፍል ውስጥ እግርኳስ ማህበሩ ለእያንዳንዳቸው የሜዳ ላይ ለየት ያሉ ትዕይንቶች አልያም ያልተለመዱ ክስተቶች ዝርዝር ማብራሪያዎች ይኑሩት-አይኑሩት መበየን ባይቻልም በወቅቱ <ትክክለኛው የአጨዋወት መንገድ> ተብሎ ከተወሰደው የሃገሪቱ ተለምዷዊ የእግርኳስ አቀራረብ ዘይቤ ግትር ግንዛቤ የቻፕማን ስልት እጅጉን ሩቅ እንደነበር እሙን ነው፡፡ በተመሳሳዩ መከራከሪያ ቻፕማን ለዊልሰን የሰጠው ሚና ምናልባት ለብቻው አንድ የተቃራኒ ቡድን ተጫዋች እንዲይዝ ባይሆን እንኳ በእርግጠኝነት የተጋጣሚያቸውን አጥቂ ቢሊ ሮበርትስን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ እንዲያጤን ነበር፡፡ ይህ አዲስ ሚና ደግሞ በእግርኳሱ የ<ጨዋታ ውጭ ደንብ> ላይ ምንም አይነት ማሻሻያ ሳይደረግ  በሁለቱ የመስመር ተከላካዮች መካከል የሚጫወት ቋሚ አማካይ እየመጣ መሆኑን የሚያመላክት ለውጥ ሆነ፡፡

በእርግጥም ሁኔታውን ለመገንዘብ ወደ ኋላ ዞር ብለን ብናስብ የአማካይ ተከላካይነት ሚና
በፒራሚድ ቅርጽ የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ስልት ውስጥ በግልጽ ባይታይም በዚሁ ፎርሜሽን ተጫዋቾች ኃላፊነቱን በውስጥ ታዋቂነት ይተገብሩት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የሚናው አለም አቀፋዊ ተቀባይነት የተገኘው ዘግይቶ ነው፡፡ ሁለት በ2-3-5 ፎርሜሽኖች የሚጫወቱ ቡድኖች ሲገናኙ ተጫዋቾቹ በሚሰጣቸው የሜዳ ላይ ሃላፊነት መሰረት በጨዋታው አምስት የፊት መስመር ተሰላፊዎች አምስት ተከላከዮችን ይጋፈጣሉ፡፡ ሁሌም የመሃል አማካዩ የተጋጣሚን የፊት መስመር የመሃል አጥቂ ይይዛል፡፡ ሆኖም አንዳንድ ቡድኖች የመስመር ተከላካዮቻቸው የተጋጣሚ ቡድን የመስመር አማካዮችን እንቅስቃሴ እግር በእግር እንዲከታተሉላቸው፤ የውስጠኛው መስመር አማካዮች ደግሞ የተቃራኒ ቡድን የመስመር አጥቂዎችን እንዲይዙላቸው ይመርጣሉ፡፡ የሼፊልድ ዩናይትዱ የቀኝ መስመር አማካይ ስለ ጉዳዩ ሲያስረዳ ” አንድ የቀኝ መስመር ተከላካይ የተጋጣሚን መስመር አማካይ የሚይዝ ከሆነ አጠቃላዩ የመከላከል መስመር ላይ የመበታተን ሁኔታ ይኖርና ክፍተቶች ይፈጠራሉ፡፡” በማለት ይገልጻል፡፡ ያም ሆኖ የወቅቱ የተከላካይ አማካዮች የተጋጣሚን የመስመር አጥቂዎች ፍጥነት ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡ ዋናው ነገር ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱም የአጨዋወት ስልቶች አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች መታየታቸው ነው፡፡ ከሁለቱ የትኛው የተሻለ እንደሆነ ለመወሰንም የግድ በወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታዎች ላይ መመስረት ይኖርብናል፡፡

ከጥንት ጀምሮ በታዩት ሁለቱ የአቀራረብ መንገዶች ውስጥ የተከላካይ አማካይ ቅድሚያ የመከላከል ኃላፊነት ነበረበት፡፡ በዚህም ሳቢያ በተከላካዮችና አማካዮች መካከል የነበረው የመከላከል እንዲሁም የማጥቃት ሚዛናዊ ውህደት በጥሩ መልኩ እንዲጠበቅ ሆኖ ቆየ፡፡ ብሬስፎርድ በጥር 1914 ” አልፎአልፎ አንድ ቡድን ሶስት አማካዮችን ተጠቅሞ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹን በሚፈለገው ደረጃ ስለማገዙ ሳስብ ጥርጣሬ ላይ እወድቃለሁ፡፡ ሁሉም ደስታ የሚያገኙት የማጥቃቱ ጨዋታ ላይ ነው፤ መከላከሉማ ራስን ለስቃይ ማመቻቸት ነው፡፡ በእኔ አስተያየት ምርጡ የመሃል ክፍል ክህሎትና አካላዊ ጥንካሬ የተዋሃዱበት እንጂ የግድ ተመሳሳይ ሚናን የሚወጡ ሶስት ተጫዋቾች የተጣመሩበት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሁለት እጅግ የላቁ የምርት ማሽኖች ቢኖሩህ ለእነዚሁ ማሽኖች ከተመረቱበት ድርጅት ሃይል ተቆጣጣሪ ትፈልግላቸዋለህ፡፡ ሁለት ጠንካራ ፍጥነት መቀነሻ መሳሪያዎች ካሉህ ደግሞ  የምርት ማሽኖቹ በተሻለ ጀረጃ እንዲሰሩ የሚያደርግ ሌላ ሶስተኛ መሳሪያ ሊኖርህ የግድ ይሆናል፡፡” ሲል በአንድ ቡድን ውስጥ ሚናቸው የተለያየ ተጫዋቾች መኖር እንዳለባቸው ጽፏል፡፡

የአንደኛው ዓለም ጦርነት ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ በነበሩት ጊዜያት አንዳንድ የተከላካይ አማካዮች በመከላከል አጨዋወት ስርዓት ላይ ያላቸውን አረዳድ በአግባቡ ማዳበር ጀመሩ፡፡ በወቅቱ የተከላካይ ክፍላቸው በማጥቃቱ ረገድ በነበረው የላቀ አስተዋጽኦ ተለይተው የሚታወቁት ኒውካስሎች የበለጠ የፈጠራ ክህሎት የነበራቸው ተጫዋቾቻቸው ከለላ እንዲያገኙ በማሰብ በ1909 ከስኮትላንዱ አበርዲን ዊልፍ ሎው የተባለ የተከላካይ አማካይ አስፈረሙ፡፡ <ሼፊልድ ቴሌግራፍ> እና <ስታር ስፖርትስ ስፔሻል> በተሰኙ ጋዜጦች ላይ የወጡ ቀደምት ጽሁፎችን በተለይ ደግሞ የ1914 ህትመቶችን ስንቃኝ ” ዊልፍ ሎው በ1910-11 በነበረው ሙሉ የውድድር ዘመን የገጠሙትን ሁሉንም የመሃል አጥቂዎች ዝናና ክብር ድባቅ ሲመታ ነበር፡፡” የሚሉ በርካታ ምስክርነቶችን እናገኛለን፡፡

አዝማሚያው ከዊልፍ ሎው ግራና ቀኝ የሚሰለፉ የኋላ-መስመር አማካዮችም በላይ የመሃል-ተከላካይ አማካዮች የመከላከል ኃላፊነት እንደተጫነባቸው አመላከተ፡፡ የሼፊልድ ዩናይትዱ የመስመር ተከላካይ በርኒ ዊልኪንሰን ” የመሃል- ተከላካይ አማካዮች(ሴንተር ሃፍ ባክ) አመዛኙ ትኩረታቸውን በመከላከል ላይ፥ የመስመር አማካዮች ደግሞ በማጥቃቱ ላይ መሆን ይኖርበታል፡፡” ብሎ ጽፏል፡፡ በአንጻሩ የብሪስቶል ሲቲው የመሃል ተከላካይ አማካይ ቢሊ ዌድሎክ  ” የመሃል-ተከላካይ አማካይ ኃላፊነት የተጋጣሚ ቡድን የመሃል አጥቂን መቆጣጠር ነው፡፡ ተጫዋቹ ይህንን ግዴታ በጥሩ ብቃት ከተወጣ የትኛውም የአለም ምርጥ የተባለ አጥቂ ክልላቸውን በአግባቡ በሚጠብቁ ሃይለኛ ታክለሮች ስለሚቸገር ውጤታማ እንቅስቃሴ ማድረግ ይሳነዋል፡፡” ሲል ይሞግታል፡፡

በ1897 ጅማሮ ላይ ሲቢ ፍሬይ የመሃል ተከላካይ አማካይን ሚና በመከላከሉ ብቻ ገድቦ የመጠቀም ታክቲክን በመጥቀስ ” ለወትሮ አንድ ቡድን 1-0 አልያም 2-0 እየመራ መከላከልን ቅድሚያ የመስጠት ዝንባሌ አሳይቷል፡፡ ከፊት መስመር ተሰላፉዎቹ አንዱን በመቀነስም ሶስተኛ ተከላካይ ቀይሮ አስገብቷል፡፡ አጥቂን ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ ከማድረግ፣ ቁጥሩን ከመቀነስ እንዲሁም ተከላካይ ተጫዋች ከመጨመር አንጻር ብዙ ሊባል ይችላል፡፡ በእርግጥ ሶስት ተከላካዮችን ማለፍ እጅግ ፈታኝ ነው፤ ይሁን እንጂ ተጫዋቾቹ የሁለገብነት ድርሻ የማይኖራቸው ከሆነ እና የተቀየረ ሚና ሲሰጣቸው በአመርቂ ሁኔታ የማይወጡት ከሆነ ሶስተኛ ተከላካይ ማሰለፉ ጠቃሚ አይደለም፡፡ የግድ ተጨማሪው ተከላካይ በተሰጠው ቦታ ብቁ መሆን ይጠበቅበታል፡፡” ሲል <ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ስፖርት ኤንድ ጌምስ> ላይ አስፍሯል፡፡

አንድን የፊት አጥቂ ወደ ኋላ አፈግፍጎ እንዲጫወት ማድረግ የመሃል ተከላካይ አማካይን በጥልቀት ከመግፋት እጅጉን ይለያል፡፡ ፍሬይ ላይ የተፈጠረውን ስሜት ለመግለጽ እንደሚቻለው በጨዋታ አቀራረቡ ወግ አጥባቂ ለሆነ ሰው አንድ ተከላካይ መጨመር ብዙውን ጊዜ 2-3-5 ፎርሜሽን ሊለወጥ የሚችል ነገር እንደሆነ ማሳያነቱ ተረጋገጠ፡፡ ከሃያኛው መቶ ክፍለዘመን የመጀመሪያው አስርት ዓመት ጀምሮ ቡድኖች ከሜዳቸው ወጪ በሚከውኗቸው አስቸጋሪ ጨዋታዎች ላይ የመሃል-ተከላካይ አማካያቸውን በጥልቀት ወደ ኋላ እየሳቡ ማጫወታቸው ያልተለመደ ክስተት አልነበረም፡፡ ለምሳሌ የቀድሞው የቼልሲ አሰልጣኝ ዳቪድ ካልደርሄድ በ1993 <ቶምሰን’ስ ዊክሊ> በተሰኘ ፕሮግራም ላይ በሰጡት ቃለመጠይቅ ” በሶስት ተከላካዮች ጥምረት ይደረግ የነበረው አጨዋወት እኔ ተጫዋች በነበርኩበት ጊዜ እንኳ ስኬታማ እቅድ  እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ በእኛ ዘመን የስርዓቱ ዋነኛ አራማጅ እና ተግባሪ የቀድሞው ኖትስ ካውንቲና ደንዲ ዩናይትድ የመሃል-ተከላካይ አማካይ ኸርበርት ዳይንቲ ነበር፡፡” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ለመሃል-ተከላካይ አማካዮቻቸው የመከላከል ኃላፊነት ብቻ እየሰጡ የሚያሰልፉ ክለቦች እንደነበሩ የሚያሳዩ አጋጣሚዎች ቢኖሩም   ሃደርስፊልዶች ግን በእንግሊዛውያኑ ዘንድ እጅጉን የሚወደሰው የመስመሮች ጨዋታ ላይ ያን ያህል እምነት ባልነበረው አሰልጣኛቸው ታግዘው ይህንኑ ሚና ያልተለመደ ዘይቤ አላብሰውት ከሌሎች የተለየ ገጽታ ኖሯቸው ቀረቡ ፡፡ “በሜዳው ውስጠኛ ክፍል የሚደረጉ ቅብብሎች ያን ያህል አስደናቂ ባይሆኑ እንኳ ለዛ የሌላቸው አይደሉም፡፡ ውጤታማም ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንዲያው ዝም ብሎ በመስመሮች ላይ ስሜት አልባ በሆነ መልኩ ከመሮጥ እና ዘጠኝ ተከላካዮች እና አንድ አጥቂ ወደሚገኝበት የተጋጣሚ ጎል ክልል ኳስን ከማሻገርም ይሻላሉ፡፡” ሲል ቻፕማን ይሞግታል፡፡ በ1924 <ኤግዛማይነር> እንዳስነበበው “ሃደርስፊልዶች የሊጉን ዋንጫ ከወሰዱ በኋላ በአጫጭር ቅብብሎች የሜዳውን ቁመት የሚያዳርሰው የሊድስ ጎዳና ቡድን አጨዋወት ዝናው ናኘ፡፡”

ቻፕማን እግርኳስ እንዴት ባለ ሁኔታ መካሄድ እንዳለበት ያለው ጥርት ያለ ግንዛቤ ብቻ በቂ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ውስጡ ያነገበውን ራዕይ ወደ ተግባር ሊለውጥ የሚችልበት ቦታን መቆናጠጡ ነበር ወሳኙ ነገር፡፡ ሌላው ቢቀር በብሪታኒያ የመጀመሪያው ዘመናዊ የእግርኳስ አሰልጣኝ ነበር፡፡ አንድን ክለብ በኃላፊነት በማስተዳደርና በመምራት በኩል ባለሙሉ ስልጣን የነበረ የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡ የተጫዋቾች ዝውውርን ከመቆጣጠር አንስቶ የቡድኑን አጨዋወት ታክቲክ በመቀመርና በመምረጥ እንዲሁም ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ እና በዕረፍት ሰዓት ተመልካቹ የተዝናና መንፈስ እንዲያድርበት በስታዲየሞች ውስጥ የሚለቀቁ ዘፈኖችን በማጫወቻ ወይም መቅጃ መሳሪያዎች ሪከርድ በማድረግ ሙዚቃዎች እስከ ማዘጋጀት የደረሰ ስራ ነበረው፡፡ ሃደርስፊልዶች በ1925 የሊግ አሸናፊነታቸውን ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት <ዘ-ስፖርቲንግ ክሮኒክልስ>  ” በአሁኑ ጊዜ የእግርኳስ ክለቦች እንዲመሯቸው የሚመድቧቸው ሰዎች ጠቃሚነትን በትክክል ተገንዝበዋልን? ለተጫዋቾች ግልጋሎት እስከ አራት እና አምስት ሺህ ፓውንዶች ድረስ ለመክፈል ዝግጁ ናቸው፡፡ እና ታዲያ እነዚህ ክለቦች ተጫዋቾቻቸውን ለሚመሩላቸው ባለሙያዎች ያላቸው ዋጋ ምን ድረስ ነው…?” ሲል ዝርዝር ጥያቄዎችን አቀረበ፡፡ “በክለቦች ዘላቂ ህልውና ተጫዋቾችን የመመልመል እና የመምረጥ ኃላፊነቱን በሚገባ የሚወጣ፣ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚረዳ፣ ከእርሱ በሚተላለፉ ትዕዛዛት ተጫዋቾች ምርጥ ብቃታቸውን እንዲያወጡ የሚተጋው እጅግ ጠቃሚው ሰው አሰልጣኙ ነው፡፡” ሲል መሰረታዊ እውነታን አከለ፡፡

በቀጣዩ ዓመት ሃደርስፊልዶች ተከታታይ ሶስተኛ የሊግ ድላቸውን ከተቀዳጁ በኋላ ቻፕማን አብሯቸው አልዘለቀም፡፡ ከበስተ ደቡብ የነበረው የአርሰናል ክለብ እምቅ አቅም ማረከው፡፡ በእርግጥ ሁኔታው “ግልጽ አልነበረም፡፡” ቢባል ይቀላል፡፡ በወቅቱ ክለቡ ባለበት ሊግ ለመቆየት ትልቅ ትግል እያካሄደ ነበር፡፡ በኃይለኝነታቸውና በተለየ ጸባያቸው በሚታወቁት የክለቡ ሊቀመንበር ሰር ሄንሪ ኖሪስ ስር የምጥ ዓመት ሲያሳልፉ ከረሙ፡፡ ሶስት ሺህ ፓውንድ ለተጫዋቾች ግዢ መደበኛ የገበያ ዋጋ በነበረበት ጊዜ ከቻፕማን ቀደም ብሎ በክለቡ የነበረው አሰልጣኝ ሌዝሊ ናይቶን ግን ከአንድ ሺህ ፓውንድ በላይ እንዳያወጣ ገደብ ተጥሎበት ሰነበተ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቁመታቸው ከ1.73 ሜትር የሚያንስ ተጫዋቾች ወደ ክለቡ እንዳይቀላቀሉ የሚያስገድድ መመሪያም ወጣበት፡፡ በ1923 ናይተን የተጫዋቾች ቁመት ገደብን በመጣስ 1.3 ሜ ብቻ የሚረዝመውን ” ድንኩ” ሂዩጅ ሞፋትን ከወርኪንግተን አስፈረመ፡፡ ሆኖም የክለቡ አስተዳደር ኖሪስ ተጫዋቹ አንድም የሊግ ጨዋታ ሳያደርግ ወደ ሉተን ታውን ሰደደው፡፡ በ1924-25 የውድድር ዘመን መጨረሻ ላይ ኖሪስ “ናይተን ደካማ ውጤት አስመዝግቧል፡፡” በሚል ሰበብ ከክለቡ አሰናበተው፡፡ ናይተን ግን “ክለቡ ከገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታዎች የሚያስብልኝን የማበረታቻ ተጨማሪ ክፍያዎች ላለመክፈል ስለፈለጉ የወሰዱት እርምጃ ነው ሲል የክለቡ ውሳኔ ላይ ቅሬታውን ያቀርባል፡

ይቀጥላል...


ስለ ደራሲው 

ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡  ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም የሚከተሉትን ዘጠኝ መጻህፍት ለህትመት አብቅቷል፡፡

Behind The Curtain: Travels in Eastern European Football (2006)

Sunderland: A Club Transformed (2007)

Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics (2008)

The Anatomy of England (2010)

Brian Clough: Nobody Ever Says Thank You: The Biography (2011)

The Outsider: A History of the Goalkeeper (2012)

The Anatomy of Liverpool (2013)

Angels With Dirty Faces: The Footballing History of Argentina (2016)

The Barcelona Legacy: Guardiola, Mourinho and the Fight For Football’s Soul (2018)


ቀደምት ምዕራፎች
መቅድም LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 1 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አንድ LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሁለት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል ሶስት LINK
ምዕራፍ 2 – ክፍል አራት LINK
ምዕራፍ 3 – ክፍል አንድ
LINK

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *